Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሕገ መንግሥቱ ለሴቶችና ለሕፃናት የዴሞክራሲ መብቶች የተባሉት የሰብዓዊ መብቶች እንዲባሉ ሐሳብ ቀረበ

በሕገ መንግሥቱ ለሴቶችና ለሕፃናት የዴሞክራሲ መብቶች የተባሉት የሰብዓዊ መብቶች እንዲባሉ ሐሳብ ቀረበ

ቀን:

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 35 (የሴቶች) እና አንቀጽ 36 (የሕፃናት) መብቶች ‹‹የዴሞክራሲ መብቶች›› መባላቸው ትክክል ስላልሆነ፣ ‹‹የሰብዓዊ መብቶች›› መባል እንዳለባቸው ሐሳብ ቀረበ፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1948 ጀምሮ በመከበር ላይ የሚገኘውንና በዚህ ዓመት እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 10 ቀን 2019 ለ71ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ቀንን አስመልክቶ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የተሳተፉት ተማሪዎች ናቸው፡፡

ከዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤትና ከሌሎቹም ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ400 በላይ ተማሪዎች በፍርድ ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው የነበረ ሲሆን፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ወ/ሮ ፀሐይ መንክር የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሑፍ ከቀረበላቸው በኋላ ተማሪዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ተማሪዎቹ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል በሕገ መንግሥቱ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ መብቶች›› ተብለው ከአንቀጽ 29 እስከ አንቀጽ 44 ድረስ ተደንግገው ቢገኙም፣ አንቀጽ 35 (የሴቶች መብት) እና አንቀጽ 36 (የሕፃናት መብት) መካተታቸው ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው፣ ሴትነትና ሕፃንነት በተፈጥሮ የተገኙ ፀጋዎች እንጂ፣ በዴሞክራሲ የተገኙ አይደሉም፡፡ የዴሞክራሲ መብቶች ከተባሉ በሰው የሚሰጡና ሊከለከሉ የሚችሉ ስለሚሆኑ ትክክል አይደለም፡፡ በመሆኑም የሰብዓዊ መብቶች ተብለው መስተካከል አለባቸው ብለዋል፡፡ በሌሎች አገሮች መስማት የተሳናቸው ዜጎች መኪና እንዲያሽከረክሩ ስለሚፈቀድላቸው በኢትዮጵያ ለምን አይፈቅድም? እንዲሁም ሐኪም ለመሆን ችሎታና ፍላጎት ቢኖራቸውም እንደማይፈቀድላቸውና ይኼ የማይሆነው ለምን እንደሆነ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

ተምሮ ሥራ በማጣትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ የሌለው ሰውን ‹‹አደገኛ ቦዘኔ›› የሚያስብል አዋጅ መውጣቱን ጠቁመው፣ መንግሥት የሥራ ዕድል ባላመቻቸበት ሁኔታ ሥራ የሌለው ሰው እንዴት ወንጀለኛ ሊባል እንደሚችልም እንዲገለጽላቸው ጠይቀዋል፡፡ ስለሰብዓዊ መብቶች በዓመት አንድ ቀን ብቻ ከመንገር በትምህርት ቤት ከታች ጀምሮ ቢሰጥ፣ ለአካል ጉዳተኞች የተለያዩ ዕድሎች ቢመቻቹ፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ማየት ለተሳናቸውና መስማት ለማይችሉ ተማሪዎች በየትምህርት ዓይነቱ ብቃት ያላቸው አስተርጓሚዎችና መጻሕፍት ቢዘጋጁ፣ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ያሉ ሴቶች ጥቃት ሲደርስባቸው ፖሊሶችና ፍርድ ቤቶች በማድበስበስ በዳዩ አካል ተገቢ ቅጣት እንዳያገኝ የሚደረግበት ሁኔታ ቢታሰብበት የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

‹‹ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የፍርድ ቤቶችና የተማሪዎች (ወጣቶች)›› በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ወ/ሮ ፀሐይ እንዳብራሩት፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱት ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሕግን መሠረት ያደረገ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቶቹ የሕዝብን አመኔታ ያተረፉ መሆን እንዳለባቸውና እኩልነት፣ ነፃነት፣ ገለልተኝነት፣ ታማኝነት፣ ሀቀኝነት፣ ሚስጥራዊነት፣ ቀጠሮ አክባሪነት፣ ራስን ማብቃትና ለለውጥ ዝግጁ መሆን የፍርድ ቤቶች እሴቶች መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ተቀብላ ያፀደቀችና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 (4) የአገሪቱ የሕግ አካል ማድረጓንም አክለዋል፡፡ ሰፋ ባለና በዝርዝር ስለሰብዓዊ መብቶች አገራዊና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማካተት ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ወ/ሮ ፀሐይ፣ የጽሑፉን ዓላማም ጠቁመዋል፡፡ ተማሪዎች ስለሰብዓዊ መብት ምንነት፣ ስለፍርድ ቤቶች ሥልጣንና ኃላፊነት ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ፣ ግዴታቸውንና መብታቸውን አውቀው ለሕግ ተገዥ፣ ሕግን የሚያከብሩ፣ በሥነ ምግባር የታነፁ፣ ለሕግ የበላይነት መረዳት ያላቸው ተማሪዎችን ማፍራት የጽሑፉ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ ከተማሪዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፣ መስማት የተሳናቸውና ማየት የማይችሉ ተማሪዎች ያነሱት ጥያቄ መመለስ ያለበት በትምህርት ሚኒስቴር በመሆኑ፣ ጥያቄውን አቅርበው ምላሻቸውን በየትምህርት ቤቶቻቸው እንደሚያደርሱ ገልጸዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተነሱ ጥያቄዎችን አድንቀውና የሚደግፉት መሆኑንም ጠቁመው፣ ለሰብዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) አቅርበው ምላሹን እንደሚሰጡም ወ/ሮ መዓዛ አስረድተዋል፡፡

መስማት የተሳናቸው መኪና ማሽከርከርና በሚፈልጉት የሕክምና ዘርፍ መማር ለምን እንደማይችሉ የሚመለከተውን አካል አነጋግረው ምላሽ እንደሚሰጧቸው ጠቁመው፣ ተደፍረው በቤት ውስጥ እንዲቀሩ ስለሚደረጉ ሴቶች ግን እነሱም ተደራጅተው መታገልና አደባባይ በመውጣት ማጋለጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ተማሪዎቹ ከዘጠኝ እስከ 15 ዓመታት ያሉ ሕፃናት ለምን እንደሚታሰሩ የጠየቁትን ወ/ሮ ፀሐይ ሲመልሱ፣ ከዘጠኝ እስከ 15 ዓመታት ያሉ ሕፃናት ጥፋተኞች አይታሰሩም ብለዋል፡፡ በቤተሰቦቻቸው ዋስትና ውጭ ሆነው ጉዳያቸውን ይከታተላሉ ሲሉም አክለዋል፡፡ የጎዳና ተዳዳሪ ወጣት ጥፋተኞች ከሆኑ በተሃድሶ ተቋም ገብተው እንዲቆዩ ይደረጋል እንጂ፣ ከአዋቂ ጥፋተኛ ጋር እንደማይታሰሩም አክለዋል፡፡ ከ15 እስከ 18 ዓመት ያሉ ግን በአግባቡ ታስረው ጉዳያቸው እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ የአደገኛ ‹‹ቦዘኔ›› ሕግ የወጣው ሥራ የሌላቸውን ለማሰር ሳይሆን በየመንደሩ የተጫነ ዕቃ፣ ‹‹ከእኛ ውጪ ማንም አያወርድም፤›› እና ሌሎች የጉልበተኝነት ድርጊት በሚፈጽሙ ላይ የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለሚጠቁ ሴቶች ፖሊሶች ከለላ አይሰጡም ተብሎ የቀረበው ጥያቄ እውነት መሆኑን አረጋግጠው፣ ፖሊስ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡም መደበቅና መከላከል እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን መሻሻልና በተለይ ሕግ የተማረ ፖሊስ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ ማንንም ዝም ብሎ ለምን እንደሚደበድብ ለተነሳው ጥያቄ፣ ፖሊስ ማንንም የመደብደብ ሥልጣን እንደሌለውና ነገር ግን ተጠርጣሪ አስቸጋሪ ከሆነ ብቻ ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድ ሕግ እንደሚፈቅድ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስም በፈጸመው ጥፋት እንደሚቀጣ አክለዋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...