Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአጽንኦት የሚሻው ኤችአይቪ ኤድስ

አጽንኦት የሚሻው ኤችአይቪ ኤድስ

ቀን:

በተመስገን ተጋፋው

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤችአይቪ ኤድስ በሽታ ከ32 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ 37.9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል፡፡ በየዓመቱም 1.7 ሚሊዮን ሰዎች በኤችአይቪ ይያዛሉ፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ፡፡

ኤችአይቪ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከታወቀበት ከ1980ዎቹ አንስቶ ወረርሽኙን የመከላከል ጥረቶች ሲደረጉ የቆየ ቢሆንም፣ ምላሹ ወደ ላቀ ደረጀ የተሸጋገረው ግን በ1990 ዓ.ም. የኤችአይቪ ኤድስ ፖሊሲ መቀረፁን ተከትሎ ነው፡፡

ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፉን ለማስቆም በአዲስ አበባ 166 የሚሆኑ የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በ2011 በጀት ዓመት ኤችአይቪ ኤድስ በደማቸው እንደሚገኝ ከሚገመቱ ነፍሰ ጡር እናቶች መካከል ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው 23,433 መሆናቸውን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ሕክምና አስተባባሪ ዶ/ር መስፍን አጋጨው ተናግረዋል፡፡ ከተወለዱ ሕፃናት ውስጥም የፀረ ኤችአይቪ ኤድስ ሕክምና ያገኙት 13,825 እንደሆኑም ዶ/ር መስፍን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 613,829 የሚሆኑ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሲሆን፣ 109,860 የሚሆኑትም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን ዶ/ር መስፍን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 436,000 መድኃኒታቸውን ሳያቋርጡ የሚወስዱ መሆኑን አክለዋል፡፡ 232,626ቱ የቫይረሱ ተጠቂ ወንዶች፣ 381,199ኙ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡

ለቫይረሱም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች፣ ትዳራቸውን የፈቱ፣ የትዳር አጋራቸው የሞቱባቸው ግለሰቦች፣ የረዥም ርቀት ሾፌሮች፣ የቀን ሠራተኞች፣ በካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችና የሕግ ታራሚዎች እንደሆኑ ዶ/ር መስፍን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ እ.ኤአ. በ2018 በተሠራው ጥናት መሠረት ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 610,335 ሲሆን፣ የሥርጭቱ ምጣኔም 0.9 በመቶ ነበር፡፡ ከኤችአይቪ ጋር ይኖሩ የነበሩ ሕፃናት ቁጥርም 56,514 ወይም ከጠቅላላው የዘጠኝ በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡

አብዛኛው የቫይረሱ ጫና ያለባቸው የአፍሪካ አገሮች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ቦትስዋና፣ ሌሴቶ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ በአፍሪካ 25.7 ሚሊዮን፣ በአሜሪካ 3.5 ሚሊዮን፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ 3.8 ሚሊዮን፣ በአውሮፓ 2.5 ሚሊዮን፣ በምሥራቅ ሜዲትራኒያን 400,000፣ በምሥራቅ ፓስፊክ 1.9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ዶ/ር መስፍን ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ ዓለም ላይ በቀን አምስት ሺሕ የሚሆኑ ሕፃናትና ወጣቶች በቫይረሱ ይያዛሉ፡፡ 64 በመቶ የሚሆኑትም በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ናቸው፡፡ 4,500  የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሚሆናቸው ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ኤችአይቪን ለመከላከል ለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እ.ኤ.አ. ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ አራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አግኝታለች፡፡ ይህም በአማካይ በየዓመቱ 250 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 እና በ2011 ዓመት ከ400 ሚሊዮን ዶለር በላይ ተገኝቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2012 በኋላ ግንየሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከግማሽ በላይ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በ2019 170 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብቻ እንደተመደበም መረጃው ያሳያል፡፡  

እ.ኤ.አ. በ2030 የኤችአይቪ ኤድስን ሥርጭት ለማቆም የተያዘውን ራዕይ ከግብ ለማድረስ አገሮች ስምምነቱን ተቀብለው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ራዕይ ከግብ ለማድረስ የተለያዩ ግቦችን አስቀምጣ በመተግበር ላይ ነች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 ሦስት ዘጠናዎች የተባሉ ግቦችን አስቀምጣ ለማሳካት እየሠራች ነው፡፡

90 በመቶ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ፣ ተመርምረው ኤችአይቪ በደማቸው መገኘቱን ካወቁ ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑትን የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ፣ ሕክምና ከጀመሩት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑትን ሕክምናቸውን በትክክል ተከታትለው በደማቸው ውስጥ ያለውን የቫይረሱን መጠን መጠን ዝቅ ማለቱን ማረጋገጥ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...