Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመገናኛ ብዙኃን የአየር ንብረት ለውጥን በአፅንኦት እንዲዘግቡ ጥሪ ቀረበ

መገናኛ ብዙኃን የአየር ንብረት ለውጥን በአፅንኦት እንዲዘግቡ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥጋት የሆነውና በተለይ አፍሪካንና ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ያላቸውን አኅጉራት እያጠቃ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ፣ በየአገሩ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በአፅንኦት እንዲዘግቡ ጥሪ ቀረበ፡፡

በፈረንሣይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ (ሲኤፍአይ) አዘጋጅነት ‹‹የአየር ንብረት ቀውስ አዘጋገብ፣ የመገናኛ ብዙኃን ድርሻና ተግዳሮቶች›› በሚል ርዕስ ከታኅሳስ 6 እስከ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚካሄደው አኅጉራዊ ጉባዔ ላይ እንደተገለጸው፣ የአየር ንብረት ለውጡ ምሥራቅ አፍሪካን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ተፅዕኖውን እያሳደረ ቢሆንም፣ በመገናኛ ብዙኃን እያገኘ ያለው ሽፋን አናሳና የሚፈለገውን መልዕክት የሚያስተላልፍ አይደለም፡፡

በአፍሪካ የሲኤፍአይ ዳይሬክተር አን ሶፊ እንዳሉት፣ የአየር ንብረት ለውጥ አሁንም በአግባቡ እየተዘገበና ትኩረት እያገኘ አይደለም፡፡ በተወሰነ ደረጃ እያገኘ የሚገኘው ሽፋንም የአየር ንብረት ለውጡ እያደረሰ ያለውን ዙሪያ ገብ ችግር ለመድረስ አላስቻለም ብለዋል፡፡

- Advertisement -

ከሁሉም በተለየ ሁናቴ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ መሆኗን በመጠቆምም የምግብ ዋስትና፣ የውኃና የጤና ተደራሽነት፣ ስደትን የማስተዳደርና በየቀጣናው የሚከሰቱ ግጭቶችንና ጦርነቶችን የመፍታት ችግር በሚስተዋልባት አፍሪካ፣ ከእነዚህ የከፋ ውድመትን ለሚያስከትለውና መኖርን አደጋ ላይ ለሚጥለው የአየር ንብረት ለውጥ ዘገባ ትኩረት መስጠትም ወሳኝ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሁሉም ጋዜጠኞች በየአገራቸው በተለያዩ አጀንዳዎች እንደሚጠመዱ፣ ሆኖም የአየር ንብረት ለውጥ በድንበር ሳይገደብ ሁሉንም የሚጎዳ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የሚዲያ ኤንድ ኮሙዩኒኬሽንስ ሴንተር (ሪፖርተር ጋዜጣ) ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው ጋዜጠኞች በፖለቲካ፣ በግጭትና በሌሎች አጀንዳዎች ይበልጥ እንደሚሳቡና ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ እሳት፣ ጎርፍና ያልተጠበቀ የተፈጥሮ አደጋዎችን እያስከተለ የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት እንደሚሻ ገልጸዋል፡፡

ዝናብ ባልተጠበቀበት ወቅት መዝነቡንና ወንዞች መድረቅ በማይገባቸው ወቅት መድረቃቸውን እንደ አብነት ያነሱት አቶ አማረ፣ ለዚህ ዋና ምክንያቱ  ምንድነው? እንዴትስ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል? የሚሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከልና ከጅምሩ ችግሩ እንዳይጎላ መሠራት ስላለባቸው ሥራዎች ቢነገርም፣ በአግባቡ አለመተግበሩን በማስታወስም ጋዜጠኞች እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን እየተከሰቱ ካሉ ነባራዊ ጉዳቶች ጋር በማጣጣም ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያና ከኡጋንዳ የተውጣጡ ጋዜጠኞች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾችና በዘርፉ የሚሠሩ ተቋማት ተወካዮች በተሳተፉበት ጉባዔ፣ የአየር ንብረት ለውጥ አዘጋገብ ላይ ሥልጠናም ተሰጥቷል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋዜጠኞች አንድ ላይ መሠልጠናቸው ልምድ እንዲለዋወጡ ያስችላል ያሉት አቶ አማረ፣ ለጋዜጠኞች የተሰጠው ሥልጠናም ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት እንዲሰጡ ግንዛቤ ያስጨብጣል ብለዋል፡፡

ሲኤፍአይ በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ካዘጋጀው ጉባዔና ሥልጠና በተጨማሪ፣ እ.ኤ.አ. ከ2020 በኋላ ተግባራዊ የሚሆን የ18 ወራት ሥልጠና ለጋዜጠኞች ማመቻቸቱን አስታውቋል፡፡

ዳይሬክተሯ ሶፊ እንደሚሉት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ ፍሪላንስ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች በሲኤፍአይ ድረ ገጽ በተቀመጠው የማመልከቻ ቅጽ መመዝገብ ይችላሉ፡፡ ከኬንያ፣ ከኢትዮጵያና ከኡጋንዳ የተመረጡ 12 መገናኛ ብዙኃን ዕድሉን ያገኛሉ ብለዋል፡፡

ማመልከት የሚችሉት መገናኛ ብዙኃን ቢያንስ አንድ ሴት ጋዜጠኛ ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን፣ ከእያንዳንዱ መገናኛ ብዙኃን ተቋምም ሁለት ሁለት ጋዜጠኞች ለ18 ወራት በሚቆየው ሥልጠና ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ የማመልከቻ ጊዜውም እስከ ታኅሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሆነ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...