Sunday, June 23, 2024

በችግር የተተበተውን ኢኮኖሚ በሰመመን መርፌ ማቆየት አይቻልም!

ባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ የገንዘብ ሚኒስትሩ የዚህን ዓመት የበጀት ረቂቅ ይዘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርቡ፣ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በመቀዛቀዙ ለነገ የማይባል የመፍትሔ ዕርምጃ እንደሚያስፈልግ ማስገንዘባቸው ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አራት ዓመታት በተከሰቱ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አለመረጋጋቶች ሳቢያ የተፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን ክፍተት፣ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስረድተው ነበር፡፡ በመጀመርያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አምስት ዓመታት ከአማካይ 10.1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ተወርዶ ለሦስት ዓመታት በአማካይ 8.6 በመቶ መመዝገቡን፣ በ2010 በጀት ዓመት ደግሞ ወደ 7.7 በመቶ ማዘቅዘቁን መጠቆማቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ ሁሉ ችግር በተነገረባቸው ዓመታት የፀጥታ መደፍረስ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣት፣ የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ መገታት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የመቆም ኃይል መቀዝቀዝ፣ የቱሪዝምና የአገልግሎት ዘርፉ መዳከም፣ የኤክስፖርት ገቢ በአስደንጋጭ ሁኔታ ማሽቆልቆል፣ ፅኑ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፈጠር፣ የአገሪቱ የውስጥና የውጭ ብድር ከመጠን በላይ መሆን፣ የምርትና የምርታማነት በአሳሳቢ ሁኔታ መቀነስ፣ ወዘተ ኢኮኖሚውን የተፈታተኑት ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች ከሰላምና መረጋጋት መጥፋት ጋር ብቻ ካያያዝናቸው ስህተት ነው፡፡ አንዱና ዋናው ትልቁ ምክንያት የመንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ከመጠን በላይ ተዋናይ መሆኑ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ መሆን የሚገባውን የግሉን ዘርፍ ሚና የነጠቀው መንግሥት፣ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ችግር በመፍጠሩ አገሪቱን ማጥ ውስጥ ከቷታል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ቀደም ሲል የተፈጸሙ ስህተቶች ለማረምና ትክክለኛ አቅጣጫ ለማስያዝ፣ የኢኮኖሚ ሪፎርም እንቅስቃሴ ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የመጀመርያ ሥራ የተወላገደውን አቃንቶ መስመር ማስያዝ ነው፡፡ ልማታዊ መንግሥት በተባለው ሞዴል ኢኮኖሚው ውስጥ በርካታ የተዝረከረኩ ነገሮች ታይተዋል፡፡ የአገሪቱን ሀብት ያላንዳች እንቅስቃሴ ሲበሉ የነበሩ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ብዙ ነበሩ፡፡ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ በመሠረቱ የግሉን ዘርፍ ማብቃት ቢሆንም፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የግሉ ዘርፍ ባይተዋር ተደርጎ መንግሥት የሁሉም ነገር አድራጊ ፈጣሪ በመሆን የአገር ሀብት መጫወቻ ሆኗል፡፡ በዘፈቀደ የሚመራ ኢኮኖሚ ተቆጣጣሪና  ጠያቂ ስለሌለበት፣ ውጤቱ ከኪሳራ አልፎ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ዕዳ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ካለፉት ስህተቶች በሚገባ በመማር፣ አገሪቱን ከችግር ውስጥ ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ ለእዚህም አሉ የተባሉ ባለሙያዎችን በሚገባ መጠቀም፣ ለፖሊሲ ግብዓት የሚረዱ ምክረ ሐሳቦችን ማሰባሰብ፣ ከውጭ የሚገኙ ተሞክሮዎችን እንደ ወረዱ ከመቀበል ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ማጣጣም፣ ከንድፈ ሐሳባዊ ትንተናዎች በተጨማሪ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን መገንዘብና አዋጭ የሆኑ የመፍትሔ መንገዶችን ማፈላለግ ጠቃሚ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ችግሮች ፋታ አይሰጡምና፡፡

መንግሥት በጀመረው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሦስት መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት አድርጓል፡፡ እነሱም የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የዘርፍና የመዋቅራዊ ችግሮች ናቸው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚው ችግሮች ተብለው የተዘረዘሩት ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የብድር ዕዳ ጫና፣ ወዘተ ሲሆኑ በሦስት ዓመታት ውስጥ ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተመልክቷል፡፡ መንግሥት ለኢኮኖሚው መዛባት ምክንያት ናቸው ያላቸውን መሬት ላይ ያሉ ችግሮችን በሚገባ አውቋቸው ከሆነ መልካም ነው፡፡ ችግሮቹንም ለመፍታት በቁርጠኝነት ለመሥራት መዘጋጀት ብቻ ሳይሆን፣ በጥናት የተደገፈና በባለሙያዎች የታገዘ ዕቅድ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎችና ድጋፍ ሰጪዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ከፍ ለማድረግ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ድጋፍ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት መበረታታት አለበት፡፡ የሚገኘውም ድጋፍ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆን እንዳለበት ዕሙን ነው፡፡ የዓለም ባንክ፣ አይኤምኤፍ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና የመሳሰሉት ተቋማትና ሌሎች ለጋሾችና አበዳሪዎች በዚህ የችግርና የጭንቅ ጊዜ መገኘታቸው እንደ መልካም አጋጣሚ መታየት አለበት፡፡  የሚደረጉ ስምምነቶችም በዚህ መንፈስ ሊታዩ ይገባል፡፡ የድጋፎቹ ጠቀሜታ ብቻ ሳይሆን የጎንዮሽ ጉዳቶችም በጥንቃቄ መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ ጉዳቶቹ በተቻለ መጠን በጣም ዝቅተኛ ሆነው የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን መጠንከር ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚው ችግሮች ሊወገዱ የሚችሉት ብቁና ንቁ ሆኖ መገኘት ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ኢኮኖሚውን ከገባበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በአስተማማኝ ለመሳብ የሚያስችል ዓውድ መፍጠር፣ ጥብቅ የሆነ የገንዘብና የበጀት ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ፣ ለአበዳሪዎች አስተማማኝ ደንበኛ መሆን የሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት፣ ከኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥትን ተዋናይነት የሚቀንሱ ትክክለኛ ዕርምጃዎችን መውሰድ፣ በአጭርና በረዥም ጊዜ ሒደት የሚከናወን ትክክለኛ የፕራይቬታይዜሽን ሥርዓት መዘርጋት፣ ቅጥ ያጣ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርና ተጠያቂነት የሌለበት የብድር አሰጣጥን ፈር ማስያዝ፣ የብሔራዊ ባንክን ሪፎርም በማካሄድ መሥራት የሚገባውን መለየት፣ የብር ምንዛሪ ተመን ማስተካከያን ጥንቃቄ በተሞላበት ሥርዓት ማከናወን፣ የሥርዓተ አልባው የግብይት ሥርዓት ውጤት የሆነውን የዋጋ ግሽበት መግታትና የመሳሰሉት ተግባራት የግድ ናቸው፡፡ እነዚህ ተግባራት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ትጋት ይጠይቃሉ፡፡ የውጭ እጅ ጠምዛዦች ወሳኝ የሚባሉ የልማት ድርጅቶችን በፕራይቬታይዜሽን ስም ጠራርገው እንዳይወስዱ፣ የመንግሥትን የኢንቨስትመንት ድርሻ በመቀነስ ስም አትራፊ የሚባሉ ተቋማትን እንዳይነጥቁና ባዶ እንዳያስቀሩ ጥንቃቄ ያሻል፡፡ የብድር ዕዳ የመክፈያ ጊዜን ቻይና እንዳራዘመችው ሁሉ፣ ሌሎች አበዳሪዎችም ኢኮኖሚው በእግሩ እስኪቆም እንዲታገሡ ማግባባት መቻል ያስፈልጋል፡፡ የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት ይገባል፡፡ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ እየተባለ ያለ ዕቅድ የሚከናወኑ ድርጊቶች ቆመው፣ ተቋማዊ አሠራር መኖር አለበት፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከገባበት አዘቅት የሚወጣው በእሳት ማጥፋት ዓይነት አሠራር አይደለም፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከገባበት አጣብቂኝ ማውጣት ይቻላል፡፡ ለዚህም ብሩህ ተስፋ እንዳለ በርካታ አመላካቾች አሉ፡፡ ነገር ግን የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ሚና እንዳለው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ከግጭት ነፃ መሆን አለበት፡፡ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውረው የመኖርና የመሥራት መብታቸው ሊከበር የግድ ነው፡፡ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ፀር የሆኑ ሕገወጥ ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ የቱሪዝም ፍሰቱ አስተማማኝ መሆን አለበት፡፡ ምርቶችና አገልግሎቶች ሳይስተጓጎሉ መቅረብ አለባቸው፡፡ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ የሆኑ ችግሮችን የማስወገድ ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት ሲሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋም አስተዋጽኦውን ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ ሰላም በሌለበት ዕድገት አይታሰብም፡፡ ለዚህም ሲባል ለመጪው ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ምርጫው ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እንዲሆን አርዓያ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ኃላፊነትን መወጣት ከተቻለ ኢኮኖሚው ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ወጥቶ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡ ሕዝቡን ከዋጋ ግሽበት ለመታደግና አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሠረት ለመጣል ሰላም ወሳኝ ነው፡፡ ለሰላም ሲባል መስዋዕትነት መክፈል ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ይህንን ማድረግ አለመቻል በአገር ላይ አደጋ መደቀን ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል እንደማይቻል መታወቅ አለበት፡፡ ካሁን በኋላ በችግር የተተበተበውን ኢኮኖሚ በሰመመን መርፌ ማቆየት አይቻልም!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...