Sunday, June 23, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላላቸው

[ለክቡር ሚኒስትሩ ሚስታቸው ስልክ ደወሉላቸው]

 • ጉድ ሆንኩ?
 • ምን ሆንሽ?
 • ቶሎ ድረስልኝ?
 • ምን ተፈጠረ?
 • ጉድ ተሠራሁ ስልህ?
 • ምንድነው ጉዱ?
 • ኧረ እየዞረብኝ ነው፡፡
 • አመመሽ እንዴ?
 • ያቆምኩበት ቦታ የለም፡፡
 • ምኑ?
 • መኪናዬ፡፡
 • . . .?
 • ተሰረቅኩ፡፡
 • ስፖኪዮ ነው የሰረቁሽ?
 • ኧረ ሙሉ መኪናው የለም፡፡
 • . . .
 • መኪናዬን ሰረቁኝ፡፡
 • እንዴት ሊሆን ይችላል?
 • ምንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡
 • ተረጋግተሽ ንገሪኝ፡፡
 • እንዴት ልረጋጋ?
 • . . .
 • ሙሉውን እኮ ነው የወሰዱት?
 • እነማን ናቸው?
 • እኔ ምን አውቃለሁ፡፡
 • ቆይ ተረጋጊ?
 • እንዴት ልረጋጋ?
 • . . .
 • መንግሥት የለም እንዴ?
 • ቆይ እስቲ፡፡
 • በጠራራ ፀሐይ መኪናዬን እየተሰረቅኩ መንግሥት አለ ማለት ይቻላል?
 • እንይዛቸዋለን፡፡
 • ይኸው አጠገቤ ያሉ ሰዎች እኮ ያርዱታል እያሉኝ ነው፡፡
 • ምኑን?
 • መኪናውን ነዋ፡፡
 • ከብት አረግሽው እንዴ?
 •  እውነቴን ነው መኪናውን አወላልቀው ነው የሚሸጡት አሉ፡፡
 • ወይ ጣጣ?
 • አሁን ስሰማ በየቀኑ በርካታ ሰዎች ናቸው የሚሰረቁት አሉ፡፡
 • መኪና?
 • እህሳ?
 • የለንም በይኛ፡፡
 • ለዚያ እኮ ነው መንግሥት አለ ወይ ብዬ የጠየኩህ?
 • የት እንሄዳለን ይኸው እያወራሁሽ አይደል እንዴ?
 • በጠራራ ፀሐይ እያዘረፋችሁን አለን ስትሉ አታፍርም?
 • ተረጋጊ በቃ፡፡
 • ስማ የመኪና ዋጋ እንደጨመረ አልሰማህም እንዴ?
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • ከየት አምጥቼ ነው የምገዛው?
 • ለሁሉም መፍትሔ አለው፡፡
 • እንዴት?
 • በቅርቡ ፈቃዱ በእጅሽ ይገባል፡፡
 • የምኑ?
 • የአስመጪነት ነዋ?
 • የምን አስመጪነት?
 • የመኪና!

[ክቡር ሚኒስትሩ ስብሰባ ላይ ከአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ጋር ተገናኙ]

 • አንተ ማፈሪያ፡፡
 • ምንው ክቡር ሚኒስትር?
 • ዞር በል ከአጠገቤ፡፡
 • ሰላም ይበሉኝ እንጂ?
 • እንደ አንተ ዓይነት ማፈሪያ ሰላም ማለት አልፈልግም፡፡
 • ምን አጠፋሁ?
 • ትንሽ አታፍርም?
 • በምኑ?
 • መቼ ነው የራስህ አጀንዳ የሚኖርህ?
 • ምን ማለት ነው?
 • ሁሌ ተለጣፊ ሆናችሁ ትችሉታላችሁ?
 • . . .
 • በቃ አበል እስካገኛችሁ ድረስ ምንም ነገር ታደርጋላችሁ ማለት ነው?
 • እንደዚህማ ሊሉኝ አይችሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው ዋሸሁ እንዴ?
 • እኛ ለአገር የምንታገል ሰዎች ነን፡፡
 • ኪኪኪ. . .
 • ምን ያስቅዎታል?
 • እናንተስ የለየላችሁ ማፈሪያዎች ናችሁ፡፡
 • አይሳደቡ እንጂ?
 • ስማ እንኳን ለአገር ለቤተሰባችሁም አትታገሉም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ትንሽ ገንዘብ ብታገኙ ቤተሰቦቻችሁን ትክዳላችሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ፀጉራችን የሸበተው እኮ ለአገር ስንታገል ነው፡፡
 • ምን?
 • እናንተ ሥልጣን ላይ የወጣችሁት በእኛ ትግል አይደል እንዴ?
 • ለነገሩ እናንተ ፀሐይ በአገሪቱ የምትወጣው እኛ ስለምንታገል ነው ልትሉ ትችላላችሁ፡፡
 • ሽሙጡ አልበዛም ክቡር ሚኒስትር?
 • በጣም የገረመኝ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
 • ምንድን ነው?
 • እንደዚያ ቁም ስቅላችሁን ሲያበሏችሁ ከነበሩ ሰዎች ጋር መልሳችሁ ስትገጥሙ ህሊናችሁ እንኳን አይወቅሳችሁም?
 • . . .
 • ለነገሩ ምን ህሊና አላችሁ?
 • ትንሽ አላበዙትም ክቡር ሚኒስትር?
 • ለማንኛውም አበል በምን ነበር የተከፈላችሁ?
 • ምን እያሉ ነው?
 • መቼም በዶላር ካልሆነ ከእነሱ ጋር ተመልሳችሁ አትገጥሙም ብዬ ነዋ?
 • . . .
 • ስማ አንድ ነገር ልምከርህ፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • እርግፍ አድርገህ ተወው፡፡
 • ምኑን?
 • ፖለቲካውን፡፡
 • መተዳደሪያዬ እኮ ነው፡፡
 • በቃ አቋቁማ፡፡
 • ምን?
 • ዕድር!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ስልክ ደወለላቸው]

 • ፈዘናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ኧረ እየተቸበቸበ ነው፡፡
 • ምን?
 • መሬት፡፡
 • . . .
 • ይኸው ተተኮሱ እኮ፡፡
 • እነማን?
 • የእኔ ጓደኞች፡፡
 • . . .
 • ክቡር ሚኒስትር እያንቀላፋን ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው የከተማው መሬት እንደ ጉድ እየተቸበቸበ ነው፡፡
 • ማን ነው የሚሸጠው?
 • አሁን ማን ይጠይቃል ብለው ነው?
 • . . .
 • ዝም ብለው ሄደው አጥረው የእኔ ነው ማለት ነው፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ክቡር ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት የሚጠይቅ ሰው የለም እኮ?
 • ምን ማለት ነው?
 • ከተማው ውስጥ እኮ ማንም እየተነሳ ነው መሬት የሚወረው፡፡
 • ይኼ እኮ ሕገወጥነት ነው፡፡
 • ማን ሕጋዊ አለ ብለው ነው?
 • . . .
 • ባይሆን ይኼ ወርቃማ ዕድል አይለፈን?
 • እንዴት ማለት?
 • ማለቴ እንደ እርስዎ ዓይነት ባለሥልጣን ይዤ መቀደም የለብኝማ፡፡
 • . . .
 • ክቡር ሚኒስትር ግንባር ግንባር የሆኑ ቦታዎችን ለይቻለሁ፡፡
 •  ምን ለማድረግ?
 • ለማጠር ነዋ፡፡
 • በምን አግባብ?
 • ያው እርስዎ የድጋፍ ደብዳቤ ይጽፉልኛል፡፡
 • የምን ደብዳቤ?
 • ለልማት ሥራው መሬቶቹ ይሰጡት ብለው ነዋ፡፡
 • . . .
 • በየደረጃው ያሉትን ሰዎች እንይዛቸዋለን፡፡
 • አልገባኝም?
 • ሁሉም በጥቅም ከመጡበት ስለማይደራደር ሥራውን ለእኔ ጣሉት፡፡
 • አደገኛ ነገር እኮ ነው እየነገርከኝ ያለኸው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ከተማው ውስጥ ያለውን አሠራር እየነከርኩዎት እኮ ነው፡፡
 • . . .
 • ክቡር ሚኒስትር ከሰሞኑ መሬት ወረራ መጠቀም አለብን፡፡
 • ያስጠይቀናል እያልኩህ እኮ ነው?
 • ወደዱም ጠሉም ብቸኛው መንገድ እሱ ነው፡፡
 • የምን መንገድ?
 • የሚያደርሰን ነዋ፡፡
 • የት?
 • ወደ ብልፅግና!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላላቸው]

 • እኛ ገብቶን ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • አገሪቱን ለሽያጭ እንደምታቀርቧት ነዋ፡፡
 • እናንተ ቦጥቡጣችሁ ጨርሳችኋት ማን ይገዛታል ብላችሁ ነው?
 • ይኸው እየተቀራመቷት አይደል እንዴ?
 • እነማን?
 • እነ አይኤምኤፍና ወርልድ ባንክ ናቸዋ፡፡
 • ማን ነው ያለው?
 • ይኸው አይኤምኤፍ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አበድራለሁ ማለቱን ሰማሁ፡፡
 • አሁን የሚሰርቅ ሰው ስለሌለ ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • እናንተ ከእኛ አትብሱም ብላችሁ ነው?
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • እኛ ቢያንስ ስለጠገብን ብንሰርቅም በጥቂቱ ነው፣ እናንተ ግን ምንም የምታስተርፉ አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ እኮ የሚገርመኝ ደርሶ ተቆርቋሪ ስትመስሉ ነው፡፡
 • ዕድሜያችንን በሙሉ ለዚህች አገር መገበራችንን አይርሱ፡፡
 • ጥያቄው እኮ ምን በማድረግ የሚለው ነው?
 • በመሥራት ነዋ፡፡
 • በመዝረፍ ነው ያልከኝ?
 • . . .
 •  ለማንኛውም እናንተ ራቁቱን ያስቀራችሁትን ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስ እየሞከርን ነው፡፡
 • እኔም አደዋወሌ ትንሽ favor እንዲያደርጉኝ ነው፡፡
 • የምን favor ነው?
 • ለፋብሪካዬ እንዲያቋድሱኝ ነዋ፡፡
 • ከምኑ?
 • ከዶላሩ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...