Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ግብዓት አቅራቢ የሚናፍቀው የጥርስ ሕክምና

የጥርስ ሕመም በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ አንዱና ዋነኛው የአፍና የጥርስ ንፅህና ካለመጠበቅ እንደሆነ በዘርፉ የሚሠሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በአብዛኛው ሰዎች ላይ የሚከሰተው የጥርስ ሕመም ከጥርስ ኢንፌክሽን፣ ከመበስበስ፣ ፊት አካባቢ ከሚደርስ አደጋ፣ ከድድ ኢንፌክሽን፣ ከጥርስና ከአፍ አካባቢ የንፅህና ጉድለት፣ ከስኳር ሕመም ሊነሳ ይችላል፡፡ ጥርስን ጨምሮ የተለያዩ የሰውነት አካላት ላይ በየጊዜው ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ብዙም አይደለም፡፡ በዚህም ሳቢያ አብዛኛው ሰዉ ጉዳቱ ሥር ከሰደደ በኋላ ወደ ጤና ተቋማት ስለሚሄድ ለሕክምናው የሚያወጣው ወጪ ከፍ ያለ ነው፡፡ በቅርቡ የግል ሕክምና ተቋማት ለማኅበረሰቡ ካደረጉት የነፃ ሕክምናና የጤና ምርመራ አንዱ በጥርስ ሕክምና ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ከእነዚህም የዶክተር እመቤት የጥርስ ሕክምና ተቋም ይገኝበታል፡፡ በነፃ ሕክምና አገልግሎት ዙሪያና ስለጥርስ ሕመምና ተያያዥ ጉዳዮች የተቋሙን ሐኪም ዶ/ር ሙሉጌታ ግርማይን ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በጤና ኤግዚቢሽኑ ላይ ምን ዓይነት የሕክምና አገልግሎት ስትሰጡ ነበር?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- በኤግዚቢሽኑ ይጠበቅብን የነበረው ነፃ ምርመራ ማድረግ ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ተቋሙ በራሱ ተነሳሽነት ከምርመራም አልፎ የጥርስ ንፅሕና መጠበቅ (ማጠብ) እና የምክር አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ በጊዜው ከ120 በላይ ሰዎች መዝግበን ለሕክምና አገልግሎት ይመች ዘንድ ጤና ተቋሙ መጥተው አገልግሎቱን እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ ለዚህም ሲባል ለሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ ተከፍሎ ጥርስ ማጠብ፣ መንቀል፣ ማሰርና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች በነፃ ሰጥተናል፡፡ የሥነ ልቦና ሕክምናን ሳይጨምር ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አውጥተናል፡፡ ነገር ግን ዓላማው ለተቋሙም ሆነ ለአገር እጅግ ጠቃሚ ስለሆነ በደስታ ነው ሕዝቡን ያገለገልነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገልግሎቱን ያገኙት ሰዎች በምን መሥፈርት ተመረጡ?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ምንም ዓይነት መሥፈርት አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ቅድሚያ የተሰጣቸው አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ቀድመው ለመጡት ነው፡፡ በዚህም ከአቅማችን በላይ የሆነ የሰው ብዛት ነበር፡፡ ዐውደ ርዕዩ ካለፈ በኋላም የመዘገብናቸውን እያስተናገድን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በሙያዎት አሥር ዓመታትን እንዳገለገሉ ነግረውናልና አብዛኛው ሰው ምን ዓይነት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋሙ ይመጣል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- አብዛኛው ጥርስ ለማሳጠብ፣ ለማስተካከል ከአፍ ጠረን ጋር በተያያዘ ወደ ተቋሙ ይመጣሉ፡፡ ጥርስ ማስነቀል፣ የድድ ሕክምና እነዚህን ጨምሮ በተቋሙ ሰባት ዓይነት የተለያዩ አገልግሎቶችን በጥራት ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የጥርስ ሕመም በምን ሊከሰት ይችላል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- በአብዛኛው የጥርስ ንፅህና ካለመጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን በጥርስ መቦርቦር፣ በጥርስ መጥቆር፣ በጥርስ ኢንፌክሽን ጥርሳችን ሊታመም ይችላል፡፡ ይኼ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን የጥርስን ንፅህና መጠበቅና በየጊዜው የጥርሳችንን በየጊዜው ወደ ጤና ተቋማት እየሄዱ የጥርስን ሁኔታ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቅድመ ጥንቃቄዎቹ ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- በቀን ሁለቴ ጥርሳችንን ማፅዳት አንደኛው ጥንቃቄ ነው፡፡ ይህን ስናደርግ ለጥርሳችን ብቻ ሳይሆን መጥፎ የአፍ ጠረንን ለመከላከል ጭምር ነው፡፡ ጥርስና ምላስን በለስላሳ የጥርስ መፋቂያ (ብሩሽ) እና ፍሎራይድ ባለው የጥርስ ሳሙና ማፅዳት ጥርስ ውስጥ ያለውን ምግብና ባክቴሪያ ያፀዳል፡፡ አፍ 37 ዲግሪ ሙቀትና ዕርጥበት ያለው በመሆኑ በባክቴሪያና በምግብ የተሞላ ነው፡፡ ይህ ሲከማች ደግሞ ድድ ከመጉዳቱ ባሻገር ለመጥፎ የአፍ ጠረን ምክንያት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሌሊቱን የተጠራቀመውን ምግብና ባክቴሪያ ጠዋት በጥርስ መፋቂያና ሳሙና መታጠብ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህን ተግባር ከመተኛታችን በፊት ማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በአፋችን በተለይም ፊልሞች ላይ የምናያቸው ዓይነት አቦራረሽ ተገቢ አይደሉም፡፡ በፍጥነትና በኃይል ሲፍቁ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን ለጥርሳችን እጅግ አደጋ ነው፡፡ ጥርስ ሲፀዳ እንደ እንቁላል ቅርፊት እንዳይሰበር የምናደርገውን ጥንቃቄ ለጥርስም ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም በለስላሳ የጥርስ መፋቂያ መፋቅ ተገቢ ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ ተግባራዊ የማይደረገው በክር ጥርስን ማፅዳት ነው፡፡ በክር ማፅዳት የሚያስፈልገው ከጥርስ መፋቂያ ያመለጡ ምግቦችን በቀላሉ ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ይህንን ካደረግን ከጥርስ ንፅሕና ከመጠበቅ በበለጠ ከመቦርቦርና ከአፍ ጠረን ራሳችንን በቀላሉ መጠበቅ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- በተቋሙ ከጥርስ ሕክምና ውጪ ምን አገልግሎት ይሰጣል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- የሥነ ልቦና ሕክምና ወይም የምክር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህም የሚሆነው አንዳንድ ሰዎች ምንም የአፍ ጠረን ሳይኖርባቸው ራሳቸው ከማኅበረሰቡ የሚያገሉ ወደ እኛ መፍትሔን ፈልገው ይመጣሉ፡፡ ታዲያ እነዚህን ሰዎች የሥነ ልቦና ምክር በመስጠት አፋቸው ፍፁም ጤነኛ መሆኑን እናስረግጥላቸዋለን፡፡ ሌላው ከሕክምናው በተጨማሪ የጥርስ አቦራረሽ (መፋቅ) እንዴት መሆን እንዳለበትና ራሳቸው ለጥርስ ሕመም ከሚያጋልጡ ነገሮች መከላከል እንዳለባቸው እናስረዳቸዋለን፡፡ የአፍ ጠረን ከንፅሕና አለመጠበቅ ብቻ ላይከሰት ይችላል፡፡ ለምሳሌ የስኳር ሕመምተኞች የድድ ሕመም፣ በሽታ ሊያመጡ የሚችሉ ባክቴሪያዎች በአፍና በአንጀት ክፍሎች ውስጥ መራባት፣ መድኃኒት (አፍን የሚያደርቁ መድኃኒቶች)፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የጉበት በሽታ፣ የሆድ ድርቀትና በሌሎች ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡፡   

ሪፖርተር፡- ከጥርስ ሕክምና ጋር በተያያዘ ብዙ ሰዎች ተቋማቱ ዋጋቸው እንደማይቀመስ ነው የሚናገሩት እርስዎ በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- የገነነ ስም ስላለው እንጂ ያን ያህል የተጋነነ ዋጋ አይደለም ያለው፡፡ ከሚሰጠው አገልግሎት አንፃር እንዲያውም አናሳ ክፍያ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ ጥርስ ለማሳጠብ 1,500 ብር ነው የምናስከፍለው፡፡ በሌሎችም የሕክምና ተቋማት ተመሳሳይ ነው፡፡ ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና መሣሪያና አገልግሎት ስለሚሰጥ የተጋነነ ነው ሊባል አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በኅብረተሰቡ የሚሰጥ አስተያየት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- በኅብረተሰቡ የሚሰጠው አስተያየት እስካሁን ጥሩ የሚባል ነው፡፡ አንዳንዴ እንደዚህ ብታደርጉ፣ ብታስተካክሉ ይላል፡፡ አንዳንድ ሰው ደግሞ ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ አላስፈላጊ ነገር ቢናገርም ከቻልን ለማስረዳት እንጥራለን፣ ለዚህ ነው የምክር አገልግሎት የምንሰጠው፡፡

ሪፖርተር፡- በተለይ የጥርስ ሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ላይ ወቀሳ የሚያነሱ አሉ?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- መገልገያ መሣሪያዎች በአብዛኛው ከውጭ ነው የምናስመጣው፡፡  በዚህም ብዙዎች ሊመሰክሩለት የሚችል ተቋም ነው፡፡ እንዲያውም ቅድም ውድ ነው ላልሺው እያንዳንዱ መሣሪያ ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑም ጭምር ተገልጋዮች ያለ ምንም ሥጋት ታክመው እንዲወጡ የመሣሪያዎቹ ጥራት ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ የጥርስ ሕክምና አገልግሎት የሚውል ግብዓት አቅራቢ ድርጅት በብዛት የለም፡፡ ቢኖርም ቶሎ የሚያልቅ፣ አንዱ ደግሞ ደረጃውን (ጥራቱን) የጠበቀ ካለመሆኑ ከውጭ ለማስመጣት እንገደዳለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በጤና ተቋማት ኤግዚቢሽን ቀጣይ ተሳትፎ ይኖራችኋል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ያለ ምንም ጥርጥር እንቀጥላለን፡፡ ኃላፊነታችንን የምንወጣበት መድረክ በመሆኑ እስከ መጨረሻው የምናገለግል ይሆናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...

የሳባ መንደር

ሼባ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሼባ/ሳባ የጉዞ ወኪል በ1960ዎቹ የተመሠረተና በርካታ እህት ኩባንያዎችን ያፈራ ነው፡፡ ሼባ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ...