Tuesday, July 23, 2024

ዘላቂ መፍትሔ የሚሻው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግጭት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ሲከሰቱ የነበሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች፣ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕወት ሲያናጉና ሲያውኩ እንደነበሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በእነዚህ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ምክንያት በደረሰው የሰላም ዕጦት የአገሪቱ ኢኮኖሚም አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡

ከኢኮኖሚው ባሻገር ትምህርት በተደጋጋሚ ተቋርጧል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የተማሪዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ዘለዓለማዊ የሆነ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በርካቶችም ከፍተኛ ለሆነ የሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የነበሩ ግጭቶች የሁሉንም ዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮና እንቅስቃሴ ሲያስተጓጉሉ የነበሩ ቢሆንም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ከአጠቃላይ የሰላም ዕጦትና ደኅንነት ሥጋት በባሰ ሁኔታ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች ለወላጆች የሰቀቀን፣ ለተማሪዎች ደግሞ የደኅንነት ሥጋት ምንጭ ሆነዋል፡፡ 

በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል እየተፈጠረ ያለው የተማሪዎች ግጭት ከፍተኛ የሥጋት ምንጭ ከመሆን አልፎ፣ ነገን ጥሩ ለማድረግ አልመው በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እየተማሩ የነበሩ ተማሪዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡

በዚህም ምክንያት ወላጆች ልጆችን ወደ ዩኒቨርሲቲ መላክ ማለት ወደ ሞት የመሸኘት ያህል እየቆጠሩ ነው፡፡ ለዚህም መንግሥት ቁርጠኛ የሆነ መፍትሔ አለማበጀቱ፣ እንዲሁም አስቸኳይ የዕርምት ዕርምጃ አለመውሰዱ ክፉኛ እያስተቸው ነው፡፡

የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችም በተደጋጋሚ ወደ መገናኛ ብዙኃን አደባባይ በመውጣት ከግጭቶቹ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የተማሪዎች ሕይወት ማለፍን፣ የአካል መጉደልን፣ እንዲሁም የሥነ ልቦና ቀውስን ከማውገዝና የተለያዩ ስብሰባዎችን በማድረግ በዘለለ ግን የሚከሰጡት ማብራሪያም ሆነ የመፍትሔ አቅጣጫ እምብዛም ነው በማለት የሚተቹ በርካቶች ናቸው፡፡

የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የዕለት ሁኔታ መረጃዎችንና ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት ጉዳዩን ከማውገዝ ባለፈ የወሰደው ዕርምጃ ቢኖር፣ ከሰኞ ታኅሳስ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የዩኒቨርሲቲዎችን ጥበቃ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ማድረጉ ነው፡፡

ይህም ዳግም ከዚህ ቀደም የነበሩ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ካላስገባ ዘላቂ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ፣ በራሱ የግጭት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ከዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ‹‹ፌዴራል ፖሊስ ከግቢያችን ይውጣ›› በሚል ያሰሙት የነበረው ዓይነት ጥያቄ በማስታወስ ሥጋታቸውን የሚገልጹ አሉ፡፡

ችግሩ ምንድነው?

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚነሱት የተለያዩ ቅርፆች ያሏቸውን ግጭቶች ያጠኑ ግለሰቦች እንደሚገልጹት የግጭቶቹ ምክንያቶች የተለያዩና ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም ቅሉ የአገሪቱ የፖለቲካና ውክልና አወቃቀር ግን ዋነኛው መንስዔ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆኑ ሌሎች ተቋማትን በአገሪቱ ካለው የብሔር ተኮር አወቃቀር ነጥሎ መመልከት እንደማይቻል የሚገልጹት የዘርፉ ጽሑፎች፣ በተለይ በድኅረ 1983 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ በተሰበከው የብሔር ማንነት ዙሪያ ያደጉ፣ የተማሩና ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የቻሉ ተማሪዎችን ከዚህ በከፍተኛ ሁኔታ ከተሰበከው የብሔር ማንነት ማዕቀፍ ውጪ መመልከት እንደማይቻል ይገልጻሉ፡፡

በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ከሌላው ተማሪ ጋር ከመቀላቀልና ከመላመድ ይልቅ ከመጡበት አካባቢ ተማሪዎች ጋር የቀረበና የጠነከረ ቁርኝት እንዲፈጥሩ የሚያደርጋቸው ሲሆን፣ በስህተትም ይሁን ሆን ተብሎ የሚፈጠሩ ጥቃቅን አለመግባባቶችን ከመጡበት የብሔር ማንነት አንፃር በመመልከት ራሳቸውን ለመከላከል፣ ወይም ደግሞ ጥቃት አደረሰብኝ የሚሉትን ወገን በቡድን በመሆን ወደ ማጥቃት ዕርምጃ ሊሸጋገር ይችላል፡፡

ይህ የወገንተኝነት ወይም የቡድን አስተሳሰብ ደግሞ ነገሮችን ከተከሰቱበት ዓውድ ከመመልከት ይልቅ፣ አንድና አንድ ትርጓሜ በመስጠት ለግጭት መባባስ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት የተደረጉ ጥናቶች አመላካች ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል አረጋ ባዘዘውና ሙሉጌታ ነቃ የተባሉ ምሁራን ‹‹Journal of Student Affairs›› ላይ ባሳተሙት ጥናት፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን እንደ ማሳያነት በመውሰድ ባካሄዱት ጥናት ላይ እንደሚገልጹ፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶችን ምክንያት ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ጽሑፋቸው ላይ እንደገለጹት ከሆነ በጥናቱ በተደረገው መጠይቅ መሠረት ያገኙት ውጤት የሚያሳየው ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች መጠናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ነው፡፡

ብሔርን መሠረት ያደረገ ግጭት ማለት ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ሙዚቃዎች አንደኛው ብሔር ከአንደኛ የተሻልኩ ነኝ የሚል አመለካከት ሲሆን፣ በጥናቱ ከተሳተፉት 317 ተማሪዎች የ87 በመቶዎቹ ምላሽ በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግችቶች ምንጩ ይህ መሆኑን ተስማምተዋል፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምንም እንኳን እንደ ስርቆት፣ ተበድሮ አለመመለስና የተለያዩ ዓይነት የግጭቶች መንስዔዎች ቢኖሩም፣ ከፍተኛው የግጭት መንስዔ ግን ከብሔር ማንነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የተማሪዎች ችግሮችን በንግግርና በውይይት የመፍታት ልማድ አለማዳበር ደግሞ ግጭቶች ከማባባስ አንፃር ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል፡፡

በዚህና በሌሎች ጥናቶች ደግሞ የብሔር ማንነትንና የሃይማኖን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች የዩኒቨርሲቲዎች መገለጫ እየሆኑ እንደሆነ ያመላክታሉ፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አስተዋጽኦ ዋነኛው አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁን ወቅት በተቃውሞ ጎራውም ይሆን በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ በርካታ ግለሰቦች የዚህ ሒደት ውጤት መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል፡፡

ምንም እንኳን በተለምዶ ‹‹ያ ትውልድ›› የሚባለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ትግሉ ጥንስስ የሚጀምረው ከዩኒቨርሲቲዎች ቢሆንም፣ አሁን እንዳለው ዓይነት ብሔርን መሠረት ካደረገ የእርስ በርስ የተማሪዎች ግጭት ይልቅ ማጠንጠኛው አጠቃላይ ግፍን፣ ጭቆናን፣ እንዲሁም የነበሩ ሥርዓቶችን መቃወም ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

የአብዛኞቹ የአገሪቱን የትጥቅ ትግል በመምራት ለድል የበቁትም ሆኑ ድል የተመቱት፣ ወይ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ነበሩ ወይም ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ በረሃ የወጡ ናቸው፡፡

ይህን ለንፅፅር በማቅረብም የአሁኑ ፈር የሳተ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግጭቶች ብዙ ከሚጠበቅባቸው ተማሪዎች መንደር የሚመጣ ከመሆኑ ጋር በማስተሳሰር ጉዳቱ በጊዜ ዘላቂ ዕልባት ካልተበጀለት፣ በዩኒቨርሲቲ ብቻ ተወስኖ እንደማይቀር በመሥጋት የአገር ህልውና ላይ የተጋረጠ ፈተና ነው በማለት የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

አሁን በዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ ግጭቶችን ከአጠቃላይ የአገሪቱ ችግሮች ነጥሎ መመልከት እንደማይቻል የሚገልጹ፣ መፍትሔውም በመሠረታዊነት የሰከነ ውይይት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲያወሱ ይሰማል፡፡ ነገር ግን ውይይቱን ማን ይጀምረው የሚለው ጥያቄ ላይ በራሱ ለመግባባት አስቸጋሪ ይመስላል፡፡ ከዚህ አንፃር ችግሮችን በኃይል ለመቆጣጠር ከማሰብ ይልቅ፣ ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን ማበጀት እንደሚጠቅም ያሳስባሉ፡፡

እንዲህ ዓይነት የመፍትሔ ሐሳቦች በሚሠነዘሩበት በዚህ ወቅት ግን መንግሥት እንደ መፍትሔ ከመረጣቸው አማራጮች መካከል፣ በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መወሰኑ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በተለይ ከዚህ ቀደም መንግሥት ለችግሮቹ ሁነኛ መፍትሔ አልሰጠም ለሚል ወቀሳ ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ውሳኔ መሠረት፣ ዩኒቨርሲቲዎች በፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ሥር የሚሆኑ ሲሆን፣ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ‹‹ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዩኒቨርሲቲዎችን የግጭት ማዕከል ለማድረግ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴና እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ለመከላከል ነው፤›› በማለት አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እስካሁን በደረሱ ጥፋቶች እጃቸው ያለበት አካላት ወደ ሕግ እንደሚያቀርብም ተገልጿል፡፡ ሆኖም አሁን ባለው ያገነገነ የብሔርተኝነት ስሜትና አመለካከት ዩኒቨርሲቲዎችን በፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ሥር ማድረጉ ጊዜያዊ መፍትሔ ከመስጠት በዘለለ፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን መቻሉን የሚጠይቁ አልታጡም፡፡

ከዚህ አንፃር በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ምሁራንም ሆኑ አጠቃላይ የአገሪቱን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ ግለሰቦች የውይይት ባህል መዳበርና ልዩነትን በፀጋ የሚቀበል ዜጋ መገንባት ላይ አትኩሮት ተደርጎ ቢሠራ፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡

ይህን ሐሳብ የሚጋሩ የሚመስሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በ2011 ዓ.ም. ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ባልተግባባንባቸው ነገሮች ሁሉ አንጣላም፡፡ ነገ ወይ እንግባባባቸዋለን፣ ያለ በለዚያም ለየባለቤቱ ትተናቸው በተግባባንባቸው እንቀጥላለን፡፡ አንድ አገር የገነባነው በመሠረታዊ ነገሮች ተስማምተን እንጂ፣ በሁሉም ነገር ተስማምተን አይደለም፡፡ ዋናው የመግባባት ሥርዓት ማደራጀት ነው፡፡ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ የሚያስኬድ ባህል መገንባት ነው፤›› በማለት ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታት እንደሚገባ አውስተው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ሌሎች የዘርፉ ምሁራን ውይይት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ከመግለጻቸውና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከአጠቃላይ የአገሪቱ ፖለቲካ ዓውድ አንፃር እንዲህ ያሉ የሰከነና የሠለጠነ ውይይት መድረኮችን ለማዘጋጀት ተነሳሽነቱን ወስዶ ኃላፊነቱን ከተወጣ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተስተዋሉ ችግሮችን የማስወገድ አቅም ከፍተኛ እንደሚሆን ያሳስባሉ፡፡ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱም ይህን ያደርጋል ብለው በተስፋ ይጠብቃሉ፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -