Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከፖለቲካው ይልቅ ኢኮኖሚው ላይ ማተኮሩ ዳቦ ይሆንልናል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኖቤል ሰላም ተሸላሚ መሆን እንደ ኢትዮጵያዊ ሁላችንም የምንደሰትበት ታሪካዊ ክስተት ተደርጎ የሚጠቀስ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት ሽልማት በግል የእርሳቸው ጥረት ውጤት ቢሆንም፣ ሽልማቱ ግን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡

እርሳቸውም ይህ ሽልማት የእርሳቸው ብቻ ያለመሆን፣ የኢትዮጵያንም ብቻ ተደርጎ የሚገደብ እንዳልሆነና ሽልማቱን ለማግኘት አንዱ ምክንያት የሆኑት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና የኤርትራውያን ጭምር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በጥቅል ሲታይ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት እንደ አገር ቢታሰብ እጅግ ከፍ ያለ ትርጉም ያለው ነው፡፡ በድህንነት፣ በረሃብና በጦርነት ትጠቀስ የነበረች አገር እንዲህም ያለ ክብር መጎናፀፍ እንደምትችል የሚያሳይ ነው፡፡ ሽልማቱ የአገራችን ታሪክ በመለወጥ ብሎም በማስተዋወቁ ረገድ በዘመናት ልዩነት የተገኘ ዕድል ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡

በተለይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው ሰብሳቢ ያደረጉት ንግግር በየትኛውም መልኩ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ሊደረግ ከሚችለው ጥረት በላይ ዋጋ የነበረው እንደነበር ስናስብ፣ ሽልማቱና የሽልማቱ መድረክ ላይ የተሰማው ሁሉ ለአገር መልካም አጋጣሚን የፈጠረ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ በጎ ታሪኮቻችንና ኢትዮጵያን የገለጹበት መንገድም ቢሆን እንደ ዜጋ ቀና ብለን እንድንሄድና ነገን በተስፋ እንድንመለከት ያደረገ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ከሆነች እኛም ኢትዮጵያውያን ነን ብለው ፈረንጆች ስለእኛ ማውራት የቻሉበት መድረክ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአጋጣሚውም እንዲህ እንድንባልና ዕድል እንድናገኝ ምክንያት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማመሥገን ተገቢ ይሆናል፡፡

ይህ ዓለም ስለኢትዮጵያ በጎ ነገር የሰማበት መድረክ የበለጠ ትርጉም የሚኖረው ግን፣ አገራችንን ካለችበት ድህነት በሚያወጡ ተግባራት ሲታጀብ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ መድረኩ መልካም ከተሠራ መሸለም እንደሚቻል የታየበት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በተዋወቀችበት ልክ ተጠቃሚ እንድትሆን ዕድሉን መጠቀም ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተዘጋጀላቸው የእራት ግብዣ ላይ ፖለቲከኞች ኢኮኖሚው ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው የሚያመለክተው መልዕክት በተግባር እንዲተረጎም እንሻለን፡፡ ይህ በአጭሩ ሲገለጽ ‹‹ሁሉም ወደ ሥራ ይግባ›› የሚል ነው፡፡

ስለዚህ አሁን ከዓለም እየተሰጠን ያለው መልካም ነገር የበለጠ ጣዕም የሚኖረው አገራችንን ወደ ፊት በሚያራምዱ ሥራዎች ራሳችንን ስናስገዛ ነው፡፡ በቀደሙት ዓመታት በሆነውም ባልሆነውም ጉዳይ ያጠፋነው ጊዜ ሊቆጨን ይገባል፡፡ በሚያስማማን ተስማምተን በልዩነቶች ላይ ደግሞ እየተነጋገርን የመሄድ ልምድ ከሌለ፣ ሕዝብን ከማደህየት በቀር የሚተርፍ ነገር የለም፡፡

አንዳንዴ የሚገርመው በርካታ ፖለቲከኞች ስለኢኮኖሚው ጉዳይ ቁብ ሳይሰጡ፣ አጥተው መያዣና መጨበጫ የሌለውን የፖለቲካ ትርክታቸውን ሲያነበንቡ ማየት የሚያቆሙት መቼ እንደሆነ ነው፡፡

አገር በፖለቲካ ንትርክ ትበለፅግ ይመስል ለንትርክ ከሚጋበዙ ድርጊቶቻቸው ተቆጥበው፣ እንደዜጋ አገር እንዴት እናሳድግ የሚለውን አንደበታቸውን መስማት እንፈልጋለን፡፡ ‹‹ኧረ ኢኮኖሚው እንዲህ ሆነ›› ከማለት በላይ የተሻለ ፖሊሲ ይዞ በመቅረብ የሚከራከሩበት ጊዜ እየናፈቀን ነው፡፡

ከፖለቲካ ሹክቻው ባሻገር ትኩረታችን ወደ ኢኮኖሚው እንዲሰበሰብ የግድ ይላል፡፡ ይህንን የማድረግ ኃላፊነት ደግሞ የአንድ የመንግሥት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ሁሉም የበኩሉን ያውሳ፡፡ ምክንያቱም አሁን ከፖለቲካው ትኩሳት በበለጠ ሊያሳስበን የሚገባው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት የማይቀመስ እየሆነ ነው፡፡ ለኢኮኖሚያችን ተገቢውን ትኩረትና ወደፊት ሊያራመድ የሚችል ፖሊሲ ቀርጾ ወደ ሥራ ካልተገባ፣ ሊከሰት የሚችለው ችግር ቀላል አይሆንም፡፡ ለምሳሌ እንኳን ሰሞኑን ይፋ በተደረገው መረጃ የኅዳር ወር የዋጋ ግሽበት ከ20 በመቶ በላይ መስፈንጠሩ ነው፡፡ ‹‹ጎበዝ ነገሩ እንዴት ነው?›› ብሎ ከመግለጽ በላይ ይህንን ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ሊገታ የሚችል ሥራ ይጠይቀናል፡፡ ይህ ወቅታዊና በቶሎ መፍትሔ የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑንም መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ስለዚህ አሁን ሁሉም ፊቱን ወደ ሥራ መልሶ ገበያውን ማረጋጋትና ኢኮኖሚው በምቹ ሁኔታ እንዲራመድ ማድረግ ያሻል፡፡ ይህ ካልሆነ በቀዳሚው ዓመት የዋጋ ግሽበቱ 15 እና 16 በመቶ ሲደርስ ጉድ ብለን ሳናበቃ፣ አሁን ከ20 በመቶ በላይ ሆነ ሲባል መጪውስ ጊዜ? እንድንል እያደረገ ነውና ከዚህ በኋላ የመንግሥት ዕርምጃ ይህንን ጉዳይ በማከም የነገን ሥጋት መቀነስ መሆን አለበት፡፡ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ከታሰበ አሁን በአግባቡ መሥራት ግድ የሚል መሆኑ በመገንዘብ ይቺን አጋጣሚ መጠቀሙ መልካም ነው፡፡

እንደ ሸማች የዋጋ ንረት ያሳስባል፡፡ ይህንን ማፍታት ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደተባለው ትኩረቱን ኢኮኖሚው ላይ አድርጎ መሥራት የግድ ነው፡፡ ከኖቤል ሽልማቱ ማግሥት ወይም ከዚህ በኋላ የፖለቲካው ሽኩቻ ከሚወስድብን ጊዜ ቀነስ በማድረግ ኢኮኖሚውን መታደግ ይኖርብናል፡፡ ስለኢኮኖሚያችን በማውራትና ክርክር በማድረግ አገርና ሕዝብን ማሻሻል እንዲለምድብን እንመኛለን፡፡ ለማንኛውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ለማድረግ ምክንያት ስለሆኑ እናመሰግናለን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት