የዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ (ዋዳ) ሩሲያን በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድሮች እንዳትሳተፍ የአራት ዓመት እገዳ መጣሉን አስታወቀ፡፡ ተቋሙ በተለይ በአትሌቲክሱ ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥርና ክትትል ከሚያደርግባቸው አገሮች አንዷ እንደሆነች የሚነገርላት ኢትዮጵያ ከሩሲያ ትልቅ ትምህርት ልትወስድ ይገባል የሚሉ አሉ፡፡
ዋዳ የሩሲያ አትሌቶችን በሚመለከት ከአገሪቱ መንግሥት ጋር ከፍተኛ ሊባል የሚችል አለመግባባት ውስጥ ገብቶ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ጉዳዩን ችላ ያለው የሩሲያ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ጥረት አላደረገም በሚል በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክና በ2022 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ላይ ምንም ዓይነት ውክልና እንዳይኖረው እገዳ የጣለበት መሆኑ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡
ሩሲያ እ.ኤ.አ. 2015 ጀምሮ በአትሌቲክስ ውድድሮች እንደ አገር ተሳትፎ እንዳይኖራት አድርጎ መቆየቱን ያስታወቀው ዋዳ፣ በ2018 በፒዮንግያንግ በተደረገው የክረምት ኦሊምፒክ 168 የሩሲያ አትሌቶች የአገር ውክልና ሳይኖራቸው መሳተፋቸው የሚታወስ ነው፡፡ በፒዮንግያንግ የክረምት ኦሊምፒክ የተሳተፉት የሩሲያ አትሌቶች፣ 33 ሜዳሊያዎች ሲያስመዘግቡ ከዚህ ውስጥ 13 የወርቅ ሜዳሊያዎች መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ እንደ ዋዳ መረጃ ከሆነ ይህ እገዳ በ2020 የሚደረገውን የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ አይመለከትም፡፡
ዋዳ ከሦስት ዓመት በፊት ባደረገው ማጣራት በአበረታች ቅመሞች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተዋል ብሎ ከፈረጃቸው አምስት የዓለም አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረች ይታወሳል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ችግሩን ለመከላከል ያደረገችውን ጥረት ግምት ውስጥ ያስገባው ዋዳ፣ ክትትሉ ሙሉ በሙሉ ባይባልም ችግሩን ለመከላከል ራሱን የቻለ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ናዶ) በማቋቋም ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እያደረገ መሆኑ የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ድረስ ያስረዳሉ፡፡ እንደ ኃላፊው ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ በቁጥር አንድ ከሚጠቀሱ አገሮች እንደመሆኗ ዋዳ በ”ኤ” ምድብ ውስጥ እንደምትገኝ ግን አልሸሸጉም፡፡