Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበመከባበርና በሥራ ትጋት ዓለምን የምትመራው ቻይና

በመከባበርና በሥራ ትጋት ዓለምን የምትመራው ቻይና

ቀን:

በእስያ ከሚገኙ 48 አገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡ በሕዝብ ብዛቷም ከዓለም ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች፡፡ በኢኮኖሚ ዕድገቷም ከአሜሪካ በመለጠቅ ዓለምን ትመራች፡፡ በፓስፊክ ውቅያኖስ ጠረፍ በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትገኘው ቻይና፣ አገር ሆና ከተመሠረተች 70 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ አጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 9,388,211 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ የሕዝብ ብዛቷም ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ነው፡፡

ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ 18.59 በመቶውን የያዘችው ቻይና፣ በሕዝብ ብዛቷም ሆነ በኢኮኖሚ ዕድገቷ ከዓለም አገሮች ቀዳሚ የሆነችበትን ምክንያት ለመታዘብ የቻልኩት ሰሞኑን በቻይና በነበረኝ የሳምንት ቆይታ ነው፡፡ ያስደመሙኝ ዕይታዎቼም እኚህ ነበሩ፡፡

ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ስወጣ የመጀመሪያዬ ባይሆንም፣ ረዥም የአየር ላይ ጉዞ ያደረኩት ግን ከኢትዮጵያ እስከ ቻይና ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንብረት በሆነው ኤርባስ አውሮፕላን ለአሥር ሰዓታት ከበረርን በኋላ እኩለ ቀን አካባቢ የቻይና የኢኮኖሚ ዞን ወይም ከተማ በምትባለው ሻንሀይ (Shanghai) አውሮፕላን ማረፊያ ደረስን፡፡

በድንቅ ጥበብ ከተሰራው ሻንሀይ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰው የኢትዮጵያ ኤርባስ አውሮፕላን፣ ጎማው መሬት ከረገጠ በኋላ መንገደኞች ማውረጃ ቦታ ለመድረስ ከ3ዐ ደቂቃ በላይ ተጉዟል፡፡

ከዘጠኝ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን የተውጣጣነው ልኡካን የከተማውን ነዋሪ የተቀላቀልነው ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀውን የኢሚግሬሽን የይለፍ ፈቃድ አግኝተን ነው፡፡

‹‹በባህር ላይ ያለች ከተማ›› (City on the Sea) ተብላ የምትጠራውና በያንግዚ ወንዝ ላይ የተመሠረተችው ውቧ ሻንሀይ፣ ከትንሽ ዓሳ ማስገሪያ መንደርነት ተነስታ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እምብርት መሆኗን ነዋሪዎቿ ይመሰክራሉ፡፡

ቻይናን እንድንጎበኝ ግብዣ ያደረገልንን የሲሲአርሲሲ (የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ) ባልደረቦች አግኝተን፣ የመጀመሪያውን የሻንሀይ ከተማ ለከተማ ጉዞ አደረግን፡፡ የሻንሀይ የአስፓልት መንገዶች ምጡቅ የምህንድስና ጥበብ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ሰፊ፣ አንዱን ከአንዱ የሚያሳልጡና በርካታ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግዱም ናቸው፡፡

 ከአውሮፕላን ማረፊያ ተነስተን ለአንድ ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ በርካታ ጎብኚዎችና የአገሪቱ ባለሀብቶች አብዝተው ከሚዝናኑበት ሁዋንግፑ ወንዝ ደረስን፡፡ የሻንሀይን ከተማ ከቀን ይልቅ በምሽት ማየት እጅግ በጣም ያስደስታል፡፡ ዓይነ ግቡ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች፣ የአገሪቱን ባህልና እሴት በሚያንፀባርቁ ቁሳቁሶች የተሠሩ መለስተኛ መኖሪያ ቤቶችና አልፎ አልፎ የተሠሩ ሰማይ ጠቀስ ማማዎች እጅግ ደማቅ ከሆነው የከተማዋ መንገዶች መብራት ጋር ተዳምረው የሚሰጡት ቀለም ሀሴት ይፈጥራል፡፡

የከተማዋ እምብርት መሆኑ በተነገረን ሁዋንግፑ ወንዝ ላይ ጎብኚዎችን ይዘው እየተንቀሳቀሱ ከሚያዝናኑ ባለብዙ ፎቅ የመንሸራሸሪያ መርከቦች መካከል ለእኛ ወደተዘጋጀችው ኦፖ ካርድ መርከብ ተሳፍረን የራት ግብዣ ላይ ታደምን፡፡ አንዳንዶቻችን በወንዝ ላይ በተገነባች ባለስድስት ፎቅ መርከብ ላይ ተጉዘን ስለማናውቅ መደመማችንን ከፊታችን ማወቅ ቀላል ነበር፡፡ ስለቻይና ምግብ ቀድመን የሰማነውና በአካል ተገኝተን ያረጋገጥነው የተለያየ ነው፡፡ እንደየአገሩ ባህልና ሃይማኖት ለምግብነት የማይውሉ የምግብ ዓይነቶች ቢኖሩም፣ በየሄደበት ‹‹ከእንጀራና ወጥ በስተቀር እንዴት ይኖራል?›› የሚለውን ሳይጨምር፣ በርካታ አማራጭ ምግቦችን የማግኘት ችግር የለም፡፡ እኛም በመንሸራሸሪያ መርከቡ ላይ ተሳፍረን በወንዝ ላይ እየተንቀሳቀስን ራታችንን ተመግበን ወደ መጨረሻው የመርከቧ አናት ላይ ወጣን፡፡

በሁዋንግፑ ወንዝ ላይ የተለያየ ቀለም በሚያመነጩ ብርሃን ተንቆጥቁጠው ወዲህና ወዲያ የሚሉት ባለ ብዙ ፎቅ እና መለስተኛ መርከቦች  በአቅራቢያው ከተገነቡት ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ከሚንጸባረቁ መብራቶች ጋር አብረው ለወንዙ ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡ ይህን የመብራት ነፀብራቅና የመርከቦች እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ረዥም በሆነው የወንዙ ዳርቻ ላይ ተሰባስበው የሚመለከቱና የሚዝናኑ የከተማው ነዋሪዎችና ጎብኚዎች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ እጅግ የሚያስደምመውን የኦፓ ካርድ ሬስቶራንት የእራት ግብዣና የመርከብ ላይ ሽርሽር ጨርሰን ለማረፊያ ወደተዘጋጀልንና በድንቅ ጥበብ ወደተገነባው ባለአምስት ኮከቡ ዌስቲን ዓለም አቀፍ  ሆቴል አመራን፡፡

በፕሮግራማችን መሰረት የጠዋቱ ጉብኝታችን ጥንታዊው የቻይና ግዛት የሆነውና ቀደም ብሎ ሶንግ ወንዝ ወይም ው ሶንግ ወንዝ ተብሎ ይጠራ በነበረው አሁን ሱዞ ክሪክ ወንዝ በሚባለው ነበርና ለቁርስ የተነሳነው ማልደን ነበር፡፡

ረዘም ያለ ጉዞ ካደረግን በኋላ በስፍራው ስንደርስ፣ በኢትዮጵያ በድልድይ፣ በባቡር ሀዲድ፣ በመንገድና በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የቻይና ሬልዌይ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልን፡፡

አካባቢው ገጠራማ የሚባለው የቻይና ግዛት ቢሆንም፣ ጥራቱን የጠበቀና በጥሩ ንድፍ የተሠራ መንገድ፣ ግራ ቀኙ ደግሞ በተለያዩ ዛፎች የተዋበ ለምለም አካባቢ ነው፡፡ ሲአርሲሲ ለወንዙ ግራና ቀኝ መጠበቂያ ግንብ በመሥራት፣ የተለያዩ ዕፀዋትን በመትከል፣ አካባቢውንና የተለያዩ ደሴቶችን በመገንባት ወንዙን ለአገሪቱ ሕዝቦችና ጎብኚዎች መዝናኛ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ ወንዙ በቀጥታ ከሻንሀይ ከተማ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ የንግድ ቀጣናውን በማስፋት የገቢ ምንጭ ለማድረግም ታስቦ እየተሠራ መሆኑን የሲአርሲሲ ኃላፊዎች ገልጸውልናል፡፡

በዋናነት እኛ ኢትዮጵያውያን ፕሮጀክቱን እንድንጎበኝ የተፈለገው፣ ሲአርሲሲ በኢትዮጵያ የሚሠራቸው የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ጋር አሠራራቸው ተመሳሳይ መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡ የወንዙን መጠበቂያ ግንብ በድንጋይ ሳይሆን ከሲሚንቶ ጡብ እየሠሩ የሚገነቡበትን ጥበብ ለተመለከተ፣ በዙሪያዋ ድንጋይ የከበባትን ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ምን ሊያስመስሏቸው እንደሚችሉ ፕሮጀክቱ አመላካች ነው፡፡

የአገር ፍቅር ኖሮት በአግባቡ የሚያሠራ ኢትዮጵያዊ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ካለ፣ ባህር ሰርጉደው በመግባት ተዓምር እየሠሩ የሚገኙት ቻይናውያን መልካም መልክአ ምድር ያላትን ኢትዮጵያ ውብ እንደሚያደርጓት አያጠራጥርም፡፡

በመግቢያዬ ላይ በዓለም ሕዝብ ብዛቷ አንደኛ መሆኗን የገለጽኳት ቻይና፣ በቀንም ሆነ በማታ በመንገዶቿ ላይ አንድም ሰው አለመታየቱ ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹1.4 ቢሊዮን ሕዝብ የት ነው ያለው?›› ብሎ ለሚጠይቃቸው የሚሰጡት ምላሽ ‹‹በሥራ ላይ  ናቸው›› ነው፡፡

በመከባበርና በሥራ ትጋት ዓለምን የምትመራው ቻይና

 

የሱዞው ክሪክ ወንዝን የሲአርሲሲ ፕሮጀክት ጉብኝት በማጠናቀቅ፣ ጉዟችንን ትንሿ የኢንዱስትሪ ዞን ተብላ ወደምትጠራው ኩንሻን ከተማ አደረግን፡፡ ኩንሻን ሲቲ ተብላ የምትጠራው ግዛት የምታስደንቀው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ወደ ከተማነት ለመለወጥ እንቅስቃሴ የጀመረችው ኢሕአዴግ ደርግን አሸንፎ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረበት ሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ የነበራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም የአካባቢው አርሶ አደር ነዋሪ በመሆኑ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከ30 ዓመታት በፊት የነበረውን የኑሮ ሁኔታ እንደተረዳነውና አሁን የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ እንዳየነው አጃዒብ ብለናል፡፡

በሌሎቹ የቻይና ግዛቶችና አካባቢዎች የማይሠሩት ፌስቡክ፣ ቲዊተር፣ ኢንስታግራም፣ ዋትስ አፕ፣ ቴሌ ግራምና ሌሎችም ቴክኖሎጂዎች ወደሚሰሩበትና በኩንሻን ሲቲ ወደሚገኘው ሶቨሬን ዓለም አቀፍ ሆቴል አቅንተን ሻንጣችንን ካስቀመጥን በኋላ የጎበኘነው የከተማዋን ሙዚየም ነው፡፡ ሙዚየሙ ከተማዋ ስትቆረቆር በመሣሪያነት ያገለግሉ የነበሩ የግብርናና የኮንስትራክሽን መገልገያ መሣሪያዎች የሆኑትን መዶሻ፣ እንጨት መላጊያ፣ አካፋ፣ ዶማ፣ የእንጨት ጀልባ፣ ብስክሌት፣ ፋስ፣ መጋዝና የተለያዩ አልባሳትን እና አሁን የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ የሚታይበት ነው፡፡ ጉብኝቱን ሙሉ የሚያደርገው ያስጎበኙን ‹‹ከተማዋን የቆረቆሩት እነእከሌ ነበሩ›› የሚሉ አስጎብኚ ሳይሆኑ፣ ከተማዋን ከከተማው አስተዳዳሪ በተሰጣቸው ኃላፊነት ለኢንዱስትሪና ኢኮኖሚ ዞን ያበቋት የ73 ዓመት አዛውንት መሆናቸው ነው፡፡

አዛውንቱ ሚስተር ሼን ይባላሉ፡፡ በሙዚየሙ ውስጥ ከተቀመጡ ቀደምት መገልገያ መሣሪያዎች ውስጥ፣ አብዛኞቹ እሳቸው የሚጠቀሙባቸው ነበሩ፡፡ በቢሮ ውስጥ ይቀመጡበት የነበረ ወንበርና ጠረጴዛ እንዲሁም አልባሳት ጭምር ተቀምጠዋል፡፡ የቢሮ መቀመጫዎቻቸው ከትንንሽ እንጨቶች የተሠሩ ጠረጴዛና ወንበሮች ናቸው፡፡ ሚስተር ሼን እንደነገሩን፣ ኩንሻን ሲቲ ከ30 ዓመታት በፊት ኋላቀር፣ ነዋሪዎቿም በግብርና የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡ ከኢትዮጵያዋ ድሬዳዋ ከተማ ጋር የእህትማማችነት ስምምነት ከዓመት ፊት መፈራረማቸውን ያስታወሱት አዛውንቱ፣ ‹‹ኩንሻን ሲቲ ከ30 ዓመት በፊት የአሁኗን ድሬዳዋን ከተማ ትመስል ነበር›› ይላሉ፡፡ ለድሬዳዋ ልዩ ፍቅር ያላቸውና ደጋግመው ስሟን መጥራት የሚያዘወትሩም ናቸው፡፡

ኩንሻን ሲቲ ስትመሠረት የነበራት የሕዝብ ብዛት 38,000 አርሶ አደርና 4,000 በንግድ ላይ የተሰማራ  በአጠቃላይ 42,000 ነበር፡፡ አሁን የነዋሪው ብዛት ሦስት ሚሊዮን ነው፡፡ አንድ መቶ ሺው አርሶ አደር ሲሆን፣ ሌላው የኢንዱስትሪ ሠራተኛ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ ከተማዋ ስትመሠረት የሕዝቡ ኑሮ ኋላቀርና መንግሥትም ገንዘብ እንዳልነበረው፣ የከተማ አስተዳደሩ እሳቸውን የዞኑ መሪ አድርጎ ሲሾማቸውም የተመደበላቸው በጀት 500,000 ዩዋን ብቻ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ይህ በጀት የተሰጣቸው ግብርና መሩን ወደ ኢንዱስትሪ መር እንዲቀይሩ ነበር፡፡ ሚስተር ሼን ለጊዜው ጭንቀት ውስጥ ቢገቡም፣ ቻይና በወቅቱ የዕድገት ፖሊሲ በማወጅና ሪፎርም በማካሄድ አሠራሯን የለወጠችበት ወቅት ስለነበር፣ እሳቸውም ከነዋሪው ጋር ተባብረውና ጠንክረው በመሥራታቸው ለውጥ ማምጣታቸውን በኩራት ይናገራሉ፡፡

በቻይና የኢኮኖሚም ሆነ የሕዝቡ የኑሮ እንዲለወጥ ያደረጉ፣ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው እጅግ በጣም የሚደንቅ መከባበር ነው፡፡ ታናሽ ታላቁን የሚያከብርበትና ታላቅም ለታናሹ የሚሰጠውን ክብር እኛም በቆይታችን ታዝበናል፡፡ ሌላው በዕድሜ ትልቅም ይሁን ትንሽ አገርን በተሻለ መንገድ ያገለግላል ተብሎ ሹመት የተሰጠውን/የተሰጣትን ባለሥልጣንና ኃላፊ ማክበር ነው፡፡ በጎበኘናቸው የተለያዩ የልማትና መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች፣ ያላቸው መከባበርና ለሥራቸው የሚሰጡት ትኩረት የመንፈስ ቅናትን ያጭራል፡፡ በጉዞ ማስታወሻዬ ላይ ይበልጥ ትኩረት ያደረኩት በአገራችን ቀደምት ከሆነችው፣ በልዩ ስሟ ‹‹የፍቅር ከተማ›› ተብላ ከምትጠራው ድሬዳዋ ከተማ ጋር የእህትማማችነት ስምምነት መፈጸሟን ከነገርኳችሁ፣ የቻይናዋ የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ዞን ኩንሻን ከተማ ነው፡፡

የኩንሻን ከተማ መሥራች ተብለው የሚጠሩት ሚስተር ሼን፣ ከተማዋ ከ30 ዓመታት በፊት ስለነበረችበትና አሁን ስለደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ተናግረው አይጠግቡም፡፡ የእሳቸው መናገር ብቻ ሳይሆን፣ አብረዋቸው የነበሩ ሁሉ እሳቸው ሲናገሩ እነሱም በፈገግታና ፊታቸው ፈክቶ ነው የሚመለከቷቸው፡፡ በኋላቀር መሣሪያዎች የተጀመረው ሪፎርም ወደ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ የለውጥ ጉዞ እንዴት እንደተጀመረም ሚስተር ሼን ገልጸውልናል፡፡ መጀመርያ አርሶ አደሩን ሊለውጥ የሚችል የማዳበርያ ፋብሪካ መገንባቱንና በፍጥነት የአርሶ አደሩን የምርት ውጤት ለውጥ እንዲያመጣ መደረጉን ይናገራሉ፡፡ ሌላው ከተማዋን በፍጥነት እንድታድግና ልዩ መለያ (ብራንድ) እንዲኖራት ያደረጋት ሁሉም ነዋሪ ተከባብሮ፣ ተባብሮና በቆራጥነት መሥራት በመቻሉ ነው፡፡ ከማዕከላዊ መንግሥት ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ ሳታገኝ የተመነደገች ከተማ መሆኗ፣ የቻይና መንግሥትንና ሕዝብን ያስገረመች ከተማ እንድትሆን ማስቻሉን ሚስተር ሼን በደስታ ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከግብርና ሙሉ በሙሉ ተላቃ የኢንዱስትሪ ከተማ መሆኗን የሚናገሩት ሚስተር ሼን፣ በዕድገታቸው የመጀመርያ ዓመታት እ.ኤ.አ. በ1984 የግብርና መሣርያዎችንና የተለያዩ የመስታዎት ምርቶችን ከጃፓን ይገዙ እንደነበር፣ በወቅቱ ሁለትና ሦስት የነበሩት ኢንተርፕራይዞች አሁን ላይ 22,000 መድረሳቸውን፣ ከ30 ዓመታት በፊት የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶቿን ይገዟት ከነበረችው ጃፓን ጋር በአሁኑ ጊዜ በኢኮኖሚ በኩል ወዳጆች ቢሆኑም፣ በፖለቲካና በሌሎች በማይግባቡባቸው ነገሮች ደግሞ እንደወቅቱ ሁኔታ መሆናቸውን (መጐሻሸም መኖሩን) አልደበቁም፡፡

ሚስተር ሼን በዋናነት የኩንሻን ሲቲ ዕድገት ሚስጥርን አካፍለውናል፡፡ በከተማዋ በሥራ ላይ የተሰማሩ የአገር ውስጥም ይሁኑ የውጭ ኩባንያዎች ነፃነት አላቸው፡፡ የቻይና መንግሥት ነፃ ሆነው እንዲሠሩና ማንኛውም ዓይነት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር የዘረጋውን የልማት መንገድ አክብሯል፡፡ ከኩባንያዎቹ የሚጠበቀው ከትርፍ ገቢያቸው ላይ ሳይደብቁ፣ ሳያጭበረብሩና ሳይዋሹ ግብር መክፈል ብቻ ነው፡፡ እያደረጉትም ነው፡፡ ነፃ ሆነው ካልሠሩ የሚመኙትን ገቢ ሊያገኙ ስለማይችሉ መንግሥትም የሚያገኘው ነገር የለም፡፡ ከ35 ዓመታት በፊት መንግሥት በኩንሻን ሲቲ ከተሰማሩ ኩባንያዎች/ኢንተርፕራይዞች ያገኝ የነበረው የገቢ ግብር 100 ሚሊዮን አርኤምቢ (ሌላው የአገሪቱ ገንዘብ ስም ነው) ነበር፡፡ ዓምና ማዕከላዊ መንግሥት ያገኘው ገቢ ደግሞ 5.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ሚስተር ሼን ነግረውናል፡፡

ይህ ትርፍ የተመዘገበው ማዕከላዊ መንግሥት ኩባንያዎች ነፃ እንዲሆኑ በማድረጉና ጣልቃ ባለመግባቱ ነው፡፡ መንግሥት የውጭ ባለሀብቶችን ሲጋብዝ መጀመርያ መሠረተ ልማቶችን ማለትም መንገድ፣ ውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል መዘርጋት ከቻለ፣ ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ኢንዱስትሪ የሚገነቡበትን ቦታ ካገኙ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት እንደሚችሉ የጠቆሙት ሚስተር ሼን፣ ስለኢትዮጵያ ያላቸውን ትዝብት አካፍለውናል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆናቸውንና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን መጎብኘታቸውን ነግረውናል፡፡ የታዘቡት ነገር ቢኖር፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹን የገነባቸው መንግሥት መሆኑን ነው፡፡ እንደ ሚስተር ሼን አስተያየት፣ መንግሥት ፓርኮችን መገንባት የለበትም፡፡ መንግሥት መሠረተ ልማቶችን ብቻ ዘርግቶ የውጭ ባለሀብቶችን መጋበዝ አለበት፡፡ ባለሀብቶች በሚጠብቃቸው ቦታ ላይ የሚፈልጉትን የኢንዱስትሪ ግንባት በራሳቸው እንዲገነቡ ማድረግና ነፃነትቸውን ማወጅ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ፓርኮቹን በመገንባቱ፣ ባለሀብቶች ከሚሰሩት ስራና ከሚያመርቱት ምርት አሰራር ጋር ለማጣጣም አለመቻላቸውን እንደገነገሯቸውና እሳቸውም ካዩት ሁኔታ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ መሠረተ ልማቱ አልተሟላም፡፡ መንግሥት ለፓርኩ ግንባታ ከፍተኛ ወጪ ከሚያወጣ ይልቅ መገንባት ያለበት ወይም ሊያሳስበው ይገባ የነበረው ስለመሠረተ ልማቱ ነበር፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን በምሳሌነት መውሰድ ቢቻል፣ ፓርኩ መገንባት ያለበት በባለሙያ ሆኖ፣ የሠራተኛውንና የማሽኑ ሁኔታ ከግንዛቤ ገብቶ መሆን አለበት፡፡

በቻይና ከ3,000 በላይ የልማት ዞኖች ቢኖሩም፣ መንግሥት የማይክሮ ፖሊሲ ልማት ስትራቴጂ ከማውጣት ውጪ፣ የመቆጣጠር ሥራ ውስጥ እንደማይገባም ለማወቅ ችለናል፡፡ የሚከታተለውና ስለኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጣዊ አሠራር የሚመለከተው የከተማ አስተዳደር ብቻ መሆኑንም ተረድተናል፡፡ ከኩባንያዎቹ የሚገኘውን የታክስ ገቢ ማዕከላዊ መንግሥትና ኢንዱስትሪው ያለባቸው ዞኖች/የከተማ አስተዳደር ባላቸው ድርሻ መጠን ስለሚከፋፈሉ፣ የከተማ አስተዳደሩ ተነቃቅቶና ጠንክሮ እንዲሠራ ጉልበት እንደሚሆነው ሚስተር ሼን ይናገራሉ፡፡ ዞኖች በክልል መንግሥት ደረጃ መሆናቸው በሕግ የተወሰነ በመሆኑ፣ የከተማ አስተዳደሩ የሚቆጣጠረው ፖሊሲውና ስትራቴጂው መተግበሩን እንጂ፣ በሥራ ውስጥ ጣልቃ አይገባም፡፡ ለውጥና ዕድገት የሚመጣው በሥራ ጣልቃ በመግባትና በመቆጣጠር ሳይሆን፣ እንደ ቻይናው መሪ ቸርማን ማኦ አነጋገር ‹‹እውነተኛው ጀግና ሕዝብ ነው›› የሚለውን ጥቅስ መመርያ አድርጎ፣ ሌት ከቀን ሳይሰለቹ በመሥራት መሆኑን ሚስተር ሼን ይናገራሉ፡፡ የቻይና ሕዝብ ይህንን ተግባራዊ በማድረጉ ውጤታማ መሆኑን፣ ትንሿ የኩንሻን ከተማ ምስክር መሆኗን፣ ከተማውን ከ30 ዓመት በፊት ለማልማት ሲወጠን የከተማዋ ባለሥልጣናት ከፍተኛ ወርሃዊ ደመወዝ 56 ዩዋን መሁኑንና አሁን ጡረታ በወጡበት ወቅት 50,000 ዩዋን መድረሱንም ይናገራሉ፡፡

ከኩንሻን ሲት ሳንወጣ ‹‹ኩንሻን አውቶ ኤሌክትሮ ቪሌጅ›› ጎራ ብለን የመስተዋትና የሎኔቮ የላፕቶፕ ማምረቻዎች ኢንዲስትሪ ፓርክ ጎብኝተናል፡፡ ከአፈር እስከ ስሪዲ (3D) መስተዋት ድረስ እንዴት እንደሚመረት ማየት ከማስደነቅም አልፎ፣ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ዓመታት የልማት ጎዳና ውስጥ የት እንደደረሰችና ኩንሻን ሲቲ በተመሳሳይ ዓመታት ውስጥ ከተራ የግብርና መሳርያ መጠቀም ጀምሮ፣ አሁን የደረሰችበትን ደረጃ ከማነፃፀር ‹‹ዝም›› ማለትን ያስመርጣል፡፡

ሎኔቮ የተለያዩ መጠን ያላቸው የኮምፒዩተር ማምረቻ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከተበታተኑ ቁሳቁሶች ጀምሮ ተገጣጥሞ ሙሉ ላፕቶፕ ሆኖ ለሽያጭ ተዘጋጅቶ ያየነውም እዚሁ ነው፡፡ ፋብሪካው እጅግ በጣም ሰፊ መሆኑንና የሠራተኛውን ብዛት ላየ፣ ‹‹እንዴት ተግባብተው ነው የሚሠሩት?›› የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም፡፡ አንድ ሠራተኛ አንዷን የኮምፒዩተር ክፍል ብቻ ገጥማ/ገጥሞ ለቀጣዩ ከማስተላለፍ ውጪ ቀና ብለው እንኳን አይተያዩም፡፡ ሥራና ሠራተኛው የየሙያውን ሠርቶ በማስተላለፍ የመጨረሻውን ውጤት በአጭር ሰዓት ማየታችን ካስገረሙን የጉብኝታችን መዳረሻዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡

የኩንሻን ሲቲ ጉብኝታችንን አጠናቀን በሰዓት 349 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ባለውና ከፊት ለፊቱ ሲያዩት የእባብ መልክ በተቀረጸው እጅግ ፈጣን ባቡር ተሳፍረን፣ ጉዟችንን የመንግሥት መቀመጫ ወደሆነችው ቤጂንግ አደረግን፡፡ ረዥሙን የባቡር ጉዞ አድርገን፣ በጉዞ የደከመ አካላችንን ያሳረፍነው በሻንጋሪላ ዓለም አቀፍ ሆቴል ነው፡፡ በቤጂንግ የመጀመርያው ጉብኝታችን በአሁኑ ጊዜ ራሱን ችሎና እ.ኤ.አ. በ2007 ተቋቁሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ101 የዓለም አገሮች ላይ የተለያዩ የግንባት ፕሮጀክቶችን በመሥራት ላይ የሚገኘውን የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ግንባታ ኮርፖሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት ነበር፡፡

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ሊዩ ዶንግ ቢሮ በሚገኝበት ሕንፃ ላይ እ.ኤ.አ. ከ1948 እስካሁን ድረስ ያለውን የቻይናን የመንገድና የባቡር ሃዲድ ግንባታ የሚዘክር ሙዚየም ይገኛል፡፡ ሬልዌ ሪሀብሊቴሽን ኢንጂነሪንግ ቢሮን ይመሩት ከነበሩት ሁዋንግ ይፈንግ ጀምሮ ሲአርሲሲና ሲሲኢሲሲን እየመሩ ያሉትን ኃላፊዎች ጨምሮ አሁን ላሉበት ዘመናዊ የከተማ መንገዶችና የባቡር ሀዲድ ግንባታዎች ሒደት ውስጥ ያጋጠማቸውን ከሞት እስከ አካል ጉድለት ድረስ የሚዘክሩ በመግለጫ የተደገፉ ፎቶግራፎች ተቀምጠዋል፡፡

ሒደቶቹን ለሚመለከት ዕድገትና ለውጥ ዝም ብሎ የሚመጣ ሳይሆን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የሚጠይቅ መሆኑን የሚያስተምር ነው፡፡ የሲሲኢሲሲ ሙዚየም ጉብኝታችንን ያጠቃለልነው በምክትል ፕሬዚዳንቱ ሚስተር ሊዩ ዶንግ ቢሮ ተገኝተን፣ በኢትዮጵያ፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በሌሎች ዓለማት ሲሲአርሲሲና ሲሲኢሲሲ የገነቧቸውን የባቡር ሃዲድ፣ መንገዶች ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሌሎች ዘመናዊ ግንባታዎችን የሚያሳይ አጭር ቪዲዮ በመመልከት ነው፡፡

ቻይናውያን በየብስ ላይ የሚገነቡት ወይም የሚሠሩት ላይ ብቻ አልቆሙም፡፡ ባህርን ሰንጥቀው ወይም በባህር ውስጥ የሚተላለፍ የባቡር ሃዲድ በመገንባት፣ አንዱን ጫፍ ከሌላኛው ጫፍ ጋር ማገናኘታቸው የቅርብ ጊዜ ዜና እንደነበር ይታወሳል፡፡ ቻይናውያን አሁን ደግሞ ከመሬት እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ በመቆፈር፣ ውስጥ ለውስጥ የሚተላለፍ የባቡር ሃዲድ በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ እኔና አብረውኝ የተጓዙ ቡድኖች ማረጋገጥ የቻልነው ይህንኑ ነው፡፡ በመሀል ቤጂንግ ‹‹ቤጂንግ ሰብዌይ ላይን ቁጥር 19 (Beijing Subway No19) የተባለ ፕሮጀክት ሲሠራ ያገኘነው በተለይ በባቡር ሃዲድ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራውን ሲአርሲሲ 14ኛን ነው፡፡ ሲአርሲሲ በቤጂንግ ከተገነቡ ጥንታዊና ዘመናዊ ሕንፃዎች ወደ መሬት ሰማንያ ሜትር ወርዶ የባቡር ሃዲድ በመገንባት ላይ ነው፡፡ የመጀመርያውን ዙር 22 ኪሎ ሜትር የገነባ ሲሆን፣ በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ያለው ባቡር የሚበርበትን አሥር ጣቢያዎችን ያገናኛል፡፡ እጅግ ግዙፍ የሆነ የዋሻ መፈልፈያ መሣርያን ያየ ‹‹እውነት ይህ መሣርያ በሰው ልጆች የሚንቀሳቀስ ነው?›› ብሎ የማይጠይቅ አይገኝም፡፡ በአጠቃላይ የቻይና መንግሥት ተቋማት የሆኑት ሲአርሲሲ እና ሲሲኢሲሲ በአገራቸውም ይሁን በሌሎች አገሮች እየሠሩት ያለው የተለያዩ ግንባታዎች ‹‹ይሁን›› የሚያሰኙ ናቸው፡፡

የመሰናበቻ እራት በቻይና ልዩ የሙዚቃ ቡድን አባላት ልዩ የሙዚቃ ቃና በሮያል ጋስትሮኖሚ ሙዚየም በሲሲኢሲሲ ፕሬዚዳንት ጋባዥነት ተስተናግደን፣ የቻይና ጉብኝታችንን አጠናቀቅን፡፡ ‹‹ዞሮ ዞሮ ከቤት…›› እንዲሉ፣ ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሳችን በፊት የመጨረሻ መዳረሻችን የቻይና ራዲዮ ኢንተርናሽናልና የቻይና ኮሙዩኒኬሽን ዩኒቨርሲቲ ነበሩ፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኘውን ቻይና ራዲዮ ኢንተርናሽናል ዘመናዊ ስቱዲዮ ካየንና ምክትል ፕሬዚዳንቷን ሚስስ ጋውል ያንጆን ስለ አሠራራቸው ካነጋገርናቸው በኋላ፣ ጉዟችን እጅግ በጣም ሰፊና የተለያዩ የኮሙዩኒኬሽን ዲፓርትመንቶች ያሉት የቻይና ኮሙዩኒኬሽን ዩኒቨርሲቲ (ሲዩሲ) አደረግን፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአራት ኪሎና ስድስት ኪሎ ግቢዎች ቢደመሩ የማይደራረሱት ስፋት ያለው ሲዩሲ ትምህርትን ከተግባር ልምምድ ጋር ያጣመረ ሥልጠና የሚሰጥ ልዩ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለበርካታ አገሮች የድኅረ ምረቃ የትምህርት ዕድል እንዲሁም ነፃ ለአንድ ወር የሚቆይ ሥልጠና ለበርካታ ጋዜጠኞችና ለሌሎችም ይሰጣል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠውን ጨምሮ ከኤርትራ፣ ደቡብ አፍሪካና ከሌሎችም አገሮች የተውጣጡ ተማሪዎች ታድመው ሲማሩ አገኘናቸው፡፡ ደስም አለን፡፡

ዩኒቨርሲቲው በበርካታ ፕሮፌሰሮችና ብቁ መምህራን የተጠናከረ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በተግባር ሥልጠና የሚሰጥበት ቀጥታ ሥርጭት የሚሠራበት ስቱዲዮው እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ከ600 በላይ መብራቶች የያዘው ሰፊ ስቱዲዮ የስካይ ላይት ሆቴል ትልቁ የመሰብሰቢያ አዳራሽን ያክላል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ እኔም ለራሴ አደላሁና ‹‹ምናለበት በአገሬ በሆነ›› አልኩኝ፡፡ በኢትዮጵያ የሲሲኢሲሲ ባልደረባ አመለሸጋው ካን ሮንጂዮ የተመራው ቡድናችን የመጨረሻውን የጉብኝት ስንብት በቅርቡ ማስፋፊያውን ባስመረቀው ቤጂንግ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አድርጎ ወደ እናት ምድሩ ተመልሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...