Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የተዛባውን የክፍያ ሚዛን ማስተካከል ከቻልን የውጭ ምንዛሪ እጥረት አይኖርም››

ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ

አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) የገንዘብ ሚኒስቴርን በከፍተኛ አማካሪነት ከአንድ ዓመት በፊት ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ፣ በወጣትነት ዕድሜ ቱባ የአካዴሚና የሥራ ልምድና ተሞክሮ ያካበቱ የሕግና የኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው፡፡ በእንግሊዝ የጀመረው የዩኒቨርሲቲ ቆታቸው፣ ከለንደን ‹ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ› የሕግ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ባገኙት የትምህርት ዕድል ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቦሎኛ፣ እንዲሁም ከፈረንሣይ ኤክሲዮን ፕሮቮንስ፣ እንዲሁም ከቤልጂየም ገንት ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስና በሕግ ትምህርቶች የማስትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከትምህርት መልስ በምዕራብ አፍሪካ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ከሚሠራ ተቋም ጋር ሥራ የጀመሩት ብሩክ (ዶ/ር)፣ ጥቂት ቆይተው ባገኙት ተጨማሪ የትምህርት ዕድል ከፈረንሣይ ኤኮል ፖሊቴክኒክ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከሕግ ይልቅ ለኢኮኖሚ ሙያ ያደላው ልባቸው፣ በኒውዮርክና በማያሚ ፍሎሪዳ በኃላፊነት የሚሠሩባቸውን ሁለት ትልልቅ ተቋማት አስተዋውቋቸዋል፡፡ በተለይም ‹ዊንድልስ ማርክስ ኤንድ ሚተንዶርፍ› በተሰኘው አንጋፋ የሕግ ተቋም ውስጥ ለስድስት ዓመታት የመንግሥት ሕጎችን በመተንተን ካገለገሉ በኋላ ወደ ማሚ በማቅናት ‹ኤ ኤንድ ኤ ካፒታል› ለተሰኘ ኩባንያ የፈንድ ኃላፊ በመሆን ለሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ነበር የእናት አገር ጥሪ የደረሳቸው፡፡ ቀድሞውንም ወደ አገር ቤት በመግባት የድርሻውን ማበርከት ስለሚችሉበት ሁኔታ ሲያወጡ ሲያወርዱ በነበሩበት አጋጣሚ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ ባገኟቸውና ኢትዮጵያን የማገለልገል ጥሪ ባቀረቡላቸው ወቅት ሳያቅማሙ ጥሪውን ተቀብለው መምጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም እየተገበረ ሲሆን፣ እንደ ብሩክ (ዶ/ር) ያሉ የውጭው ዓለም የኮርፖሬት ባለሙያዎች ዕቅዱን በደጀንነት ያቀላጥፉታል፡፡ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የሚካሄደው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወር ፕሮግራም የማማከር ድርሻ የያዙት አቶ ብሩክ፣ ደርበው ደራርበው ሌሎችም ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ ሪፖርተር ለቃለ መጠይቅ ቢሯቸው ጎራ ባለበት ወቅት በአካልም በስልክም ፋታ በማይሰጥ የሥራ ውጥረት ውስጥ ነበሩ፡፡ ስለኢኮኖሚ ሪፎርሙና ስለፕራይቬታይዜሽን ከሚደመጡ ትችቶች እየጠቃቀሰ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄዎች የብሩክ (ዶ/ር) ምላሾችን ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ100 ሚሊዮን በላይ እንደ መሆኑ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራው የትኛው የኢኮኖሚ መርህ ነው? እንደ ኬኔሺያን ያሉ መርሆዎች ናቸው? በእርስዎ ዕይታ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሞዴል የትኛው ነው?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- እኔ እንደማየው ተግባራዊ እውነታ ወይል ‹ፕራግማቲስዝም› የሚባለውን መርህ ነው፡፡ የኬኔሺያንም ሆነ የፍሬድማን ወይም የሌሎች ኢኮኖሚያዊ መርሆዎች በማክሮና በማይክሮ ኢኮኖሚ ደረጃም ሲታዩ የማስተማሪያ መጻሕፍት ውስጥ ብቻ ነው ብልህነታቸው፡፡ የአንተና የእኔ ሕይወት የሚመራው በእውነታ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ እውነታ ደግሞ በተግባራዊ ሰዎች ይመራል፡፡ በእውነቱ እኔ እንደማስበው ይህ መንግሥት እየተከተለ ያለው መንገድና የእኔም መሥሪያ ቤት የሚመራው በተግባራዊ እውነታ ላይ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ የሚሠራው አካሄድ የቱ ነው? ይህን መሠረት በማድረግ ነው ፕራይቬታዜሽን የሚሠራው፡፡ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሲነደፍና ሲበለፅግም መነሻው ይኼው ነው፡፡ እንደ ግል እምነቴና አመለካከቴ ከሆነ ለአንድ የተለየ ጎራ ራሴን ለማስገዛት በመጣር፣ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ የማውለበልበው ሰንደቅ ዓላማ የሚገልጸኝ መርህና መሥራት የምፈልገው ይኼ ብቻ ነው ማለት አልፈልግም፡፡ ተግባራዊ እውነታ ነው፡፡ እኔ የሚታየኝ፣ እንዲሁም ይኼው ተግባራዊ እውነታ ነው የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት እየተቸገረ ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳው የተጋጋለ ክርክር ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አንዱ ሆኗል፡፡ እንደምንረዳው ሪፎርሙ ሦስት መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት አተኩሯል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የዘርፍ ወይም የሴክተር ችግሮችንና የመዋቅራዊ ችግሮች በሪፎርም አጀንዳው ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚው መስክ ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የብድር ዕዳና የመሳሰሉት በሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚቀረፉ አገር በቀሉ ሪፎርም አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ ሞጋቾች ሦስት ዓመት አይሁን የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት በቂ አይደለም በማለት ይከራከራሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ምልከታ ምንድነው?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- በእኔ ምልከታ ጠንክሮ ለሚሠራ ሦስት ዓመት ማለት እንደ የሕይወት ዘመን ጊዜ ነው፡፡ በርካታ ነገሮች ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ትኩረታችን ትክክለኛው ችግር ላይ እስከሆነ ድረስ ሦስት ዓመት እንደ ሕይወት ዘመን የሚቆጠር ነው፡፡ የኢኮኖሚውን መዛባት ያስከተሉ ትክክለኛና ወሳኝ ችግሮችን ለይተህ እስካወጣህና ዋና ምልክቶቹን ወይም ጠቋሚዎቹን እስካወቅካቸው ድረስ፣ እነዚህን ለመፍታት ጠንክረህ እስከሠራህ ድረስ ሦስት ዓመት በቂ ጊዜ ነው፡፡ ጥያቄው ግን ከተለዩት ችግሮች መካከል ያልተካተቱ አሉ ወይ የሚለው ነው፡፡ እኔ ባለሙያዎች ሲከራከሩበት ማየት የምፈልገው የተለዩት ችግሮች ምን ያህል ትክክለኛ ናቸው በሚለው ላይ እንዲሆን እንጂ ሦስት ዓመት በቂ አይደለም፣ አሥር ዓመታት ሊፈጅ ይችላል፣ አይችልም የሚል ሙግት አይደለም፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተለዩ ችግሮች ከሆኑ መዛባቱን ያስከተሉት ውይይቱም እነዚሁ ችግሮች ላይ ነው መሆን ያለበት፡፡ መንግሥት ችግሮቹን ለመፍታት አበክሮ እየሠራ በመሆኑ፣ ሦስት ዓመት አጭር ጊዜ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ለምሳሌ ለመፍታት እየሞከርናቸው ያሉትን አንዳንድ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን እንመልከት፡፡ የብድር ዕዳውን ካየህ ከግማሽ ያላነሰው የዕዳ ክምችት ምላሽ አግኝቷል፡፡ አብዛኞቹን ከቻይና መንግሥት የተገኙ ብድሮች ለማራዘም ችለናል፡፡ ይህ ግማሽ ያህሉን በስኬት ያጠናቀቅንበት ውጤት ነው፡፡ የዕዳ ጫናችን በወሳኝ ደረጃ ቀንሷል፡፡ ከእያንዳንዱ የፋይናንስ ተቋም ጋር በምናደርገው ውይይት የዕዳ ተጋላጭነታችንን ለማቃለል የሚረዳ ሐሳብ እያቀረብን ነው፡፡ በርካታ መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ዕሙን ነው፡፡ በርካታ የማጣጣም ወይም የማብቃቃትና መዋቅር የመዘርጋት ሥራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህን በማከናወን ክፍያ በምንፈጽምበት ወቅት እውነታ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ይኖረናል፡፡

በሥራ አጥነት ጉዳይ ላይ ከለየን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ዕቅድ ወጥቷል፡፡ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ተቋቁሞ እነዚህን ሥራዎች ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሠራ ነው፡፡ በአይሲቲ ዘርፍ ካየንም የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከ250 ሺሕ ያላነሱ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ጠንክሮ እየሠራ ነው፡፡ ሁለት ተጨማሪ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ሲገቡና እያደገ የመጣው የዲጂታል ኢኮኖሚ ሲስፋፋ 250 ሺሕ የሥራ ዕድል መፍጠር በጣም ቀላሉ ጉዳይ መሆኑ አይቀርም፡፡ የዋጋ ግሽበትን ከተለያየ አቅጣጫ ምላሽ ለመስጠት እየሠራንበት ነው፡፡ የአቅርቦት የገንዘብ ሥርጭት ወይም ሸቀጥ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ያባባሱት ችግር ስለመሆኑ እያጣራን ነው፡፡ የትኞቹ ጉዳዮች ናቸው ይህንን ችግር እያስከተሉ ያሉት የሚለውን ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች እየቃኘን ነው፡፡ አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በሎጂስቲክስ፣ በአቅርቦት መስክ፣ ምርት በመሸሸግና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ማጣራት እየተካሄደ ነው፡፡ የምንመድበው ሀብት አግባብ ባለው መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ወይ የሚለውን ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች እየተመለከትን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወሳኝ ሸቀጦችን ማከፋፈል እንዲችሉ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል፡፡

ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ስናይ ሦስት ዓመት አጭር ጊዜ ነው ልንል አልችልም፡፡ የመዋቅራዊና የዘርፍ ችግሮች ላይም ተመሳሳይ አካሄድ እንከተላለን፡፡ በመዋቅራዊ የሪፎርሙ መስክ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዲስ የኢንቨስትመንት ሕግ አፅድቋል፡፡ በዘርፍ ረገድ የመንግሥት የልማት ድርቶችን ሚናና አስተዋጽኦ እንደ አዲስ የሚያሻሽል አካሄድ እየተከትልን ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንዶቹ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በግልጽ ሚናቸውን ዳግመኛ መፈተሽና እንደ አዲስ መቃኘት እንደሚፈልጉ ነግረውል፡፡ የግሉ ዘርፍ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ከመሻማት ይልቅ፣ እሴት ጨምረው መሥራት ወደ ሚችሉበት ደረጃ ከፍ ማለት እንደሚፈልጉ ነግረውናል፡፡ ይህ በድርጅቶቹ አስተዳደር በኩል የቀረበልን ትልመ ሐሳብ ነው፡፡ መንግሥት ክፍተቶቻቸውን ካየና ከፈተሸ በኋላ እንደ ፋይናንስ ባሉ እጥረቶቻቸው ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ይጠበቃል፡፡ አብዛኞቹ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ1940ዎቹ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ እንደ አዲስ መቃኘት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ያላቸውን መጋዘን፣ ምን ያህል መኪኖች፣ ሌሎች ንብረቶችና ቁሳቁሶች እንዳሏቸው ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁሉ እያንዳንዱ ግለሰብ በሚሠራው ልክ የሚወሰኑ ናቸው፡፡ ጠንክረን ከሠራንና ይህ እንዲሳካ ከጣርን ሦስት ዓመት የዕድሜ ልክ ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች አኳያ ሲታይ ሥር የሰደደ የምርትና የምርታማነት ችግር አለ፡፡ ብዙ ምርት የለም፡፡ እንዲሁም ያን ያህል ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት የለም፡፡ ይህ ችግር እንዴት ታይቷል?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- አጠቃላይ የምርታማነት አቅምንና የኢኮኖሚው ውጤታማነት ለማሻሸል ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ ቶሎ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ ዕድሎችም አሉ፡፡ በአይሲቲ ዘርፍ ለምሳሌ ምርታማነት የሚገለጸው እያንዳንዱ ግለሰብ ለሥራ ባዋለው ጊዜና አቅሙን ተጠቅሞ በመሥራት አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ሐሳቦችን በማመንጨት በሚሠራው ነው፡፡ ይህ ከሆነ ግለሰቦች ከተቋም ይልቅ ምርታማነታቸውን ማሳደግ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ በግብርናው መስክ ካየንም የግብርና ሚኒስቴር የሜካናይዜሽን እርሻን ለማስፋፋት እየሠራ ነው፡፡ ከቀረጥ ነፃ ዕድሎችን በመፍቀድና አዳዲስ ማበረታቻዎችን በመፍጠር፣ ትራክተርና ሌላውም የእርሻ መሣሪያ እንዲገባ ሊደረግ ነው፡፡ በማኑፋክቸሪንግ መስክ ካየንም፣ የምርትና የምርታማነት ደረጃ እስኪመጣ ድረስ ሁልጊዜም መጠበቅ ያለብን ጊዜ አለ፡፡ በፋብሪካ የሚሠሩ ግለሰቦች የሚያመርቱት ምርት ከሌሎች አገሮች ተመሳሳይ ምርት አኳያ ከታየ፣ እዚያ እስክንደርስ መጠበቅ ያለብን ጊዜ አለ፡፡ ሥልጠናና ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ በተለይም የትምህርት ሥርዓቱና ሌሎችም ለምርታማነት መሻሻል የራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል፡፡ እንዳልኩት ውጤታቸው በቶሎ የሚደረስባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ምርታማነት ተሻሽሎ ለውጥ ለማምጣት አንዳንድ መስኮች ጊዜ መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአገር የኢኮኖሚ ሪፎርም ሲነሳ ከስያሜው ጀምሮ በርካታ ክርክሮችና ሒሶች ሲሰነዘሩ ይደመጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ዕቅዱ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት በቀጥታ የተቀዳ ነው በማለት ጭምር ይሞግታሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ ወደ ራስ የሚመለከት አገር በቀል አጀንዳ ነው ይላል፡፡ በእነዚህ ሙግቶች የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- ስያሜን መሠረት አድርጎ በሚነሳ ጉዳይ ላይ መከራከር በጣም ከባድ ነው፡፡ ውይይትና ክርክሩ ስያሜ ላይ ከሆነ ዕቅዱን ሌላ የሚመች ስም እንዲሰጠው ማድረግ ነው፡፡ ለስያሜ በሚደረግ ክርክር ላይ የማጠፋው ጊዜም ሆነ እውነታን የሚያስረዳ ሙግት ማቅረብ አልችልም፡፡ ይህ ለእኔ ዕርባና የለውም፡፡ ሆኖም ማንም ቢሆን በዕውቀት ላይ የሞኖፖል ሥልጣን የለውም፡፡ የዓለም ገንዘብ ድርጅት የተወሰነ ያከማቸው ዕውቀት ይኖረዋል፡፡ የዓለም ባንክም እንደዚያው፡፡ አቶ ብሩክም የራሱ ዕውቀት አለው፡፡ ሁሉም ሰው በውስጡ ዕውቀት አለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስቀመጡት፣ ምርጥ ምርጥ ኢትዮጵያውያን ጭንቅላቶች የተሳተፉበት የሪፎርም ፕሮግራም በመሆኑ፣ እኔም በዚህ ሒደት ውስጥ መሳተፍ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ጊዜያቸውን ዕቅዱን በመንደፍ ያሳለፉ እነዚህ ሰዎች የሚደነቁ ናቸው፡፡ ከየትኛውም አካባቢ ሊገኝ የሚችል የሐሳብ ተፅዕኖ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ያለና ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ሐሳብ ገደብ የለውም፡፡ ትዋሳለህ፣ ትቀዳለህ፣ እንዲሁም ከራስህ ጋር በማዋሀድ ወይም ፈጠራ በማከል ትጠቀምበታለህ፡፡ ለእኔ መሠረታዊው ጉዳይ ይኼ ሐሳብ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል፣ ይሠራል ወይ የሚለው ነው፡፡ ይህ ተግባዊ እውነታ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ቀዳዳዎች አሉት ወይ የሚለውን በማየት ቀዳዳዎች ያሉት ከሆነ፣ እዚህ ላይ መነጋገር እንጂ ስያሜው ላይ ማተኮር አይገባም፡፡ በመዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ግማሽ እውነትነት ያላቸው አካሄዶች እየሄድን ከሆነ እዚያ ላይ መነጋገር ይጠቅማል፡፡ የትኞቹን ጉዳዮች እንደ ዘለልናቸው ለማሳየት የሚሞክር ሰው ቢኖር መልካም ነበር፡፡ አካሄዳችን ትክክል ካልሆነ ይኼንኑ በመግለጽ የሚሞግቱ ሰዎች ከስያሜ ይልቅ ሐሳባቸውን ቢለግሱ መልካም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በአገር በቀል ዕቅዱ ውስጥ ያስቀመጣቸውን ግቦች የማሳካት ብቃቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- አገር በቀሉ የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ተጨማሪ ገንዘብ ማሰባሰብ የሚያስፈልገው በመሆኑ የራሱ ፈታኝ ሁኔታዎች ይኖሩበታል፡፡ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለዕቅዱ መሳካት ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ ነገሮች በተቀመጠላቸው ትክክለኛ መስመር መጓዝ ካልቻሉ ይህንኑ በተመለከተ ጉዳዬ የሚል አካል እንዳለ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አካሄዱ ላይ ንቁ ክትትል በመኖሩ በየመንገዱ የማስተካከያ ዕርምጃ በመውሰድ ዕቅዱ እንዲሳካ መደረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ግቦቹ የተለጠጡ በመሆናቸው አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎች ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በዕቅዶቹ ላይ እየሠራ ያለው አካል ስኬታማ እንዲሆኑ እየሠራ ነው፡፡ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አካል በመሆን፣ በገቢ ማሰባሰብ ላይ የሚከናወነው ሥራ ተቋማትን ወደ ግል የማዛወር ሥራንም ያካትታል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ በሙሉ ልብ በመሥራት በጊዜው አጠናቀን ለማቅረብ እየተዘጋጀን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ኢንቨስተሮች ትርፋቸውን ወደ አገራቸው በመውሰድ ረገድ መቸገራቸው ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ይሁን እንጂ አሳሳቢ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ ገንዘባቸውን መውሰድ እንዳልቻሉ ይገለጻል፡፡ መንግሥትም ትርፋቸውን መልሰው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሲወተውት ቆይቷል፡፡ 

ብሩክ (ዶ/ር)፡- አዎን ይህ ጉዳይ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር መኖሩም ዕሙን ነው፡፡ የወጪ ንግድ ዘርፋችን የተንሻፈፈ በመሆኑ ላኪዎች ብዛት ያላቸውን ምርቶች ወደ ውጭ ለመላክ አይበረታቱም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከውጭ በማስገባትና በውድ ዋጋ በመሸጥ ገንዘብ ማግኘት ተመራጭ እየሆነ ነው፡፡ ይህ የሆነው ምርት ወደ ውጭ ለመላክ በሚፈለግበት ወቅት ውጣ ውረዱ ስለሚያስቸግር ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመቅረፍ ሁሉን አቀፍ አካሄድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ ገንዘባቸውንና ትርፋቸውን ወደ አገራቸው መላክ አለመቻላቸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መገለጫ ፀባይ ሊሆን እንደማይችል ተደጋግሞ የተጠቀሰ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት የገቢ አሰባሰብ ስትራቴጂውን በማሻሻል በርካታ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ የሚያስችል ማበረታቻ የሚሰጥበት አካሄድ እየመጣ ነው፡፡ የተዛባውን የክፍያ ሚዛን ማስተካከል ከቻልን የውጭ ምንዛሪ እጥረት አይኖርም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ የውጭ ምንዛሪ እንዴት እንደሚተዳደር አካሄዶቹን አስተካክሏል፡፡ ከሁሉ አቅጣጫ መልካም አስተዳደር ያሰፍናል፡፡ ኬንያ በአግባቡ የውጭ ምንዛሪዋን አስተዳደር አስተካክላ እጥረቱ ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ከመጣች እኛስ እንዴት ያቅተናል? ከምሥራቅ አፍሪካ ከሶማሊያ በስተቀር አብዛኛውን የዳያስፖራ ቁጥር የያዝነው እኛ ነን፡፡ ከዳያስፖራው የሚመጣውን ሐዋላ ማሳደግ ከቻልንና በመደበኛው መንገድ እንዲገባ ካደረግን፣ በርካታ ገንዘብ መምጣቱ አያጠራጥርም፡፡ በወጪ ንግድ ረገድ ቡናና ሰሊጥ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ፣ የማዕድን ዘርፉም ብዙ ሊያስገኝ የሚችል በመሆኑ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ፖታሽ፣ ሰልፈር፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ወርቅና ሌላውም ዓይነት ሀብት አለን፡፡ ተገቢውን ባለሀብትና ተገቢውን የንግድ መዋቅርና ሥርዓት ከፈጠርን ኢትዮጵያ የሚገቧትን ሁሉንም የሮያሊቲና ሌሎችም ጥቅሞችን ማግኘቷ አይቀርም፡፡ ይህ በሚሆንበት ወቅት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱም ሆነ ትርፍን ወደ ውጭ መውሰድ ችግር መሆኑ ያበቃለታል ማለት ነው፡፡ ሁሉንም ነገር አቀናጅቶ በአንድ መስመር የመቃኘት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ሁሉም ሚኒስቴሮች እየሠሩ ነው፡፡ ሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአግባቡ መሥራት ከቻሉ፣ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የሚችለው የወጪ ንግድ ምርት ከፍተኛ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ሰዎች ባልተገባ መንገድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው የበለጠ እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርገው፡፡ በረዥም ጊዜ ውስጥ ግን ይህ ችግር እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- የገቢ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል ተጨባጭ አካሄድ አለ?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- ሁልጊዜም ተጨባጭና ትክክለኛ አካሄድ ይኖራል፡፡ ነገር ግን በርካታ አካሄዶች መዘርጋት አለባቸው፡፡ የገቢ ንግዱን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት በምንሞክርበት ወቅት አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች እ.ኤ.አ. በ197ዎቹና በ1980ዎቹ የገጠማቸውን ዓይነት ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በርካታ አገሮች ከውጭ የሚገባውን ምርት ለማዳከም የታክስ ጫና ማድረግ እንደሚሻል አምነው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የጣሉት ታክስ በአገር ውስጥ ለማምረት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከባድ አድርጎት ነበር፡፡ ከውጭ የሚገቡና ለምርት ሥራ የሚውሉ ግብዓቶች የታክስ ጫና ውስጥ ወደቁ፡፡ የውጭ ምርትን በአገር ውስጥ ለመተካት ባስቀመጡት ግብ መሠረት፣ እስከ 70 በመቶ ታክስ በመጣል ገቢ ንግዱን እንደሚያኮላሹት አስበው ነበር፡፡ በዚህ ዕርምጃቸው የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እንደሚያድጉ አስበው ነበር፡፡ ሆኖም አልተሳካላቸውም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃህ ወደ ውጭ የምትልከውን ምርት ይወስነዋል፡፡ አንድ አባባል አለ፡፡ በጣም ውስብስብ ምርቶችህን ለጎረቤት አገሮች፣ በጣም መሻሻል የሚያስፈልጋቸውን ተራ ምርቶች ሩቅ ላሉ አገሮች አቅርብላቸው ይባላል፡፡ ይህ የሚሳየን የምርት ብዝኃነትን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ ወደ ውጭ በምንልካቸው ምርቶች ውስጥ አዳዲሶች መካተት አለባቸው፡፡ ቡናና ሰሊጥ በመላክ ችግሮቻችንን መፍታት አንችልም፡፡ በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ ስላለን አሁንም በርካታ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ያስፈልጉናል፡፡ በኢንዱስትሪና በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ እንዲኖረን ካስፈለገ የካፒታል ዕቃዎችን ማስመጣታችን አይቀሬ ነው፡፡ ለገቢ ንግድ የሚኖረው ፍላጎት እየጨመረ መሄዱ ግድ ቢሆንም፣ ይህንን መቋቋም የሚያስችል አካሄድ ያስፈልገናል፡፡ ትልቅ አገር አለችን፡፡ ኢነርጂን ጨምሮ በርካታ ወደ ውጭ ልንልካቸው የምንችላቸው ጥሬ ዕቃዎችና ሀብቶች አሉን፡፡ ይሁን እንጂ ስትራቴጂካዊ አካሄድ መከተልና በርካታ የወጪ ንግድ ምርቶች እንዲኖሩን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በማኑፋክቸሪንግ መስክ ኢትዮጵያ የተከተለችው አካሄድ የተሳሳተ ነው የሚሉ ክርክሮች እየተመደጡ ነው፡፡ የዚህ ክርክር መነሻም አገሪቱ ይኼ ነው የሚባል ጥሬ ዕቃ ሳይኖራት በገፍ ከውጭ በሚገባ ጥሬ ዕቃ ላይ የተመሠረተ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መከተሏ ነው ይላሉ፡፡ አምራቾች አብዛኛውን ጥሬ ዕቃ ከውጭ እንደሚያስገቡ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ወጪን በማናር የኢትዮጵያ ምርቶች በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያደርጋል የሚል ሐሳብ ይነሳል፡፡ ይህን ክርክር ይቀበሉታል?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- ወደ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ሳልገባ በደፈናው ችግሩ መኖሩ የታወቀ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ሥራው ሲጀመር የ70/30 አካሄድ ሊከተል ይችላል፡፡ [70 በመቶ ጥሬ ዕቃው ከውጭ የሚገባ] በሒደት ይህንን ወደ 60/40 በመቶ አካሄድ ዝቅ ማድረግ ይቻላል፡፡ ቆይቶ አምራቹ 90 በመቶውን ጥሬ ዕቃ ከአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህ መደበኛ የለውጥ ሒደት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ዳቦ ቤት ያለው ሰው፣ ከውጭ በሚገባ ስንዴና ዱቄት ለማምረት ከተገደደ እዚህ ላይ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያሳይሃል፡፡ መንግሥት በቁጥጥር ሥራዎች ላይ በማተኮር የግሉ ዘርፍ ተዋናይ እንዲሆንበት ማድረጉ ግን የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል፡፡ መንግሥት የሚሰጣቸው ማበረታቻዎች የተቀናጁ መሆናቸውን፣ በተለይም የታክስ ማበረታቻዎች በአብዛኛው ከአገር ውስጥ የሚገኝ ጥሬ ዕቃን ለመጠቀም የሚያስችሉ እንዲሆኑ መደረግ አለባቸው፡፡ ሆኖም የአገር ውስጥ ግብዓቶች ምን ያህል ለአምራቹ ቅርብ ናቸው? የስንዴ ምርት ከአገር ውስጥ ገበሬ ከመግዛት ይልቅ ከውጭ ማስገባቱ ርካሽ ነው? የአገር ውስጥ ገበሬ መሬቱ አነስተኛ በመሆኑ የተለያየ የጥራት ደረጃ ያለውን ስንዴ ለመግዛት የሚያስገድድ ሁኔታ ካለ የዱቄት ምርቱም የጥራት ደረጃው የተለያየ ስለሚሆን፣ እንዲህ ባሉት ጉዳዮች ላይ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያሳያል፡፡ ችግሩ የተደራረበና በርካታ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ሙከራ የሚቀረፍ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥትና የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት ኢኮኖሚው በርካታ መዛባቶች ውስጥ ገብቷል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶች ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብታለች በማለት ሲተቹም ይደመጣሉ፡፡ በዚህ ይስማማሉ?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- በጭራሽ፡፡ ወደ ቀውስ የሚወስድ ምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ አይደለንም፡፡ ምናልባት የአመለካከት ቀውስ ውስጥ ገብተን ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ቀውስ ውስጥ እንደገባን ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ግን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብቷል? ይህ የማልቀበለው ሐሳብ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ገብታለች እየተባለ ያለው እኮ በማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ነው?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- በኢኮኖሚክስና በኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች መካከል ያለው ብቸኛና የተከበረ ነገር የትምህርት ቤት እሳቤ ነው፡፡ የትኛውም የኢኮኖሚ ባለሙያ፣ ጀማሪ የኢኮኖሚ ኮርስ የወሰደውም የየራሱ አመለካከት ይኖረዋል፡፡ ይህ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቀውስ ውስጥ ያልወደቀውን ቀውስ ውስጥ ገብቷል ማለት ግን የሚያሳስብ አመለካከት ነው፡፡ ለመከራከሪያቸው ያቀረቡት ማስረጃ ምን እንደሆነ ባላውቅም፡፡ በኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ምን ያህል ማሳካት ይጠበቅ እንደነበር ሲታይ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚው ቀውስ ውስጥ ገብቷል የሚለውን አልቀበልም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ቀውስ ውስጥ ነን የሚሉት ባለሙያዎች የሥራ አጥነትን፣ የዋጋ ግሽበትን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ድክመትን፣ የገንዘብ ማሸሽ ተግባራትን በማውሳት እነዚህን የአገሪቱን አንጡራ ሀብት በማባከን ቀውሱን እንደፈጠሩት ይሞግታሉ፡፡

ብሩክ (ዶ/ር)፡- ይህ ግን ፍርኃት ከመንዛት የዘለለ ጭብጥ የለውም፡፡ ቀውስ አልተፈጠረም፡፡ እውነት ነው መፍታት ያሉብን የኢኮኖሚ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህ ጥያቄ የለውም፡፡ በዚህ መንገድ ላስቀምጠው፡፡ አንድ ድባቴ ያደረበት ሰው ዓይተህ ይኼንን ሰው ጭንቀት አድሮበታል ብትል እውነትነት አለው፡፡ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ይኼንን ሰው ካደረበት ድባቴ ለማውጣት የሚደረገው ጥረት ነው ጠቃሚው ነገር፡፡ አዎን ካፒታል ወይም የውጭ ምንዛሪን የማሸሽ ጉዳይ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ ምኑ አዲስ ነው? የነበረ የከረመ ችግር ነው፡፡ መንግሥት እንዲያውም ማበረታቻዎችን በመስጠት ሰዎች ካፒታላቸውን መልሰው ኢንቨስት እንዲያደርጉት በማድረግ፣ ሲያደርጉም በአግባቡ ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ እየሠራ ነው፡፡ ደካማ የፕሮጀክት አስተዳደርም ሆነ የአቅም ብቃት ማነስ የነበረ ችግር ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ለመቅረፍ ከፕሮጀክት ቀረፃ እስከ ትግበራው ድረስ አዲስ ሞዴልና አካሄድ መከተል እንደሚያስፈልግ አምኖበታል፡፡ ተለይተው በተቀመጡ ችግሮች ላይ ማስተካከያ እንዲደረግባቸው በርካታ ጥረቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያለፈው ታሪክ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕድል ፈንታ መወሰን አይኖርበትም፡፡

ሪፖርተር፡- የሪፎርም አጀንዳው ከሚዘውራቸው ጉዳዮች አንዱ ፕራይቬታይዜሽን በመሆኑ ይህንን ጉዳይ እናንሳ፡፡ ይህም ቢሆን ግን አከራካሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ እርስዎ በተገኙባቸው ስብሰባዎችም ይህ ጉዳይ ተነስቷል፡፡ ባለሙያዎች እርስዎ ወይም መንግሥት ካለው ምልከታ የተለየ ሐሳብ አላቸው፡፡ ለመሆኑ የፕራይቬታይዜሽኑ አንጀንዳ ምንድነው?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- የፕራይቬታይዜሽን አንጀዳ ያለን አይመስለኝም፡፡ ያለ መግባባት ችግር አለ፡፡ እኔ የማውቀው አጀንዳ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሪፎርም የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ አጀንዳ ላይ ነው እኔም እየሠራሁ ያለሁት፡፡ በካፒታል እጥረታቸው፣ በብቃት ማነስ ችግራቸውና በዕዳ ጫናቸው መቀረፍ ላይ ያተኮረና የተቀረፀ አጀንዳ ነው ያለው፡፡ ይህንን ለማሳካት መንግሥት በተለየ አቅጣጫ እየተጓዘ ሲሆን፣ በርካታ በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ ዘርፎችን ወይም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደ ግል የማዛወሩ ተግባርም አብሮ ይመጣል፡፡ ፕራይቬታይዜሽን የሪፎርም አጀንዳው አንድ ንዑስ ይዘት ነው፡፡ መንግሥት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሪፎርም አጀንዳ ላይ እንደሚሠራ እንጂ፣ ወደ ግል ማዛወር ላይ በሚያጠነጥን አጀንዳ እየተንቀሳቀሰ አይደለም፡፡ ዓላማውም ይህ አይደለም፡፡ በተገኘሁባቸው የሕዝብ ውይይቶች አንዳንዶች ሐሳቡን በመሳት ሲናገሩ ዓይቻለሁ፡፡ ለምሳሌ ስለስኳር ዘርፍ ፕራይቬታይዜሽን ሲነሳ፣ ኢትዮጵያ በስኳር ምርት ራሷን መቻል ብቻም ሳይሆን ወደ ውጭ በመላክ ጭምር ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል ለማድረግ ነበር፡፡ ይህ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ አልተሳካም፡፡ ስለዚህ አሁን እንዲሳካ ለማድረግ ተጨማሪ 100 ቢሊዮን ብር ከበጀት፣ ከግምጃ ቤት በማውጣትና የታክስ ከፋዩን ገንዘብ በመጠቀም የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓቱን ትቀይራለህ? ወይስ እንደ መንግሥት የቁጥጥር ሥራህ ላይ በማተኮር ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ በመተው፣ በግልጽ አሠራር ከዚህ ዘርፍ የሚመነጨውን ገንዘብ ሌሎች መሠረተ ልማቶችና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ታውላለህ? ንግዱን የማከናወኑ ሚና የግሉ ዘርፍ ራስ ምታት እንዲሆን ተውለት፡፡ ተጨማሪ ካፒታል የሚጠይቁ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ከየት ነው ይኼንን ካፒታል የሚያገኙት? መንግሥት እንደሆነ የአጭር ጊዜ ብድር መውሰድ አቁሟል፡፡ ስለዚህ ተጨማሪውን ገንዘብ ከየት ነው የምታገኘው? ወደ ግል በከፊል በማዛወርና የራሳቸውን የተወሰነ ድርሻ እንዲይዙ በማድረግ ሥራቸውን ማስቀጠሉ ነው ያለው አማራጭ፡፡ የነበሩት ውይይቶች ጤናማ ነበሩ፡፡ ይሁንና ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮምን የተመለከቱ አንዳንድ ክርክሮች ጭብጣቸውን የሳቱ ነበሩ፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል እንዲዛወር የሚደረገው ሁለት ተፎካካሪዎች ስለሚመጡበት፣ በገበያው ያለውን ንቁ ተሳትፎ የሚያሻሽል መዋቅር እንዲኖረውና በምሥራቅ አፍሪካ ጭምር ውጤታማ ተዋናይ እንዲሆን ለማገዝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ሐሳብ መልካም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በኬንያ አየር መንገድ ላይ የደረሰው ሲታይ ጥያቄ እያጫረ ነው፡፡ መጀመርያ ወደ ግል የተዛወረው የኬንያ አየር መንገድ (KQ) በኪሳራ ተንኮታኩቶ አሁን መልሶ ወደ መንግሥት እጅ እንዲገባ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ እንደ ብሔራዊ ኩራት የሚታየው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ ሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የኬንያ አየር መንገድ ዕጣ እንዳይገጥማቸው ሥጋት አለ፡፡ ይህ እንዳይከሰት ምን ያህል ታስቦበታል?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- እንደ እኔ በኬንያ አየር መንገድ ላይ የደረሰው ነገር እኛ ከምንሠራው ጋር የሚያገናኘው ነገር የለውም፡፡ ከእኛ ሥራ ጋርም አይነፃፀርም፡፡ የኬንያ አየር መንገድ ለግሉ ዘርፍ በመሸጡ ወይም በግሉ ዘርፍ በመተዳደሩ ምክንያት አይደለም ችግር የገጠመው፡፡ ችግሮች ማጋጠም የጀመሩት በናይሮቢ የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች ያሳደሩት ተፅዕኖ የቱሪስቶችን ቁጥር በመቀነሱ፣ የተቋሙ የማስፋፊያ ስትራቴጂ፣ የአስዳደራዊ ስትራቴጂዎቹና ሌሎችም ጉዳዮች ናቸው አየር መንገዱ አሁን ለሚገኝበት ሁኔታ ያበቁት፡፡ አየር መንገዱ ወደ ግል ተዛውሮ ነበር፡፡ አሁን መልሶ ወደ መንግሥት እጅ እየዞረ ነው፡፡ ይህ ግን ከእኛ ጋር የሚያገናኘው ነገር አይታየኝም፡፡ የስኳር ዘርፉን ካነሳህ የምታወራው በፍፁም ስለማይገናኝ ጉዳይ ነው ማለት ነው፡፡ ስለኢትዮ ቴሌኮም ሲነሳ አስነተኛ ድርሻ ያላቸውን አክሲዮኖች ነው የሚሸጠው፡፡ ይህም የተቋሙን የፋይናንስ አቅም በመገንባት የገበያ ድርሻውንና የመስፋፋት አቅሙን ለማገዝ የሚደግፈው አካሄድ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የኢነርጂ ዘርፉም በከፊል ወደ ግል ይዛወራሉ፡፡ ይሁንና ጥናታችን ገና ያላለቀ በመሆኑ፣ በከፊል የሚዛወሩ ድርጅቶች ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ በደንብ እያጠራን ነው፡፡ አስተሳሰባችንን ይበልጥ በማስፋት በመጪዎቹ 10 እና 15 ዓመታት ውስጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ጥናቱ ይነግረናል፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ ግን ከዚህ ቀደም የተከናወኑትን እንደማናስቀር ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ይህንን ሥራ ስጀምር በአብዛኛው የጻፍኳቸው ምክረ ሐሳቦች ያጠነጠኑት ከስኬቶች ይልቅ በውድቀቶች ላይ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሌሎች አገሮች እንዴት ሳይሳካላቸው እንደቀረ ማወቅ ስለሚጠቅመን ነው፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ለማወቅ ስንሻ በአብዛኛው በግልጽነት ችግር፣ በሙስና፣ እንዲሁም አርቆ ማሰብ ባለመቻል ጦስ የተፈጠሩ ችግሮች እንዳሉ ዓይተናል፡፡ እኛ ለመፍጠር የምንሞክረው ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ እንዳይደገም ለማድረግ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...