Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አልበዛም ወይ?

ሰላም! ሰላም! ሰው ዘንድሮ ምን እንደበላ ወይም ምን እንዳበሉት አላውቅም ከራስ በላይ አዋቂ ሆኗል። ለራስ የሚያውቅ ጠፍቶ ምክር በዱላ በሆነበት አገር፣ ሰው ለመምከር የሚያዘው ሠልፍ የዳቦ ወረፋን ያስንቃል። እውነቴን ነው የምላችሁ። እናት ልጃቸው ሞተ አሉ። በዕንባ ዓይናቸው ሊጠፋ ደረሰ። ኋላ ቀብረው ሲመለሱ ማልቀሱን ትተው ኩላቸውን ተኳሉ። ወዳጅ ዘመድ ነኝ ባይ አሽሟጠጣቸው። በኩሉ ምክንያት ነዋ። ኋላ ምን አሉ እንግዲህ? ‹‹ከእኔ የቀረበው ሄዶ ለእናቱ ይንገራት፤›› ሲሉ፣ ከእናት በላይ አውቃለሁ ያለ አፉ እንደ ተጠመዘዘ ቀረ። ታዲያ እኔን እኮ የከበደኝ ይኼ ነው። ድሮ ድሮ ሰው አንድ ነገር ብሎ ተንኩሷችሁ የመልስ ምት ስትሰርቡለት ገብቶት ዝም ይል ነበር። የዛሬ ሰው ግን ራሱ ከሚያስበውና ከሚያወራው በላይ ሌላው የሚለውን መስሚያ የለውም። ‹መስሚያዬ ጥጥ ነው› ሲል ለካ ትውልዱ ወዶ አይደለም አትሉም? ባይሆንማ ኖሮ መደማመጥ እንደ ኤቨረስት ተራራ ይሆንብን ነበር?

እናላችሁ በቀደም አንዱ፣ ‹‹አንበርብር ለምን ለራስህ አታውቅም?›› አለኝ። ይኼውላችሁ ነገር ፍለጋ መሆኑ ነው። ‹‹እሺ ምን ብዬ ልወቅ?›› ስለው፣ ‹‹አለ የተባለ ሁሉ ገንዘቡን ወደ ውጭ አገር እያሸሸ በዶላርና በዩሮ እያስቀመጠ፣ አንተ ለምንድነው ዝም ብለህ በዲቫሉዌሽን የሚላሽቅ ብርህን የምታየው? ይኼ አገር በዚህ ሁኔታው ተስፋ አለው ብለህ ነው?›› ብሎ ምንም ሳልለው ከመሬት ተነስቶ በአገሬና በእኔ ላይ እኩል ሳቀ። ‹‹አይ ምን መሰለህ. . .›› ምናምን እያልኩ ገና መናገር ስጀምር፣ ‹‹ዝም ብለህ እኔን ብትሰማኝ ይሻልሃል። ከአንተ የበለጠ ስለገንዘብ የሚያውቅ የለም። ምን አለፋህ ይኼን አገር አምነህ የላብህን ፍሬ በከንቱ ከምታበላሸው በቶሎ አሽሸው፤›› ሲለኝ ቀስ ብዬ እንደ ምንም በሰበብ አስባብ ከእሱ ከራሱ ሸሸሁ። ለዓይን ከአፍንጫ የቀረበ አለ እስኪ አሁን? ታዲያ ምን ልክፍት ነው አፍ አፍችንን እያለ አላስቀምጥ የሚለን? ኧረ ምን ጉድ ነው! እኔማ ዘንድሮ ሰውን ምን ነካው ማለት ትቼ ራሴን መመርመር ጀምሬለሁ፡፡ ምናልባት ወፈፍ እያደረገኝ ይሆን? ምን ልበል ታዲያ!

መቼም ይህች ጨዋታ ብዙ ሳታስወራን አትቀርም። ከራስ በላይ ራሳችን ንፋሱን ካላሸነፍን እያሉ የሚገጥሙትን ትግል ለማን ልንገረው የሚያስብል ነው። ይኼውላችሁ እኛ ዘንድ አንድ የጎረቤቴ ልጅ አለች። ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ ዘንድሮማ ካላገባች ጉድ ነው ይባባላል መንደርተኛው። ከሚባባለው መሀል ደግሞ ስንቱ መሰላችሁ ተፋቶ የሚኖረው። ልጅቷ መቼም ሲፈጥራት ውብ ናት። አንድ ቀን ተስቶኝ ማንጠግቦሽ ፊት ስለዚችው ሸጋ ልጅ ሲወራ፣ ‹‹ውቤ ከረሜላ የተዘፈነው መቼም ለእሷ መሆን አለበት   . . .›› ብዬ ሳምንት ሙሉ እህል የማይል ሽሮ ብቻ በልቻለሁ። ኩርፊያ መሆኑ ነዋ። መቼም የማትቀና ሚስት ስጠኝ አይባል ነገር፡፡ ሚስት ለባሏ ባል ለሚስቱ፣ ዜጋ ለአገሩ አገር ለዜጎቿ ካልቀናች ምኑን ኑሮ ምኑን ትዳር ይበላል? ታዲያ ይህችን ውብ ስትወጣ ስትገባ ያም ያም አውቆ ‹ጓደኛሽን አታስተዋውቂንም እንዴ አንቺ? የት ነው ምትደብቂው› እያለ ይጠዘጥዛታል። የዘንድሮ ቅዝቃዜና የዘንድሮ ሰው አላበዙትም እንዴ!

ልጅት ደግሞ ‹ማማዬ… ማማዬ…› ሲዘፈን ተወልዳ መሥፈርቷ በቴስታ የማይማታ፣ የት ወጣሽ የት ገባሽ የማያበዛ፣ ሌሎች ‹ማማዬ… ማማዬ…› የሚለው ዘፈን ላይ ያሉት ሂሶች ሲነሱ የማያነሱት ሰው ነው ምትፈልገው፡፡ ትወጣና መንገድ መንገዱን ስታይ ትውላለች፡፡ ‹‹አንቺ ልጅ ማግባት የምትፈልጊው ትራፊክ ፖሊስ ነው ወይስ ተላላፊ ድንገተኛ መንገደኛ? ››እያሉ እናቷ ሳይቀሩ ያሾፋሉ፡፡ መንገዱ ግጭት ብቻ አይደል? ነጂው ይጋጫል፣ ተነጂውም ይሞታል፡፡ ይኼን ዓይታ አላገባም አለች፡፡ ‹ለምን?› ስትባል ‹‹ከዚህ ሁሉ ገጭና ተገጪ አንዱ ባሌ ቢሆን መንገድና አመል አይለቅምና ማታ ቤቱ ገብቶ ነይ ልግጪሽ ማለቱ አይቀርም፤›› ብላ አረፈችው፡፡ ጉድ እኮ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ይኼ ወሬ ተነዛ ማለት እንግዲህ አስቡት፡፡ በትራፊክ አደጋ አንደኛ መሆናችን አልበቃ ብሎ ባለመጋባት ሰንጠረዥም ቀዳሚ ልሆን ነው ማለት ነው። የቀዳሚ ነገር ሲነሳ እንዴት ነው ከአገር፣ ከአፍሪካ፣ ከዓለም አንደኛ ማለት የምንወደው? አንደኛ መሆን ጥሩ ነገር ቢሆንም ያለ ሥራ ግን አይቻልም!

እናላችሁ ስለዚህ ብርን በውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ስለማሸሽ ነገር ሰሞኑን ብዙ ስሰማ ነበር። ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር የምንሸጋገረው እንግዲህ በዚህ አያያዛችን መሆኑ ነው። ‹‹እኔን የሚገርመኝ ግን በቃ ብዙው ሰው የሚያስበው አንድ ዓይነት ነገር ነው ማለት ነው?›› አለኝ በቀደም ምሑሩ የባሻዬ ልጅ ነገሩን አንስቼለት። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹ሠርተን ሠርተን ሲጠራቀምልን ለምንድነው ከትልቅ ቤት፣ ከቅንጡ አውቶሞቢልና ከውስኪ ቤት ሌላ ማሰብ የማንችለው?›› ሲለኝ፣ ‹‹ነገር አታምጣ!›› ብዬ እንዳልሰማ ሆንኩበት። ነገር ፈርቼ እንጂ በውስጤ የሚብላላው መዓት ነው። በተለይ ስለእኛ የምናወራቸው ነገሮችና የምናደርጋቸውን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ነገሮች ሳይ ሳቄም ዕንባዬም እኩል ይመጣሉ። ለምሳሌ ብዬ ላስቆጥራችሁ። ለምሳሌ አገር አገር እያሉ ለመጮህና ለመታየት አንደኞች ነን። ከዚያስ አትሉም? ከዚያማ ዞር ሲሉ ቡጭቅ ይቀጥላል፡፡ አንተዋወቅም እንዴ!

ዘወር ተደርገን ስንታይ ተውት ሌላውን፣ ለአካባቢያችንን ፅዳት መጠበቅ ግድ የማይሰጠን ሆነን እንገኛለን። ‹እከሌ ሀብታም ነው ግን አይሰጥም። አቤት ተሸክሞት ሊሞት ነው? ወይስ መቃብር ቤት ሲወርድ ሊንተራሰው ነው?› እያልን ባለሀብቱን ሁሉ ስናማ ላየን ከእኛ በላይ ተመፅዋችና የተቸገረ የሚረዳ ያለ አይመስልም። ነገር ግን እንዲያ ከምንለው ውስጥ እንደ አቅሚቲ የምናከራያት ቤት ያለችን ሰዎች፣ የተከራይ ለቅሶና ብሶት አልታወቀን ብሎ በወር በወር ኪራይ የምንጨምር ሆነን እንገኛለን። እንዲያው እሱን ትታችሁት የቤት ውስጥ ሠራተኞቻችንን በትህትናና በወንድም በእህትነት ስሜት የምንከባከባቸውስ ስንቶቻችን ነን? ስንትና ስንት የግፍና የበደል ኃጢያት ላያችን ላይ ተሸክመን የሌሎችን ንፁህ ህሊና ስናቆስል እንገኛለን፡፡ በማስመሰል አንደኛ እኮ ነን!

ያለ መተዋወቅን ነገር ሳነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ። የትናንትን አያድርገውና ከአሥር ዓመታት በፊት አዲስ አበባን በቀበሌያቸው ስም በቁጥጥራቸው ሥር ያዋሉ ማፊያዎች እንደነበሩ የምታውቁ ታውቃላችሁ። መቼም አልሰማንም አላየንም ባይ ካለ ይገርመኛል። ስንቱ ሚስቱን በአደባባይ ተቀማ? ስንቱ ገንዘቡን ተነጠቀ? ስንት ልጃገረዶች ያለ ፍላጎታቸው ተገደው ተደፈሩ? ስንቱ የፍትሕ ያለህ ብሎ እሪ አለ? የሰማ አልነበረም። ምክንያቱስ ካላችሁ አለመተዋወቅ። ሕዝቡ ያውቃቸዋል፡፡ አውቋቸው ይፈራቸዋል፡፡ መንግሥት ‹ኧረ በሕግ አምላክ አንድ በልልን› ሲባል ምንድነው የምታወሩት? ይል ነበር አሉ። አሉ ነው እንግዲህ። የአሉባልታ መብታችን መቼም አልታገደም። ኋላ አንድ ቀን ከእነዚያ ጎረምሶች መሀል አንደኛው ይሞታል አሉ። ኮንሰርት ይዘጋጅ ይባላል፡፡ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በእጃቸው ነው አሉ። ባነር ተሰቀለ። ፍላየር ተበተነ፡፡ በቀረው ደግሞ ማታ ማታ እየዞሩ በየመሸታ ቤቱ ትኬት መሸጡን ተያያዙት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማፍያነት በሌሎች ድርጊቶች እየተለመደ መሆኑን ልብ ብላችኃል? ካላላችሁ አካባቢያችሁን ዞር ዞር እያላችሁ ቃኙ፡፡ የሚያዋጣው ቅኝት ነው!

እንግዲህ ስላለመተዋወቅ አይደል የምናወራው? ያው እንደለመደው አንዱ ጥጋበኛ በዕድሜ ጠና ወደሚል ወደ አንድ ሰው ጠጋ ብሎ 15 ትኬቶች ያስቀምጣል። ‹‹ምንድነው?›› ይላል ሰውዬው። ‹‹ጓደኛችን በድንገት ስለሞተ ለእሱ መታሰቢያ ኮንሰርት እያዘጋጀን ነው። እና አሁን ወሬ ሳታበዛ የ15 ትኬት 15 ሺሕ ብር ዱብ በል. . .›› ይላል አሉ። ጉድ እኮ ነው። ይኼ ሁሉ እንግዲህ ተወልደን ባደግንባት አዲስ አበባ ነው። ሰውዬው፣ ‹‹እኔ የምትለው ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ይኼ ጓደኛችሁ ለአገር ያበረከተው አስተዋጽኦ ምንድነው? ማነው ስሙ? ይታወቃል?›› ብሎ ሲጠይቅ አሉ ያ ወሮበላ የትም እንደለመደው፣ ‹‹አቦ ምን ወሬ ታበዛለህ? ዱብ በል ብያለሁ ዱብ በል. . .›› ብሎ ማስፈራራት። ለካስ ይኼን ሁሉ የሚባባለው በከፍተኛ ደረጃ ከሚታወቅና ከሚፈራ፣ እንዲሁም በቦዲ ጋርድ ከሚታጀብ ባለሀብት ጋር ኖሯል፡፡ ከዚያማ ምን ይነገራል? ዋጋውን አገኘ፡፡ እኔማ በወሬ በወሬ ይኼን ጉድ ስሰማ ወይ አለመተዋወቅ ጣጣው እያልኩ አገሬን የወረራትን የትዕቢት ቫይረስ ረገምኩ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ለማለት የፈለግኩት ካልተዋወቅን፣ ካልተጠናናን በቃ አንከባበርም ማለት ነው? ሕግ ብቻ የማይገዛን ለምንድነው? ኧረ ከምን ይሆን የተፈጠርነው? ንገሩኝማ በሞቴ! አንዳንዴ ሳስበው ትዕቢት ልብ ሲደፍን ማሰቢያም ይዘጋል መሰለኝ!

በሉ እንሰነባበት። እኔና የባሻዬ ልጅ ተያይዘን በጊዜ ግሮሰሪያችን በረንዳ ላይ ተሰይመናል። አጠገባችን ያለ ምንም ዕውቀት በድፍረት ስለዓለም የፖለቲካ አካሄድ አንዱ ይቦተረፋል። ሰምተን እንዳልሰማን ብናልፈው ደግሞ አንዱ በጎን የፊደል ካስትሮን ታሪክና አንብቦ ስለማያውቀው ዲያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም ይቀደዳል። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹እንዲያው እንዲህ ኃፍረት ሙልጭ ብሎ ይጥፋ? ሰው ቢሰማኝ ምን ይለኛል የሚል ይጥፋ?›› ይለኛል። ‹‹ሁሉም ተንታኝ። ሁሉም አዋቂ። ሁሉም የፊቱና የኋላውን እኩል የማወቅ አቅም ያለው ሆኖ የተፈጠረበት እንደዚህ ያለ ዘመን ያለ አይመስለኝም፤›› እያለ የባሻዬ ልጅ ሲናገር አንዱ ብድግ ብሎ፣ ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ፤›› አለ። እሺ ቀጥል አልነው። ቀጥል ከማለት ውጪ ምን እንበለው ታዲያ!

እሱም የእኛን ትዝብት ተጋሪ ሆኖ ኖሮ፣ ‹‹እኔ ምንም ሊገባኝ ያልቻለ ጉዳይ አለ። እሱም ምንድነው? ይኼ ሁሉ ተንታኝ፣ ይኼ ሁሉ ምሑር፣ ይኼ ሁሉ ተዋናይ፣ ይኼ ሁሉ መካሪ፣ ይኼ ሁሉ ተሟጋች ባለባት አገር እንዴት ሦስት ሺሕ ዘመን በጦርነት ብቻ አለፈ? ይህችን ብቻ መልሱልኝ፤›› ብሎ ተቀመጠ። ‹ደህና ነገር የሚያወራ መስሎኝ›  እየተባባለ ሁሉም ፊቱን ከእሱ አዞረ። ችግር የማይፈታ ዕውቀት፣ አቅጣጫ የማይወስን ትንታኔ፣ ዘዴና ብልኃት የማያፈልቅ ኢንፎርሜሽን፣ እንዲያው ብቻ በየሄድንበት ለወንበር ማሞቂያ አልኩ ለማለት ተብሎ ሲቀደዱ ውሎ ሲቀደዱ ማምሸት፣ ደግሞ ከእሱም ብሶ አለመደማመጥ፣ መናናቅ፣ መገለማመጥ፣ ማን ስለሆንክ? ማን ስለሆንሽ? እየተባባልን ስንኖር አያሳዝንም? እኔማ ደሜ ይፈላል፡፡ በተለይ አስመሳዮችና አለቅላቂዎች በበዙበት በዚህ ዘመን ሌላው ሰው አንገቱን በይሉኝታ ደፍቶ መንገዱን ሲለቅላቸው ያናድደኛል፡፡ እንዴት ሆኖ ነው ወሬኛና አሉባልተኛ አገሩን ሲወር ዝም የሚባለው? ይሉኝታና ኃፍረት አይበቃም ወይ? ስድ አደጎችና ወረበሎች እንዳሻቸው ሲጨፍሩ፣ ምድረ ወሬኛ በሐሰት ሲቀደድ፣ ጥራዝ ነጠቆች ሲለፋደዱና አገሪቱ በኃላቀሮች ስትጎተት እንዴት ዝም ይባላል? አልበዛም ወይ? መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት