Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልዩኔስኮ የጥምቀት በዓልን ጨምሮ በ42 ዕጩዎች ላይ በዚህ ሳምንት ውሳኔ ይሰጣል

ዩኔስኮ የጥምቀት በዓልን ጨምሮ በ42 ዕጩዎች ላይ በዚህ ሳምንት ውሳኔ ይሰጣል

ቀን:

ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ ለዘንድሮ በዓለም ወካይ ቅርስነት በታጩ 42 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ላይ እየመከረ ነው፡፡ በኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ ከኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ቀን 14ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ የሚገኘው የበይነ መንግሥታዊ ኮሚቴ መርምሮ ውሳኔ ከሚሰጥባቸው ከተለያዩ አገሮች ከታጩት የማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ የኢትዮጵያ የጥምቀት ክብረ በዓል ነው፡፡

የሞሮኮ፣ ናይጀሪያ፣ ሲሸልስ፣ ግብፅ፣ ሞሪታንያ፣ ሱዳንና ቱኒዝያ ባህላዊ ቅርሶችም ለውሳኔ መቅረባቸውን ዩኔስኮ በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡

በየዓመቱ በዋናነት ጥር 11 የሚከበረውና ዋዜማውንና ማግሥቱን ጨምሮ ለሦስት ቀናት የሚዘልቀው የጥምቀት ክብረ በዓል በብሔራዊ ደረጃ የተመዘገበው ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለዩኔስኮ የተላከው ሰነድ ምን ይላል?

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የጥምቀት ክብረ በዓልን በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ እንዲገባ፣ ለመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ በላከው ሰነድ እንደተመለከተው፣ ጥምቀት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ መሠረት ታሪካዊ መሠረቱን ሳይለቅ አሁን እንዳለው መከበር የጀመረው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ነገሥታቱ አብርሃና አጽብሐ የክርስትና ሃይማኖትን ተቀብለው ብሔራዊ ሃይማኖት ሲያደርጉ የጥምቀት በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር አድርገዋል፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በብሉይ ኪዳን ሥርዓት መሠረት ሲከበር የኖረ ‹‹የበዓለ መጸለት/የዳስ በዓል›› የሚባል ስለነበር ጥምቀት በእሱ ምትክ የጉዞና የአደባባይ በዓል ሆኖ እንዲከበርም አድርገዋል፡፡

እነዚህ ቅዱሳን ነገሥት ለሃይማኖቱ ማደግ ብቻ ሳይሆን ለበዓሉም መስፋፋት ተግተው ሠርተዋል፡፡ በዓሉ በየዘመኑ እያደገ መጥቶ በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ያሬድ በዘመኑ ይፈጸም የነበረውን የበዓሉን አከባበር ሥርዓት በማየት ለበዓሉ አከባበር የሚስማማ የዜማ ሥርዓት አዘጋጅቷል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለበዓሉ ያዘጋጀው የዜማ ድርሰትም ከበዓሉ ዋዜማ (ከተራ) ጀምሮ የሚፈጸም በመሆኑ ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀትንና ሥርዓትን ሰጥቶታል፡፡

ቅዱስ ላሊበላም 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአንድ ወጥ ዓለም ፈልፍሎ ባነፃቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥራ ውስጥ በዓሉን ሁሉም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት የሚያከብሩበትን ቦታ በዮርዳኖስ ወንዝ ስም ምሳሌነት አካቶ ሠርቶታል፡፡ እስካሁንም ድረስ በላሊበላ ከተማ የሚገኘው ይህ ቦታ ‹‹ዮርዳኖስ›› በመባል ይታወቃል፡፡

ከዚያ በኋላ የተነሱ ነገሥታት እንደ አፄ ይኩኖ አምላክ (13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) አፄ ዘርዓ ያዕቆብና አፄ ናኦድ (15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ካህናቱና ሕዝቡ ታቦታቱን አጅበው በአንድነት የሚያከብሩትን ይህንን ጥንታዊና መንፈሳዊ በዓል በየዘመናቸው ደምቆ እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይወሳል፡፡ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም በጎንደር የነገሡት አፄ ፋሲል ለመዋኛ ገንዳ ያሠሩት የጥምቀት በዓል ማክበሪያ የተደረገ ሲሆን፣ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ከነገሡት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጀምሮ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በዓሉ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡

ለሦስት ቀናት ያህል (ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ) በተከታታይ በሚከበረው በዚህ ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ መንፈሳዊ መዝሙሮች፣ የተለያየ ስልት ያላቸው ያሬዳዊ ዜማዎች ይደመጣሉ፡፡ በበዓሉ ላይ የየአካባቢው አገረሰባዊ ዘፈኖች፣ ጭፈራዎችና ውዝዋዜዎች በስፋት ይከናወናሉ፡፡ የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎችም ይደረጋሉ፡፡ በዓሉም እነዚህን የትውን ጥበባትና የሥነ ቃል ሀብቶች ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ይላል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለዩኔስኮ በላከው የይመዝገብልኝ ሰነድ፡፡ 

ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ ገጽታው ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡

በየዓመቱ በኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን እንደሳበ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምእመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ  በሚማርኩ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁልጊዜ አዲስ ነው። ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።

የጥምቀት ክብረ በዓልን በዩኔስኮ በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity)  የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በይፋ እንቅስቃሴ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች  ያደረገውን ጥናት አጠናቆ  ከቀነ ገደቡ ከመጋቢት 22 ቀን 2010 .. በፊት ለዩኔስኮ መላኩ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ እሰካሁን ያስመዘገበቻቸው ሦስት የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች  የመስቀል ክብረ በዓል፣ የፊቼ ጫምባላላ እና የገዳ ሥርዓት መሆናቸው ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...