Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዘርና ሃይማኖትን መነሻ በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጠረጠሩ ለፍርድ ሊቀርቡ ነው

ዘርና ሃይማኖትን መነሻ በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጠረጠሩ ለፍርድ ሊቀርቡ ነው

ቀን:

ዋነኛ ጠንሳሾች ቢታወቁም ለመያዝ እንዳልተቻለ ተጠቁሟል

በባለሥልጣናትና በባለሀብቶች የሸሹ ንብረቶችን ለማስመለስ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል

ከሁለት ወራት በፊት ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በአዳማ፣ በሰበታና በአዲስ አበባ ከተማ ዘርና ሃይማኖትን መነሻ በማድረግ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሕይወታቸው ባለፈና በአካላቸው ላይ ጉዳት በደረሰ ወገኖችና በግለሰቦች፣ በሕዝብና በመንግሥት ንብረቶች ውድመት የተጠረጠሩ 250 ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ዓርብ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፣ ጥቅምት 12 እና 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለይ በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎችና በአዲስ አበባ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ ‹‹የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በርካታ ወገኖች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ንብረት ወድሟል፣ ተዘርፏል፡፡ በወገኖች ላይ ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ይህ ሁሉ የወንጀል ድርጊት የተፈጸመው ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት በማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ድርጊት የፈጸሙ አካላት ሆን ብለው ሕዝቡ ወደ ሽብር እንዲገባና ለሽብር ጥቃት እንዲነሳሳ ለማድረግ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ግን የቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስ ጥቃቱ ሊቆም መቻሉን አክለዋል፡፡

ከፌዴራል መንግሥት፣ ከክልልና ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተውጣጣ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል ከ330 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር አቶ ዝናቡ ተናግረዋል፡፡ በተደረገው ተጨማሪ ምርመራ 250 ተጠርጣሪዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉትም ከሕግ ተጠያቂነት ስለማያመልጡ ኅብረተሰቡ በጉያው ከመደበቅ ይልቅ አጋልጦ በመስጠት አጋርነቱን እንዲያሳይ ጠይቀው፣ በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በደረሰ ጥቃት የተጠረጠሩ በየጎጣቸው በመደበቃቸው በቁጥጥር ሥር ለማዋል ችግር እንደገጠመ ጠቁመዋል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የወንጀል ድርጊት እየተበራከተ መምጣቱን ያስረዱት አቶ ዝናቡ፣ የጥፋት ኃይሎች ገንዘብ መድበው ዘርን መሠረት ያደረገ ብጥብጥ እንዲፈጥሩ እያደረጓቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር የምርምር ቡድን በማቋቋም  ባደረገው ምርመራ፣ በወልዲያ፣ በወሎና በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች በጥቅምትና በኅዳር ወር የተፈጠሩ ግጭቶች ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን የሚያሳዩ ፍንጮች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በብጥብጡ ከሚወድመው የሕዝብና የመንግሥት ንብረት በተጨማሪ፣ ተማሪዎች የአካል ጉዳትና የሥነ ልቦና ጫና እንዲደርስባቸው ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ በተጠቀሱት ዩኒቨርሲቲዎች በቀጥታ ከብጥብጡ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 16 ተጠርጣሪዎች በምርመራ ላይ እንደሚገኙም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ዘርና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው የሚቀሰቅሱትን ዋናዎቹ የድርጊቱ ጠንሳሾች እየታወቁ በቁጥጥር ሥር የሚውሉት ግን በጅምላ ተሳትፈዋል የተባሉት ብቻ የሚሆኑበትን ምክንያት ተጠይቀው፣ ‹‹እነሱን መለየት አልተቻለም፣ አንዳንዶቹን ግን ለይተናቸዋል፡፡ በሌሉበትም የከሰስናቸው አሉ፤›› ከማለት ባለፈ፣ ‹‹እከሌ ይባላሉ፣ ያልተያዙበት ምክንያት ይህ ነው፤›› አላሉም፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሌላው በትኩረት እየሠራበት ያለው ጉዳይ ሙስናን በሚመለከት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዝናቡ፣ በሕዝብና በመንግሥት ሀብት ላይ ሙስና የፈፀሙ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸው ላይ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከመክሰስና ከማስቀጣት ባለፈ ጥፋተኛ መሆናቸው ሲረጋገጥ፣ በሕገወጥ መንገድ ያገኙት ሀብት ለመንግሥት ተመላሽ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ውሳኔ ካረፈባቸው የሙስና ተከሳሾች 50 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ማስመለስ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ ከዋና ኦዲተር ግኝት በመነሳት ከተመደበላቸው ዓመታዊ በጀት በሙስና ያጠፉትን 312 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትም እንዲመለስ መደረጉንም አክለዋል፡፡ በመንግሥት ባለሥልጣናትና ተባባሪዎቻቸው ወደ ውጭ አገር ከተሻገረ ሀብት ውስጥ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ለማስመለስ ከአገሮቹ ጋር ውይይትና ስምምነት መደረሱን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም በበርካታ የሙስና ፋይሎች ላይ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡ በጥሬ ገንዘብና በቁሳቁስ ምን ያህል ንብረቶች እንደባከኑና ወደ ውጭ እንደሸሹ የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዋናነት በሕግ ሪፎርም ላይ እየሠራ በርካታ ሕጎችን በማርቀቅና በማሻሻል ላይ መሆኑን ጠቁመው የጥላቻ ንግግር አዋጅ፣ የፌዴራል ተቋማት አስተዳደር አዋጅና ሌሎችም ረቂቅ አዋጆች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለቋሚ ኮሚቴ መመራታቸውንም አቶ ዝናቡ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...