Thursday, February 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር በሶማሌ ክልል ታሳሪዎችንና እስር ቤቶችን ጎበኙ

የሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር በሶማሌ ክልል ታሳሪዎችንና እስር ቤቶችን ጎበኙ

ቀን:

በሶማሌ ክልል መስተዳድር ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ያለው ተነሳሽነት እጅግ የሚያበረታታ መሆኑን፣ በጅግጅጋ ከተማ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (/ር) አስታወቁ፡፡ በጉብኝታቸው ከክልሉ መስተዳድር ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው ከመወያየታቸው በተጨማሪ እስር ቤቶችንና ታሳሪዎችን ጐብኝተዋል፡፡

በክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተሠርቶ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን አዲስ ማረሚያ ቤት ሲጎበኙ፣ እጅግ ለተጨናነቀው በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ ለሚገኘው ፋፈን ማረሚያ ቤት መጣበብ መፍትሔ የሚሰጥና ለታራሚዎች ጤናማና ሰብዓዊ አያያዝ የሚረዳ ትክክለኛ ዕርምጃ ነው ማለታቸውን ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በጅግጅጋ ከተማ መስተዳድር ፖሊስ ሕፈት ቤት ሥር የሚገኘው በተለምዶ ‹‹ሀቫና›› በመባል የሚጠራው እስር ቤት የንፅህና ደረጃና የእስረኞች አያያዝ ሊሻሻል ስለሚገባበት ሁኔታ ከኃላፊዎቹ ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን፣ ኮሚሽኑም አፈጻጸሙን በቅርበት እንደሚከታተል በመግለጫው ተገልጿል፡፡

የተወሰኑ ታሳሪዎች በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፣ እንዲሁም ለኮሚሽኑም ከቀረቡ አቤቱታዎች በፖሊስ አካላዊ ጥቃትና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንደተፈጸመባቸው ስላሳወቁ፣ ኮሚሽኑ ሥልታዊ ክትትሉን ይቀጥላል ተብሏል፡፡ እስካሁን በተገኘው መረጃ መሠረት አልፎ አልፎ የሚከሰት ኃይል የመጠቀምና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ሊኖር እንደሚችል ከመጠቆም ያለፈ፣ ሥልታዊ የሆነ ወይም የተስፋፋ የፖሊስ ድብደባ እየተፈጸመ ነው የሚያሰኝ አይደለም ተብሏል፡፡

ነገር ግን አዲስ መብራቱ የተባለ ወጣት ተማሪ በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኃላ ተፈጽሞበታል በተባለው ድብደባ በደረሰበት ጉዳት ሆስፒታል ገብቶ ሕይወቱ ማለፉ የተገለጸ መሆኑ፣ እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ ክስተት በመሆኑ ኮሚሽኑ ጉዳዩን በዝርዝር በማጣራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

እንዲሁም ሐምሌ 28 ቀን 2010 .. ተከስቶ በነበረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሕክምናና መልሶ መጠገንና ከጐረቤት ክልሎች የተፈናቀሉ ሰዎችን መብት አጠባባቅ በተመለከተ፣ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ለረጅም ዓመታት ከኖሩበት የመንግሥት ቤቶች ተገድደው የመልቀቅ ችግሮች የገጠማቸውን ሰዎች መብት አጠባበቅ በተመለከተና ተዛማጅ ጉዳዮች ኮሚሽኑ ከመስተዳድሩ ጋር ስለመፍትሔ አቅጣጫዎች በመወያየት አበረታች ምላሽ መገኘቱንና አፈጻጸሙንም በቅርበት እንደሚከታተል አስረድታል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት መሠረት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሰለባ ለነበሩ ሴቶች የክልሉ መስተዳድር ያደረገው የገንዘብና የሞራል ድጋፍ የሚመሠገን ዕርምጃ መሆኑን፣ ለቀሪዎቹም ሰለባዎች ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሰጡት ቃል የሚያበረታታ መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

‹‹በተለይ የክልሉ ክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ዑመር  ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና መስፋፋት፣ እንዲሁም የጥሰት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መጠገንና መልሶ መቋቋም ያላቸው በተግባር የሚታይ ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት እጅግ የሚያበረታታና ለሌሎች የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ባለሥልጣናት በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፤›› ነው ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ የሚታየውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ለማሻሻል አስፈላጊ ከሆኑ ዕርምጃዎች ውስጥ የፍትሕ አስተዳደርና የፀጥታ ጥበቃ አካላትን ብቃት መገንባት፣ ለዳኝነት አስተዳደር ልዩ ትኩረት በመስጠት በሙያዊ ብቃትና ሥነ ምግባር ላይ የተመሠረተ አቅም ማጎልበት፣ የግንዛቤ ማስፋፋትና ተጐጂዎችን መልሶ መጠገንና ማቋቋም ይጨምራል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከክልሉ መስተዳድር ለተደረገለት ድጋፍና መልካም የሥራ ግንኙነት ምሥጋናውን ገልጾ፣ ከላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ሁሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብሮ እንደሚሠራና የክትትል ሥራውን የሚቀጥል መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ማስተካከያ

በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም...

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...