Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከስድስት ዓመት ተኩል በላይ የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ታዬ ዲበኩሉ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ተሰማ፡፡

አቶ ታዬ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ግፊት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በምትካቸው የባንኩ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ ከበደ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሠሩ ቦርዱ ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል፡፡

አቶ ታዬ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ ኅብረት ባንክን ከተቀላቀሉ በኋላ በፕሬዚዳንትነት እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡

ለአቶ ታዬ ከኃላፊነት መልቀቅ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በተለይ በቅርቡ ባንኩ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩ አፈጻጸም ከሌሎች ባንኮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው ተብለው በባለአክሲዮኖች መሞገታቸው ታውቋል፡፡ ባንኩ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 979 ሚሊዮን ብር በማትረፉ፣ ባለአክሲዮኖች ተቃውሞ በማሰማታቸው ቦርዱ በጉዳዩ ላይ መክሮ ውሳኔ እንዲሰጥ አስገድዶታል ተብሏል፡፡

የኅብረት ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ ከበደ

 

ባለአክሲዮኖች ኅብረት ባንክ የዕድሜውን ያህል አፈጻጸሙ በቂ አይደለም ከማለታቸው በተጨማሪ፣ በቦርዱና በእሳቸው መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከኃላፊነታቸው ለመልቀቃቸው ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል፡፡ ምንጮች እንደሚሉት የባንኩን አሠራር ለማጠናከር ሌሎች ተጨማሪ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አቶ ታዬን ተክተው በተጠባባቂነት የተሰየሙት የባንኩ አይቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ በዋናነት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ልምድ ያቸው ባለሙያ ናቸው፡፡ የተሰጣቸው ኃላፊነት የሚፀናው የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክን አዎንታ ሲያገኝ ነው፡፡ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ኃላፊነታቸውን እንዲረከቡ መደረጉ ታውቋል፡፡ አቶ ታዬን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁለት ሳምንት በፊት የባንኩ ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ አዳዲስ የቦርድ አባላትን ለመምረጥ ባካሄደው ምርጫ፣ በዕጩነት ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች ውስጥ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙት ሦስቱ ቦርዱን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ ሦስት ዕጩ የቦርድ አባላት ውስጥ የቀድሞው የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ለመሆን የሚያስችላቸውን ውጤት አግኝተዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ በዕለቱ ከ14.02 ሚሊዮን በላይ የአክሲዮን ድምፅ ሲያገኙ፣ አቶ ኤፍሬም ኃይለ ማርያም 12 ሚሊዮን የአክሲዮን ድምፅ፣ እንዲሁም ኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ 7.2 ሚሊዮን የአክሲዮን ድምፅ አግኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች