Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፀሐይ ኢንሹራንስ ከ173 ሚሊዮን ብር በላይ ለሞተር ኢንሹራንስ ካሳ ከፈለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፀሐይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ለደንበኞች ከከፈለው አጠቃላይ ካሳ ውስጥ ከ81 በመቶ በላይ የሚሆነው ለሞተር ኢንሹራንስ ካሳ የተከፈለ መሆኑን አመለከተ፡፡ ዓመታዊ ትርፉም በ13 በመቶ ማደጉን አስታውቋል፡፡  

የኢንሹራንስ ኩባንያው ባለፈው ቅዳሜ ባካሄው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ካቀረበው ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ በሒሳብ ዓመቱ የሞተር ኢንሹራንስን ጨምሮ ለደንበኞቹ የከፈለው አጠቃላይ የጉዳት ካሳ 212.3 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 173.2 ሚሊዮን ብር ለሞተር ወይም ከተሽከርካሪ ጉዳት ጋር ለተያዘው ኢንሹራንስ ሽፋን የተከፈለ ካሳ ነው፡፡ ይህም የተሽከርካሪዎች አደጋ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እያሳረፈ ያለውን ተፅዕኖ ያሳያል ተብሏል፡፡ ኩባንያው በጠቅላላ 212.3 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ለደንበኞቹ ከመፈጸም ባለፈ፣ 168.8 ሚሊዮን ብር በመጠባቂያነት የተያዘ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ከባለፈው ዓመት አንፃር ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ለካሳ ክፍያ የፈጸመው ወጪ 11 በመቶ፣ ለመጠባቂያ የያዘው ደግሞ 16 በመቶ ይበልጣል፡፡ የካሳ ክፍያው በዚህን ያህል ደረጃ ለማደጉ ደግሞ የተሽከርካሪ አደጋና የመለዋወጫ ዕቃዎችና የጉልበት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ያመጣው ድምር ውጤት መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ፀሐይ ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት ከውል ሽያጭ አገልግሎት 300.2 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ አግኝቷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ተገኝቶ ከነበረው ገቢ ጋር ሲነፃፀር የአምስት በመቶ ጭማሪ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፣ ለዓመቱ ከታቀደው ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው የዓረቦን ገቢ ስብጥር ሲታይ የሞተር ኢንሹራንስ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ይህም ከአጠቃላይ የዓረቦን ገቢ 69 በመቶ፣ በሌሎች የኢንሹራንስ ዘርፎች 31 በመቶ፣ ሊያቢሊቲ 13 በመቶ፣ ኢንጂነሪንግ 3.5 በመቶ፣ ማሪን 25 በመቶ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን፣ ቀሪው ከተለያዩ የኢንሹራንስ ዓይነቶች የተገኘ የዓረቦን ገቢ ነው፡፡  

ለጉዳት ካሳ ያዋለው ወጪ ከፍ ያለ ቢሆንም፣ ኩባንያው የሒሳብ ዓመቱን በአትራፊነት መወጣቱን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ኩባንያው ያገኘውን የትርፍ ምጣኔ በተመለከተ የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ‹‹በሒሳብ ዓመቱ በተደረገ ከፍተኛ ጥረት 33.6 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ሊገኝ ችሏል፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡ ይህ የተጣራ ትርፍ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ13 በመቶ ዕድገት ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ውጤት ከነበሩ የተለያዩ ተፅዕኖዎች አንፃር፣ አጠቃላይ የዕድገት ምጣኔ በገቢም ሆነ በሌሎች ሁለንተናዊ ዘርፎች አመርቂ የሚባል መሆኑን የገለጹት ቦርድ ሰብሳቢው አቶ ማንደፍሮ ክርኩ፣ በተለይ በአገሪቱ ከነበረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አንፃር ሲታይ ውጤቱ መልካም ሊባል የሚችል ነው ብለዋል፡፡  የኩባንያውን የተከፈለ ካፒታል ወደ 110.6 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ የሚጠቀመው መረጃ፣ የኩባንያው ሀብት ደግሞ 599.4 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ያመለክታል፡፡ የሀብት መጠኑ ካለፈው ዓመት ሲነፃፀር የ102.3 ሚሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል፡፡  

ኩባንያውን ከኦፕሬሽን የሚያገኘውን ገቢ በኢንቨስትመንት ገቢ ለማገዝ እንደቻለና የራሱ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ እንዲኖረው ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ለግንባታ የሚሆነውን ቦታ በጨረታ መግዛቱን ገልጿል፡፡ በሊዝ ለተረከበው ለዚህ ቦታ 18 ሚሊዮን ብር የሊዝ ቅድሚያ ክፍያ መፈጸሙንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታውን ዕውን ለማድረግ የሕንፃው ዲዛይን ጨረታ ወጥቶ በግምገማ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ባለአክሲዮኖች እንዲገዙት የታሰበው 120 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በሙሉ ለነባር ባለአክሲዮኖች ተሸጦ ስለመጨረሱም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ነገር ግን ለቀጣይ ዓመታት የኩባንያውን የዕድገት ዕቅዶች ማስፈጸሚያ ተጨማሪ ካፒታል እንደሚያስፈልግ የቦርዱ ሰብሳቢ ጠቁመዋል፡፡ ተጨማሪ ካፒታል የሚያስፈልግበት ዋና ዋና ምክንያቶች ብለው ያስቀመጡት የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ፣ የተጎዱ ተሽከርካሪዎች ማከማቻ ቦታ ግዥና ተያያዥ ሥራዎች፣ በቅርቡ ለታሰበው የሕይወት ኢንሹራንስ መነሻ ካፒታል ዋናውን መሥሪያ ቤት ከቅርንጫፎች ጋር የሚያስተሳስር የመረጃ ቴክኖሎጂ ማሰሪያና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ወጪዎች የሚሆን ተጨማሪ ካፒታል የሚያስፈልግ በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ዝቅተኛ የካፒታል መጠንን ያሻሽላል ተብሎ ስለሚጠበቅ፣ የኩባንያውን የካፒታል መጠን ከወዲሁ ማሳደግ አስፈላጊ እንደሚሆን የሥራ አመራር ቦርዱ ያቀረበው ጥያቄም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ፀሐይ ኢንሹራንስ 213 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ የቅርንጫፍ ቁጥሩን 23 አድርሷል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች