Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና 70ኛው የፊፋ ጉባዔ በአዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና 70ኛው የፊፋ ጉባዔ በአዲስ አበባ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2012 ዓመታዊ መርሐ ግብር ተጀምሯል፡፡ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ጋር ተያይዞ በማዘውተሪያዎች አካባቢ ይስተዋሉ የነበሩ አለመግባባቶችና ሁከቶች እስካሁን ባለው በሁሉም ከተሞች ጨዋታዎች ስፖርታዊ ጨዋነት ሰፍኖባቸዋል፡፡ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ሳይቀር “በያገባኛል” ስሜት ዘርፉ የሰላም ማዕከል ሆኖ እንዲቀጠል በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሊጉና በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ክለቦች ሊጉን በራሳቸው ማስተዳደር ይችሉ ዘንድ ዓብይ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማድረግ ውድድሩን እንዲያስተዳድሩ አድርጓል፡፡ ይህ ማለት ክለቦች የስታዲየም መግቢያ ትኬት፣ የፀጥታ አካላት፣ የአምቡላንስ አገልግሎት፣ የዳኞችና የኮሚሽነሮች ምደባና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን በኃላፊነት ተረክበዋል፡፡ ይሁንና በፌዴሬሽኑና በክለቦች መካከል አሠራሮችን ተከትሎ አሁንም የሚደመጡ ቅሬታዎችና አለመግባባቶች መከሰታቸው አልቀረም፡፡      

የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ፊፋ) በመጪው ሰኔ ወር 70ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን በኢትዮጵያ እንደሚያከናውን ይጠበቃል፡፡ በአዲስ አበባ የሚደረገውን ጉባዔ አስመልክቶ፣ የፊፋ ዋና ጸሐፊ ፋትማ ሳሙራና የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ የአንድ ቀን ቆይታ አድርገው ከርዕሰ ብሔሯ ሳህለወርቅ ዘውዴ ጀምሮ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይቱ በዋናነት በኢትዮጵያ ሲከሰቱ የቆዩ ብሔር ተኮር ግጭቶች ለጉባዔው ሥጋት መሆኑ ስለማይቀር መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥና ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ ለመጠየቅ መሆኑ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ፊፋ በአዲስ አበባ ለማካሄድ በዕቅድ ይዞ የቆየውን ይህን ጉዳይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ጉባዔውን ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሊያዞር ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው ወገኖችም አልጠፉም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምን ይላል፣ ደረጀ ጠገናው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከወትሮ በተለየ በራሱ ሕንፃ የዕለት ዕለት ዕቅዶቹን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ይሁንና ከሠለጠነ የሰው ኃይል አደረጃጀት ጋር አሁንም ክፍተት እንዳለበት የሚናገሩ አሉ፡፡

አቶ ኢሳያስ፡- ተቋሙ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማሟላት ጥረት እያደረገ ነው፣ በሚፈለገው ልክ እየሄደ ነወይ በጣም ገና ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ቀደም ሲል በሦስት ቦታ ተከፋፍሎ የነበረው የተቋሙ ሠራተኛ ወደ አንድ ማዕከል ማምጣት ተችሏል፡፡ ይህ ሁሉም ሰው ሥራው ላይ መሆን አለመሆኑ ታውቆ ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ የተቋሙን አደረጃጀትና የሰው ኃይሉን በሚመለከት ቀደም ሲል የተጠኑ ጥናቶች አሉ፡፡ ያንን መነሻ በማድረግ የማስተካከያ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ተቋሙ ሁሉም እንደሚያውቀው ሲንከባለሉ በመጡ ውስብስብ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ ፕሮፌሽናሎችን በተፈለገው ጊዜ ለማሟላት አልተቻለም፣ እንዲያም ሆኖ ግን በተወሰነ መልኩ ውሳኔ የሚሹ ዲፓርትመንቶች በበቁ ሙያተኞች እንዲሟሉ ተደርጓል፣ እየተደረገም ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል የአደረጃጀትም ሆነ የሰው ኃይል ጥያቄ ሲነሳ ቀድሞ የፋይናንስ ችግር በቀዳሚነት ይቀርብ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ተቋሙ በራሱ ሕንፃ የዕለት ዕለት ተግባሩን እየከወነ ነው፤ በዚያ ላይ ሕንፃው በከፊል ለኪራይ አገልግሎት ውሎ ተጨማሪ የፋይናንስ ገቢ እያመነጨ መሆኑ ይነገራል፡፡ ፋይናንስ ካለ ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት ለምን አልተቻለም?

አቶ ኢሳያስ፡- ፌዴሬሽኑ ሕንፃውን ከመገዛቱ በፊት ለፊፋ ባስገባው ቢዝነስ ፕላን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት ይቻል ዘንድ በነበረው ስምምነት መሠረት፣ የተወሰኑ ክፍሎችን ለማከራየት ጨረታ ሁለት ጊዜ ውጥቶ በሚፈለገው መጠን ተጫራች አልቀረበም፡፡ ግልጽ ጨረታ ለሦስተኛ ጊዜ ወጥቷል እየጠበቅን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዘንድሮ የውድድር መርሐ ግብር ተጀምሯል፣ ከፀጥታ ጋር በተገናኘ የነበረው ሥጋት ሙሉ በሙሉ ለማለት ወደፊት የሚታይ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ መልካም የሚባል ጅምር እየታየ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የፌዴሬሽኑ አተያይ ምንድነው?

አቶ ኢሳያስ፡- ከምንም በላይ የእግር ኳስ ሜዳው ፀጥታ ወደሚፈለገው ነገር እየመጣ ነው፣ ነገር ግን ሥጋት የለም ለማለት ጊዜ ወስዶ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በማዘውተሪያዎች የታየውን የሰላም ጭላንጭል ለማስቀጠል ከፌዴሬሽናችን ጀምሮ በየደረጃ የሚገኙ አካላት የድርሻችንን መወጣት ግድ ይላል፡፡ ይህ ለማምጣት ቀደም ሲል ረጅም ርቀት ተጉዘናል፣ ተስፋ ሰጪ ነገር እያየን ነው፣ በዋናነት የክለብ ደጋፊዎችና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ትልቁን ሥራ እያከናወኑ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ደጋፊዎቻችን መረዳት ያለባቸው ሽብርና ድንጋይ መወራወር የማይጠቅም፣ ይልቁንም ለከፋ ለንብረትና ለሕይወት ውድመት መንስዔ እየሆነ ችግሩ የሁሉንንም ቤት የሚያንኳኳ መሆኑን ነው፡፡ እያንዳንዳችን የእኔ ብለን ልንከታተለውና ልንከላከለው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ የሁለት ሳምንት ጉዞ እጅጉን የተፈሩ በተለይ በአማራና በትግራይ ክለቦች መካከል የታየው የወንድማማችነት መንፈስ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ሳይቀሩ የመቐለ ደጋፊዎች ካረፉበት ሆቴላቸው ድረስ በመሄድ ያወያዩበት ሁኔታ መኖሩ ታይቷል፡፡ ከዚህ ጀርባ ማየት የሚቻለው በሕዝባችን መካከል መሠረታዊ የሚባል ጥላቻ የሌለ መሆኑን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሊጉን በባለቤትነት ክለቦች እንዲያስተዳድሩት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ፌዴሬሽኑ በተለይ ከአዲስ አበባ ክለቦች ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባቱ ይነገራል፣ ችግሩ ምንድ ነው?

አቶ ኢሳያስ፡- ክለቦቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ናቸው፤ አለመግባባቱ “ቅራኔ” በሚያስብል ደረጃ ሊገለጽ የሚችል አይደለም፡፡ ፌዴሬሽኑ ከስታዲየም መግቢያ ትኬት ሽያጭ ላይ 32 በመቶ ማግኘት “አለብኝ” “የለብህም” በሚል የተፈጠረ በውይይት የሚፈታና ሒደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የሚገርመው እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚጫወት ፕሮግራም የተያዘለት ሰበታ ከተማ የሜዳ ገቢውን በሚመለከት በነበረው እንዲቀጥል ተስማምቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለቱ ክለቦች ቅሬታ ምንድነው?

አቶ ኢሳያስ፡- ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከስታዲየም ገቢ የሚቆርጠው 32 በመቶ ይበዛብናል የሚል ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ በኩል አሠራሩ የቆዬና የተለመደ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ገቢው ለውኃ፣ ለመብራት፣ ለሜዳ ሥራና ለሠራተኛ ወርኃዊ ክፍያ የሚጠቀምበት በመሆኑ ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም የሚል ነው፡፡ ክለቦቹ ፍላጎታቸውን አሳዩ እኛ ደግሞ ፍላጎታቸው ካለው ሁኔታ በመነሳት የሚያስኬድ ስላልሆነ በመነጋገር እንፍታው ነው፣ ይፈታልም ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ እግር ኳስ ሜዳውን እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ አሁን ላይ ክለቦች የየከተማቸውን ጨዋታ ከትኬት ሽያጭ ጀምሮ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እንዲያከናውኑ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ይገባኛል ሲል በምን አግባብ ነው?

አቶ ኢሳያስ፡- ሜዳውን እንድናስተዳድር ኃላፊነት የተሰጠን ከስፖርት ኮሚሽኑን ነው፣ በዚያ መሠረት የውስጥ ደንቦችን በማውጣት እያስተዳደርን የምንገኘው እኛ እንደመሆናችን መጠን በደንቡ ውስጥ በተካተተው መሠረት ድርሻችንን ማግኘት ይኖርብናል የሚል ሐሳብ አለን፡፡ ችግሩ ያን ያህል ወደ ክርክር የሚወስድም አይደለም የእኛ የክለቦቹ የውስጥ ጉዳይ ነው፡፡ ትኬት ቆረጣን በሚመለከት ክለቦች መቁረጥ እንደሚችሉ፣ ከዚህ በፊት የነበረው አሠራር መቀጠል እንደሌለበት ፌዴሬሽናችን የሚያምንበት ጉዳይ ነው፡፡ አምቡላንስ፣ የፀጥታ አካላትንና ተያያዥ ነገሮችን ማመቻቸትም በተመሳሳይ፡፡ ክለቦቹ እያንዳንዳቸው የሜዳ ገቢያቸውን በሚመለከት የመወሰን ሙሉ መብት አላቸው፣ የተቋሙም ፍላጎት ይኼው ነው፡፡ አሠራሩም በየትም አገር የተለመደና ያለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጉዳዩ እርሶ እንደሚሉት ሳይሆን፣ ክለቦቹ ችግሩን ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ማድረሳቸውና ሚኒስቴሩም የክለቦቹን ሐሳብ በመደገፍ ፌዴሬሽኑም አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥ መመርያ እንዳስተላለፈ የሚያመላክቱ ነገሮች አሉ፡፡

አቶ ኢሳያስ፡- ሚኒስቴሩን በሚመለከት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግልጽ ደብዳቤ አስተላልፏል፡፡ አሠራሩ ትክክል እንዳልሆነ፣ ክለቦቹ መነጋገርም ካለባቸው ከስፖርት ኮሚሽኑ ጋር መሆን እንዳለበት ጭምር አሳውቀን ሚኒስቴሩም አቅጣጫ ተሰጥቶበታል፡፡ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ለማኅበራት እውቅና የሚሰጠው ስፖርት ኮሚሽን እንደመሆኑ፣ የተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተም ግንኙነት ማድረግ እንዳለብን የሚገባኝ፣ ከዚሁ ተቋም ጋር መሆኑን ነው፡፡ ይህ ማለት የካፍና የፊፋ አሠራር እንደተጠበቀ ማለት ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ከተስማማን ኮሚሽኑን አልፎ ወደ ሚኒስቴሩ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተገቢም አይመስለኝም፡፡ ይህንኑ በሚመለከት ግልጽ ደብዳቤ ጽፌያለሁ፣ ምላሽም አግኝቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ፊፋ 70ኛ ጉባዔው በአዲስ አበባ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ጉባዔው ወደ ሌሎች የአህጉሪቱ አገሮች ሊዘዋውር እንደሚችል ይሰማል፣ ያለው ነገር ምንድነው?

አቶ ኢሳያስ፡- እንደተባለው የፊፋ ዋና ጸሐፊ ፋትማ ሳሙራና የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ከሰሞኑ መጥተው ከሚመለከታቸው የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተውበታል፡፡ ከፀጥታ ጋር በተገናኘ በአገሪቱ ሰላም እንደሌለ ፊፋና ካፍ የተጋነነ ሪፖርት ደርሷቸዋል፣ ውሸት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከስፖርት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከሌሎችም የመንግሥት ተቋማት ጋር ግልጽ ውይይት አድርገዋል፡፡ የሚገርመው በችግሩ ምክንያት ሊጉ ጭምር መቋረጡ ነው የተነገራቸው፡፡ በመሆኑም ፊፋና ካፍ ሊግ የማይካሄድበት አገር እንዴት ተደርጎ ጉባዔ ማካሄድ ይቻላል የሚል ግምት እንደነበራቸው፣ እዚህ መጥተው ያገኙት ደግሞ የተለየ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረው በአገሪቱ ባለው ነገር ደስተኛ መሆናቸውን፣ ስብሰባውም በመጪው ሰኔ እንዲካሄድ ዝግጅት እያደረጉ ስለመሆኑ ጭምር ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ የሚገርመው ሁለቱ ኃላፊዎች አዲስ አበባ በገቡበት ዕለት የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዕጣ የሚያወጡበት ዕለት ስለነበረ ያንን በዓይናቸው ተመልክተዋል፡፡ ከፀጥታ ጋር በተገናኘ ችግር እንደነበረ፣ አሁን ግን ሁሉም ነገር በሰላም እየተከናወነ ስለመሆኑ ከፌዴሬሽኑ ሊግ ኮሚቴ ጋር ሳይቀር ተነጋግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል እንግዶች እንደሚመጡ፣ ምን ያህል ሆቴሎች እንደሚያስፈልጉ፣ ለጉባዔው የተመረጠው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሰብሰቢያ አዳራሽ ለጉባዔው በሚመጥን መልኩ የዲዛይን ማሻሻያ እንደሚደረግለት፣ በየክፍለ አኅጉሩ የሚገኙ የእግር ኳስ ሌጀንዶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በብሔራዊ ወጣቶች አካዴሚ ስታዲየም የእግር ኳስ ግጥሚያዎች እንያደሚደርጉ በሚልኩት የኢሜይል መልዕክት አሳውቀዋል፡፡ የሚቀር ነገር ቢኖር በድጋሚ የፊፋ ልዑካን በጥር ወር መጥተው እንደሚያረጋግጡ ፕሮግራም ይዘዋል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...