Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን ከማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለማውጣት አይኤምኤፍ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የታቀደው ኢኮኖሚ ሪፎርም የዕድገት ምጣኔን በጊዜያዊነት ሊያቀዛቅዝ እንደሚችል አይኤምኤፍ ጠቁሟል

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ኢትዮጵያን ከገጠማት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለማውጣት የ2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ስምምነት መፈረሙን፣ ስምምነቱም ለቦርድ ቀርቦ ውሳኔ እንደሚሰጥበት አስታወቀ፡፡

የአይኤምኤፍ ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ሶናሊ ጄን ቻንድራ የተመራ የባለሙያዎች ቡድን እ.ኤ.አ. ከኦክቶበር 29 እስከ ኖቬምበር 8 ቀን 2019 ድረስ በነበረው የአዲስ አበባ ቆይታ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የገመገመ ሲሆን፣ በግምገማው ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የደረሰበትን ስምምነት የተመለከተ መግለጫ ረቡዕ ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አውጥቷል፡፡

በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታውም የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የጀመሩትን የኢኮኖሚ ሪፎርም አይኤምኤፍ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንዲያግዝ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ በእሳቸው የተመራው ቡድንም ከመንግሥት ኃላፊዎቹ ጋር በመምከር የቀረበውን የ2.9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ጥያቄ ተቀብሎ ቅድመ ስምምነት ማድረጋቸውን ሚስ ሶናሊ አስረድተዋል፡፡

የተደረገው ቅድመ ስምምነት ለአይኤምኤፍ ቦርድ ቀርቦ ውሳኔ የሚያገኝ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የጠየቁት የገንዘብ ድጋፍ በአይኤምኤፍ የብድርና የድጋፍ ፖሊሲ አካል በሆኑት፣ ኤክሰቴንድድ ክሬዲት ፋሲሊቲ (ECF) እና ኤክስቴንድድ ፈንድ ፋሲሊቲ (EFF) መሠረት ውሳኔ እንደሚያገኝ አስታውቀዋል፡፡

የአይኤምኤፍ የብድር ፖሊሲ እንደሚያስረዳው የፖሊሲው አንዱ ማበደሪያ ሥልት የሆነው ኤክስቴንድድ ፈንድ ፋሲሊቲ (EFF)፣ በኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮች ሳቢያ ከፍተኛ የክፍያ ሚዛን መዛባት ለገጠመው በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኝ አገር ከችግር ለመውጣት ጊዜ የሚጠይቅ ሲሆን የሚሰጥ የብድር ዓይነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ድጋፍ ጥያቄዋን ለማቅረብ የጠቆመችው ኤክስቴንድድ ክሬዲት ፋሲሊቲ (ECF) የተባለው ሌላኛው የማበደሪያ ሥልትም፣ በተመሳሳይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና የተራዘመ የክፍያ ሚዛን መዛባት ውስጥ የሚገኙ አገሮች ሪፎርም በማድረግ ወደ ተረጋጋና ዘላቂ የኢኮኖሚ መዋቅር እንዲሸጋገሩ ድጋፍ የሚያደርግበት መንገድ ነው፡፡

ይህ የአይኤምኤፍ የብድር ፖሊሲ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ አገሮች የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን ተረጋግተው እንዲወስዱ የመተንፈሻ ጊዜ የሚሰጥ እንደሆነም የራሱ መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ አገር በሁለቱም የማበደሪያ ሥልቶች ከተቋሙ ሊበደር ሲጠይቅ፣ ተቋሙ የሚያቀርባቸውን የፖሊሲ ማስተካከያ ምክረ ሐሳቦችን ተቀብሎ መተግበር እንደሚኖርበትና ትግበራው ላይም ክትትል እንደሚደረግበት የብድር ፖሊሲ መረጃው ያመለክታል፡፡

የገንዘብ ተቋሙ ባለሙያዎች ቡድን ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ባደረገው ቅድመ ስምምነት መሠረት የሚሰጠው 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር፣ አምስት ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት ትኩረት እንደሚያደርግ የተቋሙ መግለጫ ያመለክታል፡፡

ከእነዚህም መካከል የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታትና የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ ወደ የሚወሰንበት ለማሸጋገር፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን የአገር ውስጥና የውጭ ብድር ለመቆጣጠርና ከብድር ጋር የተያያዙ ቀውሶችን ለመፍታት፣ የአገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ፣ የአገር ውስጥ የገንዘብ ተቋማት ላይ ሪፎርም በማድረግ የግሉን ዘርፍ እንዲደግፉ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የገንዘብ ተቋሙ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ኢኮኖሚውንና የመንግሥትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የፈተሹበትን የተጨመቀ ሰነድ ሪፖርተር አግኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ የብድር ጫና፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በግብርና ምርታማነት መቀነስና በከፍተኛ የትራንስፖርት ዋጋ መናር፣ እንዲሁም ከፀጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ የዋጋ ንረት አገሪቱ እየተፈተነች መሆኑን ያመለክታል፡፡

የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ የ1.8 ወር የገቢ ዕቃዎችን የሚሸፍን ብቻ እንደሆነና በዚህም ምክንያት የገቢ ንግድ መቀነሱን፣ በተመሳሳይም የወጪ ንግድ ከዓመታት ወዲህ በማሽቆልቆል ላይ መሆኑን ያስረዳል፡፡

መንግሥት የአገሪቱ ኢኮኖሚ መዛባትን ማስተካከልና ችግሮችን ለመቅረፍ በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚ እንዲኖር ማቀዱን እንደተገነዘቡና የታቀደው ሪፎርም በጎ እንደሆነ በሰነዱ አውስተዋል፡፡ ነገር ግን የኢኮኖሚ መዛባት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚወሰዱት ዕርምጃዎች፣ ማለትም የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲወሰን ለማድረግ የተያዘው ፕሮግራም የዋጋ ንረትን እንዳያስከትል ሥጋት እንዳለ፣ እንዲሁም የገንዘብና የበጀት ፖሊሲውን ለማጥበቅ የተያዘው ዕቅድ አገሪቱ ከገጠማት ከፍተኛ የዕዳ ጫና፣ እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያዘውን የውጭ ክፍያ ሚዛን ለማስተካከል ተገቢ ሆኖ ሳለ፣ ወደ ግል ዘርፉ ሽግግር ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ የብድር አቅርቦትን በማሳጣት ዕክል እንዳይሆን በተነሳው ሥጋት ተካቷል፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ያቀደው የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲውን ለማጥበቅ፣ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ላይ ሪፎርም በማካሄድ አዲስ ብድር እንዳይወስዱና ፕሮጀክት እንዳይጀምሩ ማድረግና የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም በተለይም በመንግሥት በተያዙት ላይ ማካሄድ መሆናውን መረጃው ያመለክታል፡፡

ወደ ግሉ ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑና በሪፎርሙ ጥብቅ የገንዘብና የበጀት ፖሊሲ ለመከተል መታቀዱ በጎ ቢሆንም፣ በሽግግር ሒደቱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ዝቅ እንደሚል በሰነዱ ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች