Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአህዮች በጥቁር ገበያ

አህዮች በጥቁር ገበያ

ቀን:

በቻይና በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ባህላዊ መድኃኒቶች ‹‹ኢጃዎ›› አንዱ ነው፡፡ ኢጃዎ የተለያዩ በሽታዎችን ከመፈወስ ባሻገር በኮስሞቲክስ ኢንዱስትሪ ውስጥም ትልቅ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ከዘመናት በፊት ባለፀጎች የሚጠቀሙት ውድ ምርት የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ቻይናዊ የኢጃዎ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡

ቢሊዮን ዶላሮች የሚገላበጡበት የኢጃዎ ገበያ የዓለምን ትኩረት የሳበው ዘግይቶ ነው፡፡ ኢጃዎ የሚመረተው ከአህያ ቆዳ ነው፡፡ ከተቀቀለ የአህያ ቀዳ ተጨምቆ የሚወጣው ‹‹ጀላቲን›› ዋነኛ የኢጃዎ ግብዓት ነው፡፡ ገበያ ላይ ያለው ተፈላጊነት ጣራ በነካበት በአሁኑ ወቅት፣ ፍላጎቱን ለማርካት በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን አህዮች መታረድ ይኖርባቸዋል፡፡

በገበያ ላይ ያለው የኢጃዎ አቅርቦት እ.ኤ.አ. በ2013፣ 3,200 ቶን የነበረ ሲሆን፣ ይህ እ.ኤ.አ. በ2016 ወደ 5,600 ቶን ማደጉን ዶንኪ ሳንክቹዌሪ ያስረዳል፡፡ በሦስት ዓመት አንዴ ለሚዋለዱት አህዮች ኢንዱስትሪው የሚጠይቀውን ያህል ቁጥር ማምጣት ግን አልተቻም፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1992 ጀምሮ በቻይና የሚገኙ አህዮች ቁጥር በ76 በመቶ ቀንሷል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ቻይና የተሻለ የአህዮች ቁጥር ወዳላቸው አገሮች ዓይኗን መጣል ጀመረች፡፡

ሰፊ የአህዮች ቁጥር ወዳለባቸው ሌሎች የእስያ አገሮች፣ አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ ገባች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2007 ወዲህ በብራዚል የነበረው የአህዮች ቁጥር በ28 በመቶ፣ በቦትስዋና 37 በመቶ፣ በኪርጊስታን ደግሞ 53 በመቶ አሽቆለቆለ፡፡ በቻይና ያለው የኢጃዎ ገበያ በዚህ ከቀጠለ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በዓለም ላይ የሚገኙ አህዮች ቁጥር በግማሽ እንደሚቀንስ በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡

አስደንጋጭ አኃዞችን ያወጡ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች ጉዳዩን ለም እንዲያውቀው ቢያደርጉም፣ የኢጃዎ ገበያ ግን እያደገ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም፡፡ ኢጃዎን የሚያመርቱ የቻይና ኩባንያዎች ከብራዚልና ኪርጊስታን ተነስተው አሁን ደግሞ ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ማድረጋቸው እየተነገረ ነው፡፡

 በጋማ ከብቶች ሕክምና ዙሪያ የሚሠራው የብሩክ የእንስሳት ሆስፒታል በኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ደስታ አረጋ፣ በአንድ ወቅት የአህያ ሥጋ ወደ ውጭ እልካለሁ ብሎ ሥራ ጀምሮ የነበረው የቻይና ኩባንያ አጀንዳው ለኢጃዎ ምርት የሚሆን የአህያ ቆዳ መሰብሰብ እንደነበርና ኩባንያው በማኅበረሰቡ ተቃውሞ ከአገር ቢወጣም፣ አሁንም የኢትዮጵያን አህዮች በእጅ አዙር ከማግኘት እንዳልተቆጠበ ይናገራሉ፡፡ ኩባንያውም ከኢትዮጵያ እንደወጣ በኬንያ መሥራት ጀምሯል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ በኬንያ አራት የአህያ ማረጃ ቄራዎች ተከፍተዋል፡፡ ቄራዎቹ በቀን ከ1,000 የሚበልጡ አህዮችን እንደሚያርዱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በመጀመርያ አብዛኛዎቹ ኬንያውን አህዮቻቸውን እያወጡ ይሸጡ ነበር፡፡ ለአንዱ አህያ የሚጠራው ዋጋ ከቀን ወደ ቀን እያደገ መጥቶ ጣራ መንካቱ ደግሞ ገበያውን ሳቢ አድርጎታል፡፡ በኬንያ የአንድ አህያ ዋጋ እ.ኤ.አ. በ2016 ከነበረበት 78 ፓውንድ እ.ኤ.አ. በ2019 ወደ 156 ፓውንድ ከፍ ብሏል፡፡

ሁኔታው ኬንያ የነበራትን 1.8 ሚሊዮን የአህያ ሀብት በአንድ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል፡፡ በኬንያ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ የሚታረዱ አህዮች ቁጥር ከአጠቃላይ ውልደት መጠኑ በአምስት እጥፍ ይበልጣል፡፡ በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ አራት የአህያ ቄራዎች 301,977 የኬንያ አህዮችን አርደዋል፡፡ በዚህ ከቀጠለ እ.ኤ.አ. በ2023 የኬንያ የአህያ ሀብት ሙሉ ለሙሉ ሊሟጠጥ ይችላል፡፡ ሁኔታው አህያቸውን እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ለሚጠቀሙት ኬንያውያን ትልቅ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ‹‹አህያችንን አንሸጥም›› የሚሉ ኬንያውን መኖር ደግሞ ለጥቁር ገበያ መስፋፋት መንገድ ከፍቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኬንያ የአህያ ስርቆት ተጧጡፏል፡፡ አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ እ.ኤ.አ. በ2018 1,000 አህዮች መሰረቃቸውን ሪፖርት ተደርጓል፡፡

ኬንያ ያላት የአህያ ሀብት መመናመን በኢጃዎ ምርቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነውና የቻይና ኩባንያዎች አሁንም ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ እንደጣሉ ነው፡፡ ሰፊ የአህያ ሀብት ካላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በትግራይ ክልል 886,103፣ በአፋር 125,671፣ በአማራ 3,279,179፣ በኦሮሚያ 3,419,932፣ በሶማሌ 200,639፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 82,228፣ በደቡብ 811,105፣ በጋምቤላ 2,150፣ በሐረር ክልሎች 14,356፣ በድሬዳዋ ከተማ 24,226 በጥቅሉ 8,845,589 አህዮች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡

በኬንያ ያለው የአህያ ሀብት መመናመን በኢትዮጵያ ደግሞ ሰፊ ሀብት መኖር ያባበላቸው በኬንያ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች፣ ከኢትዮጵያ ቢባረሩም በእጅ አዙር ከኢትዮጵያ አህያ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ አቶ ደስታ እንደሚሉት፣ አንድ የቻይና ኩባንያ የአህያ ቄራ የከፈተው በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው የኢትዮጵያን አህዮች ቀረብ ብሎ ለማግኘት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ በርካታ አህዮች ወደ ኬንያ በሕገወጥ መንገድ ይጓዛሉ፡፡ አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ረዥምና አድካሚ ጉዞ ያለ በቂ ምግብና ውኃ ሲጓዙ ብዙዎቹ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ 20 በመቶ የሚሆኑት መንገድ ላይ ይሞታሉ፡፡ በሞያሌና በኦሞ ኩራዝ በኩል እየተነዱ የሚወጡት አህዮችን ከየአካባቢው የሚሰበሰቡ ደላሎች ተበራክተዋል፡፡ በኬንያ ለሚታረዱ አህዮች 80 በመቶ የሚሆነው ከኢትዮጵያ የሚጓዙ ናቸው፡፡ ለአንድ አህያ የሚጠራው ገንዘብም እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ ገበያው አጓጊ ሆኗል፡፡ ስለዚህም አርሶ አደሩ ውኃ ማመላለሻና መጫኛ ትራንስፖርቱን አውጥቶ እየቸበቸበ ይገኛል፡፡

መንግሥት የማያውቅው ይህ የአህያ ንግድ ለአብዛኞቹ ኢትጵያውያን እንግዳ በመሆኑ ጠያቂ አልነበረም፡፡ ምሽት ላይ በገፍ እየተነዱ ድንበር ሲያቋርጡም የሚያስቆም አለመኖሩ ተነግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአንድ አህያ ዋጋ 10,000 ብር መግባቱን ለአቶ ደስታ የነገራቸው አንድ ወዳጃቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ‹‹አህዮቹ የት እንደሚሄዱ አይታወቅም ነበር፤›› ብሏቸዋል፡፡ መሰራረቁም እንደ ኬንያ አሥጊ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

አስከፊው ጉዳይ ደግሞ በሕገ ወጡ የንግድ እንቅስቃሴ የተገኘው ሁሉ ለዕርድ መቅረቡ ነው፡፡ መውለድ የሚችሉ ሴት አህዮች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለዕርድ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ዘ ጋርዲያን እንዳስነበበው እርጉዝ አህዮችም ለቆዳቸው ሲባል እየታረዱ ነው፡፡ ዕርዱ የሚከናወነውም ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ መሆኑን የሚያሳይ ቪዲዮ እንደደረሳቸውና ምስሉም ተቋማት፣ ‹‹በማስረጃ ክፍል ውስጥ የአህያ ፅንስ እንደሚታይ ከጎኑም ለመታረድ ተራውን የሚጠብቅ ሌላ አህያ መኖሩን የሚያሳይ እንደሆነ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ አሰቃቂው የዕርድ ሒደት ከፍተኛ የፅዳት ጉድለት ያለበትና ከእንስሳ ወደ ሰዎች ለሚተላለፉ እንደ አትራክስ ያሉ በሽታዎች መዛመት መንገድ የሚከፍት መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በቻይና እየተጧጧፈ የመጣው የኢጃዎ ንግድ እርጉዝ አህዮችን እስከ ማረድ የደረሰ፣ ይህም የአህዮች የውልደት መጠን ውስን ከመሆኑ ጋር ተደምሮ የዓለም የአህያ ሀብት በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እንዲመናመን እንደሚያደርገው የገለጹት አቶ ደስታ ናቸው፡፡  

አንድ የአህያ ውርንጭላ አድጎ ለአቅመ አህያ ለመድረስ ረዥም ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ አንዲት አህያ የምትወልደውም በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ቻይና የምትፈልገውን የአህያ አቅርቦት ለማርካት 20 ዓመታትና ከዚያ በላይ ተግቶ አህዮችን ማራባት ይፈልጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...