Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ደስ ይበለን እንጂ!

ሰላም! ሰላም! ኧረ ይኼ ከአውሮፓ በረዶ በተውሶ የመጣ ቅዝቃዜ እንዴት ነው? አልቻልነውም እኮ! እስኪ አስቡት በዚህ የሰቀቀን ኑሮ ላይ ሌላ አሰቃቂ ቅዝቃዜ ተጨምሮበት። በፊት የአየር ንብረት ለውጥ ሲባል ምንም የማይመስለኝ ሰውዬ አሁን ችግሩ እየገባኝ ነው፡፡ ያለ ጊዜው የሚከሰት ደመና የዝናብ ዶፍ ይዞ ከች ሲልና የማናውቀው ዓይነት ቅዝቃዜ ሲያንገበግበን ችግሩ ካልገባን፣ ልክ እንደ እነ አቶ ትራምፕ የባጥ የቆጡን ያስቀባጥረናል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር እየፈጠረ ነው ሲባሉ ሐሰት ነው አሉ፡፡ ምድር በካርቦን ሙቀት እየጋለች የሰሜን በረዶ እየቀለጠ ጎርፍ ሲበዛ፣ ‹‹አያችሁ እናንተ ሙቀት ከመጠን በላይ ሆነ ስትሉ ቅዝቀዜና ጎርፍ ደግሞ እያስቸገሩን ነው. . .›› ብለው መሳቂያ መሳለቂያ መሆናቸውን የነገረኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ የአርክቲክ በረዶ መቅለጥ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መሆኑ ያልገባቸው ሰው፣ አሜሪካን የምታህል ልዕለ ኃያል አገር ይመራሉ ሲባል ያስደነግጣል፡፡ እኛም አንችለው የለም ይኼው ኑሮንም ቅዝቃዜውንም ችለን ሰንብተን ተገናኝተናል።

እንዲያው አብዛኛውን ሰው ወክዬ የሰሞኑን አጥንት ቆርጣሚ ቅዝቃዜ ማንሳቴ ነው እንጂ፣ እኔስ እውነት ለመናገር ዕድሜ ለማንጠግቦሽ ሙቀቱ አልተለየኝም። ይብላኝ ፍቅርና አብሮነት መሀል ፖለቲካና ነገር እየቆሰቆሱ ለተኳረፉ። እንዲያው እናንተ ምነው ሰው ግን እንዲህ የፍቅርና የአንድነት ጠላት ሆነሳ? ‹‹ፍቅርና አብሮነት የሚገኘው በመተሳሰብ ውስጥ እንጂ ለብቻ በሚከማች ገንዘብ ወይም ወዳጅነት ውስጥ አይደለም፤›› ብዬ ለአዛውንቱ ባሻዬ ብሶቴን ባሰማ፣ ‹‹ልፋ ቢልህ እንጂ የዚህ ዘመን ሰው መካሪ የሚያሻው ነው? አውቆ አጥፊ ሁላ!›› ነበር መልሳቸው። እውነት ነው እኮ! አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት መቼ ይሰማል? በተለይ የአገራችንን ፖለቲከኞችን ሳስብ አውቆ ከመተኛት በላይ ድንቁርና የተጠናወታቸው ይመስለኛል፡፡ ያውም ዕድሜና መማር የማይገራው ድንቁርና! ለአገሩ የሚያስብና የሚለፋማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሮ ሲያከብረን ሲያዩ ቢማሩ ምናለበት?

 እንዳልኳችሁ ሰው በሚያገኘው ቀዳዳ ሁሉ ሥራው ጎራ መለየት ሆኗል። ለሌላው አለማሰብና ለራስ ብቻ መኖር ገኗል። በቀደም ምን ሆነ መሰላችሁ? አንድ የሚከራይ ቪላ ቤት ነበርና የሚከራይ ለማግኘት ላይ ታች ስል ውዬ በመጨረሻ ተሳክቶልኝ ተከራይ አገኘሁ። ሰውዬው ብቻውን ነው። ልጅም ሚስትም የለውም። ‹‹እንዴት ነው ቤተሰቦችህ በአገር የሉም?›› አልኩት ጎልማሳነቱንና መልከ መልካምነቱን መላልሼ እያየሁ። ‹‹የለም! ቤተሰብ ምን ይሠራል?›› ቢለኝ ክው አልኩላችሁ። ይህችን ይወዳል አንበርብር ምንተስኖት? ምነው ተዘጋጅ እንኳ ቢለኝ እያልኩ፣ ‹‹እንዴ! ምን ለማለት ነው?›› አልኩት በደረቀ ድምፅ። ‹‹በዚህ ጊዜ ቤተሰብ? ያምሃል እንዴ? ሚስት ከመፈለግ ነዳጅ ብፈልግ ብቻዬን ይሳካልኛል እኮ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ሰው አምርሯል ማለት እኮ ይኼ ነው። ቀላል አምርሯል? ወዲያው ከምሬቱ ጀርባ ምን እውነት ቢኖር ይሆን? ብዬ መመራመር ጀመርኩ። እንዲህ ዓይነት ሰው ጠፍቶ እኮ ነው ምሬታችን ገደቡን ያለፈው፡፡ መልሱን ታዲያ አንድ ወዳጄ ድሮና ዘንድሮ በሚለው ጨዋታው ውስጥ ያገኘሁት መስሎኝ ከእሱ ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜ ያወጋኝን አሰላስል ጀመር። በማሰላሰሌ መሀል ደግሞ ብቸኝነት የሚባለው ነገር አልገባኝ አለ፡፡ ብቸኝነት ከፖለቲካ ለመሸሽ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ ለመገለል፣ ቤተሰባዊ ሕይወትን ላለመቀበል፣ ወዘተ. እያልኩ ሳስብ ውስጡ ንፉግነት ታየኝ፡፡ ለነገሩ ንፉግነት የተጠናወተው ለአገርም አይበጅም ነው የሚባለው! ልክ ይመስለኛል! ለምን መሰላችሁ ለአገር የሚበጅ ክብሩ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ነው፡፡

ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል አይደል ወጉ? ድሮና ዘንድሮ በማለት የቤቱን ድባብ ወዳጄ ያጫወተኝ እንዲህ ብሎ ነበር። ‹‹ድሮ ትዳር ለመያዝ ገና ማቀድህ ሲሰማ ደግሶ ከመዳር አልፎ፣ በርታ እስከምትል ድረስ ቀለብ ሸመታ ሳይቀር ዘመድ ወዳጅ ያግዝሃል። ‘አይዞህ’ የሚልህ የሚጠይቅህ አገር ምድሩ ነው። አንተ አመል ይኑርህ እንጂ ሚስትህም አጋርህ፣ ዓይንህን ዓይታ የምታስበው የሚገባት፣ ከሌላው ነገር በፊት ትዳሯና ቤቷ የሚበልጥባት ነበረች፤›› አለና ጥቂት ራሱን በአሉታ አወዛወዘ። ‹‹አሁንስ?›› እለዋለሁ ወሬው ግላዊ አመለካከትና አስተያየት የሰፈነበት እንደሆነ እየተገነዘብኩ፣ ‹‹አሁንማ ብቸኝነት ቢጠናብህ ከሰልህን ገዝተህ፣ በቆሎህን እየጠበስክ በቴሌቪዥንህ ብትፈልግ ፊልም ካልሆነም ሙዚቃ ታያለህ እንጂ ከሌለህ ማን ሊጠጋህ? የኑሮህ ደረጃ እየተለካ ወዳጅነት በሚመሠረትበትና ዝምድና በሚፈለግበት ጊዜ ላይ ነን ያለነው፡፡ ትዳርም የሚመሠረተው እኮ የመደብ ጀርባህ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ አነጋገር ማንነትህም ይበጠራል፡፡ አበቃ!›› አለኝ እጁን ወደ ሰማይ እየዘረጋ። እኔም፣ ‹አይ አንተ! የእኛንስ የፀባይ ለውጥ መቼ አየኸውና?› ብዬ ክፉ ሳልናገር ተሳስቄ ዝም። ሰው አመለካከቱንና እምነቱን ሲነኩበት ተርብ ሆኗላ ጎበዝ!

ታዲያ ቪላ ቤቱን የተከራየው ደንበኛዬም ይኼን አስተሳሰብ የደገመው ስለመሰለኝ ለማጣራት ደግሜ ብጠይቀው፣ ‹‹ወንድሜ  በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ገንዘብ ተኮር ሆኗል። ዕድሜ በቡድን ዘርፈው በቡድን እየተከፋፈሉ ለሚያባሉን። ወንድሜ ትዳር ለመፈለግ ስንቀሳቀስ የምጠየቀው የእነ ማን ወዳጅ ነህ? አካውንትህ ውስጥ ስንት ሚሊዮኖች ይንቀሳቀሳሉ? ስንት ባንኮች ውስጥ ምን ያህል ሼሮች አሉህ? ከባለሥልጣናትና ተቀባይነት ካላቸው ፖለቲከኞች ጋር ቅርበት አለህ ወይ? ግንባር ቦታዎች ላይ መሬቶች ይዘሃል ወይ? ወዘተ. የመሳሰሉ ጥያቄዎች አሰለቹኝ. . .›› አለኝ። ይኼም አለ እንዴ ብዬ ኮሚሽኔን ተቀበልኩና ተሰናበትኩት። መቼስ በአንድ ጀንበር እንዲህ ያለ ለጆሮ የሚከብድ ወሬ መስማት ይከብዳል። የጥቂቶች አዋዋልና አዳር ለብዙዎች መገለጫና ስም ሲሆን ግን ያሳዝናል። በጣም ያሳዝናል፡፡ በበኩሌ ነገራችን ሁሉ ለሕዝባችን ባዕድ ሆኖ እኛ ግን በሕዝብ ስም ስንነግድ ማለት ነው፡፡ አውሮፓና አሜሪካ በቢዝነስ ክላስ ቲኬት የሚያካልሉ ቅንጡዎች ከማንም በላይ ሕዝባዊ ነን እያሉ ሲፎልሉ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ምቾታቸው አይገርመኝም፣ የሚገርመኝ ምቾታቸውን ለደሃው ለማካፈል ወይም እንዲያገኘው ለማድረግ ቅንጣት ጥረት ሳያደርጉ ዣንጥላ ተሸካሚ መፈለጋቸው ነው. . .›› ሲለኝ ሳቄ ከሠፈራችን አልፎ ከተማው መሀል የተሰማ መሰለኝ፡፡ አንጀታችን እያረረ እንሳቀው እንጂ! 

እናላችሁ ሰሞኑን ቅዝቃዜው ሲጠናብኝ ነገር ዓለሙ እያስጠላኝ ቤቴ ተጠቅልዬ ከማንጠግቦሽ ጋር ሳወጋ፣ ከዚያም ከዚህም የለቃቀምኩትን ወግ እያነሳሁ ሳጫውታት እውላለሁ። ድንገት እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነገር ሳላስበው ካፌ ካመለጠ፣ ‹‹ኧረ አንተ ሰውዬ ተወኝ ስለፈጠረህ? ለምንድነው እንደ አገሬ ፖለቲከኞች የሚምታታ ነገር መዘባረቅ? ቀጥ ያለ ነገር አውራ! ተምታቶ ማምታታት እንኳን ለአንተ ለፖለቲከኞችም አልጠቀመ፤›› አለችኝ። ይኼ ፖለቲካ ፓርቲ በቃ የሁሉም አፍ ማሟሻ ሆነ እያልኩ በሆዴ ‹‹ማለት?›› በማለት መጠየቅ። ‹‹በቀደመው ሥርዓት ደርግ ‘ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!’ ካለ በኋላ አገሪቷን በደም እያጠበ ከመርሁ ጋር ሲጋጭ ኖሮ አለፈ። እነሆ በኋላ ደግሞ ኢሕአዴግ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ’ ብሎ ዴሞክራሲ አለ ብለን ያሻንን ስንናገር ፀረ ልማት፣ ፀረ ሰላም ብሎ ሲፈርጀን ኖረ። በቃ ስሙ ተቀይሮ ‘ልማት’ ተባለ እንጂ አብዮት ውስጥ ነበርን ስንል ሐሳብን በነፃነት ስለመግለጽ፣ ስለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፣ ስለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እያወራን ያደረገንን ታውቃለህ። አንተም ተምታቶ የሚያምታታ ነገር አያጥቃህ የምልህ ለዚህ ነው፤›› ስትለኝ እውነት ማንጠግቦሽ አልመስልህ ብላኝ ፈዝዤ አየኋት፡፡ ‹‹ግለሰብና መንግሥትን እያነፃፀሩ የሆድን መዘርገፍ ተጀመረ እንዴ?›› ብዬ ከት ብዬ ስቄባት ሳበቃ፣ ‹‹በይ እኔ እንደ ሰማሁሽ ሌላ ሰው እንዳይሰማሽ አደራ፤›› ብያት ወጥቼ ሄድኩ። በቃ የዛሬ ሰው እንዲህ አልጨበጥ ይበል? ‹‹ይኼ ከምኑም የለበት ወሬ ብቻ›› ስትሉት ቁም ነገረኛ፣ ባለጌ ስትሉት ጨዋ፣ አፍራሽ ስትሉት ገንቢ ሆኖ ይገኛል። ከጓዳ ሕይወቷና ከሥራዋ ባሻገርም ምንም የምታውቀው የማትመስለኝ ውዷ ማንጠግቦሽም ደንበኛ የፖለቲካ ተንታኝ ሆና አረፈች። ለነገሩ ተምረናል እያሉ ቁምነገር የሌለው ነገር በቴሌቪዥን ከሚዘበዝቡብን የማንጠግቦሽና መሰሎች ቀና ንግግር ይበልጣል፡፡ በትንተና ስም  ከሚያዝጉን ቀናዎች ሲገስፁን ብናዳምጥ ከስንትና ስንት ስህተቶች በፀዳን!   

መቼም ሮጬ ሄጄ የማወራው ለእሱ ስለሆነ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ አግኝቼ የማንጠግቦሽን ትንተና ብነግረው፣ ‹‹እውነቷን እኮ ነው!›› ብሎኝ የሚሉት ሌላ የሚሠሩት ሌላ ስለሆነባቸው ተጨዋወትን። በኋላም ‹‹ኔጋቲቭ›› እና ‹‹ፖቨቲቭ›› የሚሉ ቃላትን በስሙ ስላስቀየራቸው ንጉሥ የባሻዬ ልጅ የሚያስቅ ነገር አጫወተኝ፡፡ እኔም ‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ›› እያልኩ ሰማሁት፡፡ ሆሊውድ አምባገነኖች ምን ያህል ራስ ወዳድና ህሊና ቢስ ገዥዎች እንደሆኑ ለማሳየት ፈልጎ ከሠራው ፊልም ያየው መሆኑን ጠቅሶ የባሻዬ ልጅ ጨዋታውን ቀጥሏል። ‹‹የንጉሡ ስም አላዲን ይባለል። ሁሉም ነገር በእርሱ ስም እንዲቀየር ከማዘዙ የተነሳ ‘ኔጌቲቭ’ እና ‘ፖዘቲቭ’ በስሙ ተዛውረዋል። ታዲያ የኤችአይቪ ምርመራ ውጤት ያደረገ ሰው ውጤቱ የሚነገረው ‘ኤችአይቪ አላዲን’ ወይም ‘ፖዘቲቭ አላዲን’ ተብሎ ነው። ይታይህ እንግዲህ፤›› አለኝ ፈገግ ብሎ። ጨዋታችን በምድራችን ላይ የተነሱ አምባገነንና ጨካኝ መሪዎችን አስታወሰኝ። ከማናለብኝ ስሜታቸው የተነሳ የሰው መብት የደፈሩ ስማቸው በታሪክ መዝገብ ላይ ጎድፎ ተጽፎ ትውልድ ሲሳለቅባቸው የሚኖሩ በአዕምሮዬ ተዘረዘሩ። ብልህ መሪና መንግሥት ግን በታሪክ ተወቃሽ መሆንን ስለማይሻ ከልብ ለሕዝብ መሥራትና መቆርቆር መገለጫ ባህሪው ነው፡፡ የታሪክ ጥላሸት ራሳቸውን ለመቀባት የሚጣደፉ ያልበሰሉት ደግሞ ሁሉም ነገር በእነሱ ፈቃድ የሚከናወን እየመሰላቸው፣ የሁሉም ነገር ስትራቴጂስት ነን እያሉ ሲመፃደቁ ማየት ያቅለሸልሻል፡፡ ባልበሰለ ጭንቅላትና በግትርነት የሚመራ ፖለቲካ ሲዘባርቅ መጀመርያ የሚያጠፋው ባለቤቱን እንደሆነ ታሪክ ከመጠን በላይ አስተምሮናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተግባር የሚረጋገጥ ስለሆነ ጊዜን መጠበቅ ደግ ነው!   

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ቅዝቃዜው ሲጠናብን እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን አመራን። ግሮሰሪያችን ከወትሮ የተለየ ድባብ አይታይባትም። ሳቅ፣ ጨዋታና ብሽሽቁ እንደተለመደው አለ። እንደ ወትሮው ያልነበረው የባሻዬ ልጅ ነው። ድንገት ተለውጧል። ‹‹ምነው? ምንሆነሃል?›› አልኩት ከፍቶት እያየሁት። ‹‹እንዲያው ዝም ብዬ ነው እባክህ ብቻዬን የምፈጥረው ነገር ያለ ይመስል፤›› አለኝ። ‹‹በእርግጥ መፍጠር የፈጣሪ ተግባር ነው። ልዩነት ማምጣት ግን መቻሉን አትርሳ፤›› አልኩት ትከሻውን ቸብ እያደረግኩ። አሁንም ዝምታው ቀጠለ። ‹‹ኤጭ ትነግረኝ እንደሆነ ንገረኝ። ለጨዋታ እንጂ የሚያስቆዝምማ መቼ ጠፋ?›› ስለው ደንገጥ ብሎ፣ ‹‹አንዳንዴ ለራሴም ጭምር ስለሚገርመኝ እኮ ነው፤›› አለኝ በተጨነቀ ድምፅ። ‹‹ምኑ?›› ጠየቅኩት መልሼ። ‹‹የዚህች አገር እንቆቅልሽ ነዋ! ሌላ ምን አለብን አንበርብር?›› ብሎ መልሶ ጠየቀኝ። ‹‹ምነው የሰማኸው አዲስ ነገር አለ እንዴ?›› ስለው፣ ‹‹አዲስ ነገር ባንሰማስ ያልፈታነው ችግር ተጠራቅሞ አለ አይደል እንዴ?›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹ዝም ብዬ ስታዘብ ወዴት ይሆን እየተጓዝን ያለነው ስል መሽቶ ይነጋል። ተመልከት እስኪ ተማሪው ለዕውቀት ሳይሆን ወረቀት ለመያዝ ይማራል፣ አልጠግብ ባይ ነጋዴው ከዚህም ከዚያም ያምታታል፣ አማኙ ‘ከእኔ ሌላ የለም!’ የሚል ጽንፈኝነት አጥቅቶታል። በዚህ በኩል ሌብነቱ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የፀጥታ ሥጋቱን ታየዋለህ። ለአገር የማያስበው ለራሱ ጎርሶ ራሱን ሊያድን ብቻ እየሮጠ የአገር ችግር የሚፈታ ጠፋ። እውነት ማነው ከራሱ አስቀድሞ የዚህችን አገር ጥቅም እያስቀደመ ያለው? እንጃ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ይመስለኛል፤›› ብሎኝ ካስቀዳው ተጎነጨ።

‹‹አንተ ምን ይሁን ትላለህ?›› አለው ፊት ለፊታችን ተቀምጦ የምናወራውን ሲሰማ የነበረ ጎልማሳ። የባሻዬ ልጅ ከአንገቱ ቀና ብሎ ድምፁን ጎርነን አድርጎ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም!›› ብሎ ሲመልስ የግሮሰሪዋ ታዳሚዎች በሙሉ ቀና ብለው አዩት። ጠያቂው ብርጭቆውን አንስቶ፣ ‹‹ከራስ ጥቅም በፊት ለአገር!›› አለው ፈገግ ብሎ። ድራማ የማይ እስኪመስለኝ የምሰማውንም ሆነ የምመለከተውን ማመን አልቻልኩም። ሁሉም የሚጎነጨውን አንስቶ በአንድ ድምፅ መፈክር ያወርዳል፡፡ ከራስ ወዳድነት እስከ ጽንፈኝነት የመረረው ሁሉ ወደ ኋላው እያየ ነገን የናፈቀ ይመስላል፡፡ ራስ ወዳድነትና ቡድንተኝነት ፋሽን በሆነበት በዚህ ዘመን ጠያቂና መርማሪ ትውልድ ካልተፈጠረ ነገም ያስፈራል፡፡ ለዚህም ይመስላል ከራስ በፊት ለአገር የሚለው የግሮሰሪዋን ሰዎች ቺርስ የሚያስብለው፡፡ ‹‹ከራስ ወዳድነት እስከ ጽንፈኝነት ድረስ ያሉት በሽታዎች ይወገዱ ዘንድ አሁንም ቺርስ!›› የሚል መፈክር የሰማሁ መሰለኝ፡፡ በሰመመን ውስጥ ሆኜ ከአገር በላይ ምን ይኖር ይሆን ስል፣ ‹‹ምንም!›› የሚል መልስ ይሰማኛል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ሲባል የሚያንገሸግሻቸው ምን ሆነው ይሆን ስል ‹‹ልክፍት!›› የሚል መልስ ይደርሰኛል፡፡ አለመለከፍ ነው! አንዳንዶችማ እንደ ዶናልድ ትራምፕ ማርሽ ተቀላቅሎባቸዋል፡፡ እግዜር ሳይጣላ አይደግስምና ኢትዮጵያን የሚያስከብሩ ብዙ ጀግኖች አሉ፡፡ ስሟን አስጠርተው ያኮሩን ብዙ ናቸው፡፡ ፈጣሪ ያክብራቸው፡፡ እኛም ደስ ይበለን እንጂ! ኩርት ብለናል! መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት