በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የከተማ አስተዳደሩ የቁጠባ ቤቶች ግንባታ ልማት ኢንተርፕራይዝ እያስገነባቸው ያሉ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ሊዘርፉ በነበሩ ግለሰቦች፣ ጥቃት የደረሰባቸው የጥበቃ ሠራተኛ ሕይወታቸው አለፈ፡፡ ፖሊስ ሁለት ተጠርጣሪዎችን ይዞ በምርመራ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ረቡዕ ታኅሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ሌሊት ቁጥራቸው 30 የሚሆኑ ግለሰቦች ተሽከርካሪ ይዘው ረድኤት ዳግም ኢንጅነሪንግ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ከኢንትርፕራይዙ ኮንትራት ወስዶ እየገነባው ባለው 160 አባወራዎችን በሚይዘውና ባለ 15 ፎቅ በሆነው ሁለት ብሎክ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመዝረፍ መምጣታቸውን፣ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳግማዊ ፋሲል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በውድቅት ሌሊት ለዝርፊያ የመጡት ግለሰቦች በዕለቱ በጥበቃ ላይ በነበሩት አቶ ሹመት ተገኝ የተባሉ የማኅበሩ ሠራተኛ ላይ ከባድ የድብደባ ጥቃት አድርሰውባቸው ለሕክምና ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል የገቡ ቢሆንም፣ ሐሙስ ታኅሳስ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ሌሊት ሕይወታቸው ማለፉን አስረድተዋል፡፡
የኤልኤች ሴኩዩሪቲ ኤጀንሲ የጥበቃ አባል የነበሩት ሟች የጥበቃ ሠራተኛ፣ በድንጋይና በብረት መደብደባቸውንም አክለዋል፡፡ ለዝርፊያ መጥተው የነበሩ ግለሰቦችን ሌሎች በአጎራባች የነበሩ የጥበቃ ሠራተኞች ጭምር ተረባርበው ያሰቡትን ዘረፋ ሳይፈጽሙ እንዳባረሯቸው፣ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በተወሰኑት የጥበቃ ሠራተኞች ላይ ጉዳት በመድረሱ፣ ሆስፒታል መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩንም የቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 ፖሊስ ጣቢያ እያጣራው መሆኑን አክለዋል፡፡
በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚገኘው የቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ ሳጅን እመቤት ታምራት ስለወንጀል ድርጊቱ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ወንጀሉ መፈጸሙን አረጋግጠዋል፡፡ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው የጥበቃ ሠራተኛ አቶ ሹመት ተገኝም ሕይወት ታኅሳስ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ሌሊት ስምንት ሰዓት አልፏል ብለዋል፡፡ ሁለት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ መሆናቸውንና ንብረት እንዳልተዘረፈ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው የጥበቃ ሠራተኞች የነበሩ ቢሆንም፣ ጉዳታቸው መጠነኛ በመሆኑ ሕክምና ተደርጎላቸው ከሆስፒታል መውጣታቸውን ሳጅን እመቤት አስረድተዋል፡፡