Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ባንክ ከታክስ በፊት 625 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አሥረኛ ዓመቱን የያዘው ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 625 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገልጿል፡፡ ባንኩ ባለፈው እሑድ ኅዳር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ እንዳሳወቀው፣ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው የትርፍ መጠን ከቀዳሚ ዓመት የ198 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ የ2011 የሒሳብ ዓመት ለዘርፉ ፈታኝ የሆኑ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዓመት እንደነበር ያመለከቱት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሰውአለ አባተ (ዶ/ር)፣ በተለይ ከፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የተከሰተው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በአገር አቀፍ ደረጃ የወጪ ንግድና የሐዋላ መዳከምን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት መባባስ ዋና ዋናዎቹ ቢሆንም ባንኩ አትራፊ መሆን ችሏል ብለዋል፡፡

ይህም ቢሆንም ግን ባንኩ የተሻለ ትርፍ ማስመዝገቡንና ከታክስ በፊት የተገኘው ትርፍም የ46.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው ባንኩ ሊቀነሱ የሚችሉ ወጪዎችን በጥንቃቄ በማስተዳደርና ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል በተደረገው ጥረት እንደሆነም የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

ከዓመታዊ ሪፖርቱ መረዳት እንደሚቻለው፣ ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገቱ እንደ ቀዳሚዎቹ ዓመታት ያነሰ መሆኑን ነው፡፡ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገት ከብዙዎቹ ባንኮች በተለየ የሚታይም ነው፡፡ ከሌሎች ባንኮች አንፃር ብቻ ሳይሆን ባንኩ ባለፉት ተከታታይ ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገቱ በባለሁለት አኃዝ ዕድገት የነበረው ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ግን የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገቱ በስድስት በመቶ የተወሰነ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት መገንዘብ እንደሚቻለው፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ዕድገት በስድስት ሚሊዮን ብር በመጨመር 10.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ነው፡፡ በ2010 ሒሳብ ዓመት የተቀማጭ ገንዘቡን 9.4 ቢሊዮን ብር ሲያደርስ፣ ከ2009 ዓ.ም. አንፃር ሲታይ በ2.1 ቢሊዮን ብር በማሳደግ ነበር፡፡

በአንፃሩ ግን ባንኩ የአስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥር በ55 በመቶ አሳድጓል፡፡ ይሁንና የአስቀማጮችን ቁጥር በ2010 ከነበረው 349,000 በ2011 የሒሳብ ዓመት ወደ 541,000 ቢያደርስም፣ የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን ግን በአስቀማጮቹ ቁጥር አንፃር ያለማደጉን ያሳያል፡፡

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 10.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከቀዳሚ ዓመት ዕድገት ያሳየው በ639 ሚሊዮን ብር ወይም (6.4 በመቶ) ብቻ ነው፡፡ በአንፃሩ ባንኩ ለብድር ያዋለው የገንዘብ መጠን የ19.2 በመቶ ዕድገት በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 8.28 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የብድር መጠኑ በ1.3 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ይህ ውጤት የተመዘገበው ባንኩ ከሚሰጠው አዲስ ብድር ውስጥ 27 በመቶ የሚሆነውን ለብሔራዊ ባንክ የቦንድ ግዥ በዋለበት ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ የሚያስታውሰው የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት፣ እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስም ባንኩ ለብሔራዊ ባንክ የቦንድ ግዥ 3.26 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባንኩ የአጭር ጊዜ ብድሮችን ድርሻ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የ40 በመቶ ድርሻ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ስለመደረጉና የብድር ሥርጭቱ ሁሉንም የኢኮኖሚ ዘርፎች መሸፈኑም ተመልክቷል፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከተሰጠው ብድር የገቢና የወጪ ንግድ ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡ ግብርና ደግሞ ዝቅተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ክፍያቸው አጠራጣሪ የሆኑ ብድሮች ከጠቅላላው ብድር ያላቸው ድርሻ 3.86 በመቶ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ባንኩ በተለያዩ አፈጻጸሞቹ ከፍተኛ የሚባለውን ውጤት ካስመዘገበባቸው ውስጥ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎትን የተመለከተው አፈጻጸሙ ደግሞ 194.6 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ያሳያል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር የ60 በመቶ ወይም (73.4 ሚሊዮን ዶላር) ብልጫ አለው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት 403.1 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ90 በመቶ ወይም የ191 ሚሊዮን ብር ዕድገት አለው፡፡ ይህ ውጤት የተመዘገበው በአገር አቀፍ ደረጃ የወጪ ንግድ ገቢ በተቀዛቀዘበትና በኢንዱስትሪው ውስጥ ከውጭ ምንዛሪ ማሰባሰብ ጋር ተያይዞ ያለው ውድድር ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠንካራ ሆኖ እየመጣ ባለበት ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ አበረታች መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ገቢ በ31.7 በመቶ ወይም የ441 ሚሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ 1.833 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የቦርድ ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል፡፡

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጠቅላላ ሀብቱ የ11.3 በመቶ ወይም የ1.47 ቢሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት ወደ 14.5 ቢሊዮን ብር ሊያድግ ችሏል፡፡ የተጣራ የብድር መጠኑ ከባንኩ ጠቅላላ ሀብት ውስጥ 57 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከፍተኛውን መጠን ይዞ ይገኛል፡፡

እ.ኤ.እ. ሰኔ 30 ቀን 2019 ላይ የባንኩ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል፣ ሕጋዊ መጠባበቂያ፣ ልዩ መጠባበቂያና ያልተከፈለ ትርፍን ጨምሮ የ585 ሚሊዮን ብር ወይም የ29.5 በመቶ ዕድገት በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ 2.57 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተከፈለ ካፒታል የአጠቃላይ ካፒታሉን 68.9 በመቶ ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ በ296.3 ሚሊዮን ብር ወይም 20.1 በመቶ ዕድገት በማሳየት 1.77 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ለነባር ባለአክሲዮኖች የተጨማሪ አክሲዮን ሽያጭ መከናወኑ ለተመዘገበው የካፒታል ዕድገት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ምክንያት እንደሆነም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

ባንኩ በሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎትን ለመጀመር ሙከራ በማድረግ ውጤታማ መሆኑን የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሙሉ ትግበራ አገልግሎት ፈቃድ በማግኘት የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎቱን መስጠት ጀምሯል፡፡ የወኪል ባንክ አገልግሎት በተመለከተ በሒሳብ ዓመቱ የወኪል ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሙከራ አገልግሎት ፈቃድ አግኝቷል፡፡ ባንኩ የቅርንጫፎች አድማሱን በማስፋት ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ብሎም የተቀማጭ ማሰባሰቡን ሥራ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል፣ 34 አዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ አጠቃላይ የባንኩ የቅርንጫፎች ቁጥር 205 ማድረስ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች