Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሳንሱር እያደረጋቸው መሆኑን ጠበቆች ተናገሩ

የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሳንሱር እያደረጋቸው መሆኑን ጠበቆች ተናገሩ

ቀን:

በሰኔ 15 ግድያ የተከሰሱ በኤግዚቢት በተያዘ ንብረታቸው ወንጀል እየተሠራባቸው መሆኑ ገለጹ

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 (3ሀ) የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) በማንኛውም መልኩ መከልከሉን ደንግጎ እያለ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ድንጋጌውን በመጣስ፣ በደንበኞቻቸውና በእነሱ መካከል ብቻ ሚስጥር ሆኖ መጠበቅ ያለበት የሰነድ ማስረጃ ላይ ምርመራ እያደረገባቸው መሆኑን ጠበቆች ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

የማረሚያ ቤቶቹ ድርጊት የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የጣሰ በመሆኑ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አቤቱታ ያቀረቡት፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማና በአዲስ አበባ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው 13 ተከሳሾች ጠበቆች ናቸው፡፡

ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በደንበኞቻቸውና በእነሱ መካከል መጠበቅ ያለበትን ሚስጥር እያዩና ሳንሱር እያደረጉ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ በመሆኑ፣ ሊከለከል ስለሚገባ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሾቹ አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ አቶ አስጠራው ከበደ፣ አቶ ሲሳይ አልታሰብ፣ አቶ አበበ ፈንታ፣ አቶ አስቻለው ወርቁ፣ አቶ ተሾመ መለሰ፣ አቶ ዓለምኔ ሙሉ፣ አቶ ከድር ሰዒድ፣ አቶ አየለ አስማረ፣ አቶ አማረ ካሴ፣ አቶ ፈንታሁን ሞላ፣ አቶ ክርስቲያን ታደለና አቶ በለጠ ካሳ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ክስ ላይ የቅድመ ክስ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል፡፡

ተከሳሾቹ መቃወሚያቸውን በጽሑፍ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ችሎት ካቀረቡ በኋላ፣ አቤቱታ እንዳላቸው ጠይቀው ሲፈቀድላቸው አቤቱታውን አሰምተዋል፡፡

ክስ በተመሠረተባቸው ዕለት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏቸው ምርመራውን መጨረሱንና የምርመራ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን በመግለጽ፣ በማስረጃነት ያላካተታቸው፣ ነገር ግን በኤግዚቢትነት ተይዘው የሚገኙ ንብረቶቻቸው ለቤተሰቦቻቸው ተመላሽ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውን አስታውሰዋል፡፡

ፖሊስ ያለ ምንም ምክንያት ንብረታቸውን መያዙንና ለፍርድ ቤትም ቢያመለክቱም መፍትሔ እንዳላገኙ፣ በጊዜ ቀጠሮ ላይ እያሉ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎትና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም እንዲመለስ ትዕዛዝ የሰጡ ቢሆንም፣ ትዕዛዙ ተግባራዊ ሊደረግላቸው እንዳልቻለ በአቤቱታቸው አስረድተዋል፡፡ አንዳንድ ንብረቶቻቸው በምርመራ መዝገብ ላይ የተመዘገቡ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹን ንብረቶች ግን ፖሊስ ያለ ደረሰኝ የወሰዳቸው በመሆኑ ‹‹ቢጠፉ ተጠያቂ የምናደርገው ማንን ነው?›› በማለትም ጠይቀዋል፡፡ በብርበራ ወቅት የሚወሰዱ ንብረቶች ተቆጥረውና ዓይነታቸው ጭምር ተገልጾ መረከቢያ ሰነድ ለተጠርጣሪ መስጠት ቢኖርበትም፣ ባለመደረጉ ሊጠፉ ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ከእነሱ ወስዶ ፖሊስ  ባቀረበለት ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ላይ ምንም የሚፈልገው መረጃ እንደሌለ ገልጾ የመለሰላቸው ቢሆንም፣ ለቤተሰቦቻቸው መመለስ ሲገባ ወንጀል እየተሠራባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ እንዲመለሱላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁ የሰጠውን ብይን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሕግ አግባብ ውጪ ብይኑን በማገድ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ከሚፈቅደው 28 የምርመራ ቀናት በላይ 48 ቀናት የፈቀደ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ሕገወጥ ትዕዛዝ በማገድ አከራክሮ ወይም መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥ ቢመልሰውም፣ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ባለመቀበል ከሕግ ውጪ አስረው በማቆየት ክስ እንደመሠረቱባቸው አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸው ክስ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1 ሀ እና ለ)፣ 38 እና 238 (2) ድንጋጌን በመተላለፍ ሆኖ ሳለ፣ ማረሚያ ቤቱ ግን የተረከባቸው የሽብር ተግባር ተከሳሾች አድርጎ በመሆኑ፣ ሊስተካከልና ሊታረምላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ተከሳሾቹ ጨምረው እንዳስረዱት፣ የታሰሩት ፖለቲከኛ በመሆናቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ነው፡፡ በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ እስካልተባሉ ድረስ ንፁህ ሆነው የመገመት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ተከሳሾች የሚያገኙትን መብት ሊያገኙ ሲገባቸው ሻይ፣ ቡናና መጻሕፍት መከልከላቸውንና ቤተሰብ በአግባቡ እንዳይጠይቃቸው መደረጉን በማስረዳት፣ በሕግ ከተከለከሉ መጽሐፍት በስተቀር ሌሎች መጻሕፍት እንዲገቡላቸውና ሌሎች የጠየቋቸው እንዲፈቀዱላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

ጤናን በሚመለከት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን በመግደል የተጠረጠረው አሥር አለቃ መሳፍንትና የአብን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ጠበቆች አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ በልዩ ጥበቃ ውስጥ የነበረው አሥር አለቃ መሳፍንት ወደ ማረሚያ ቤት የተዛወረ ቢሆንም፣ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል በመከታተል ላይ የነበረው ሕክምና እንደተቋረጠበት ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡ ከአንገት በላይ ከባድ ሕመም ስላለበት የተቋረጠው ሕክምና እንዲቀጥልለትና አንድ እግሩ ወደ ሽባነት እየሄደ ስለሆነ፣ እንዲታከም ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቀዋል፡፡ አቶ ክርስቲያንም በአለርት ሆስፒታል እየተከታተለው ያለ የቆዳ ሕክምና እንደተቋረጠበትና ማረሚያ ቤቱን ሲጠይቅ ለመፍቀድ በኮሚቴ ስለሚወሰን፣ ሕክምና ሊያገኝ ባለመቻሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠበቆቹ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሌላም ተከሳሽ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን አቤቱታ ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ተከሳሾች የተከሰሱት በሽብርተኝነት ባለመሆኑና በሕክምና፣ በምግብና በቤተሰብ ጉዳይ ያቀረቡትን ጥያቄ ማረሚያ ቤቱ አርሞ ተግባራዊ እንዲያደርግ ብሏል፡፡ መጻሕፍትን በሚመለከትና ባቀረቡት የክስ መቃወሚ ላይ ብይን ለመስጠት ለታኅሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...