Thursday, February 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ከፍ ብሎ መገኘት ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ሳተላይቷን ዓርብ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቻይና ወደ ህዋ እንዲመነጠቅ አድርጋለች፡፡ ይህ እጅግ በጣም ደስ የሚል ተግባር ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ከፍታ የሚያንደረድር ነው፡፡ እንደሚታወቀው የህዋ ሳይንስ ምርምርና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለታዳጊ አገሮች ቅንጦት አይደለም፡፡ ሳተላይትን ከመሬት ወደ ህዋ በማምጠቅ የውኃ አካላትን፣ የብስንና ከባቢ አየርን በማጥናት ጠቃሚ መረጃዎች ማግኘት መቻል ከኢንቨስትመንት በተጨማሪ ጥረት ይፈልጋል፡፡ በዚህም መሠረት ለጤና፣ ለትራንስፖርት፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለግብርና፣ ለኢነርጂ፣ ለማዕድናት፣ ለኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለብሔራዊ ደኅንነት፣ ለምርምርና ለመሳሰሉት ተግባራት የራስን ሳተላይት ማምጠቅ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከአዲሱ ሳተላይት በርካታ ጠቀሜታዎች እንደምታገኝ ተስፋ ይደረጋል፡፡ ታዳጊዎችና ወጣቶች በህዋ ሳይንስ ትምህርት በብዛትና በጥራት እየተማሩና እየተመረቁ፣ የምርምር ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ፣ በአገር ውስጥ የህዋ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች እየተስፋፉ፣ የሳተላይት መፈብረኪያዎች እየተከፈቱና ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች አገሮች መትረፍ የሚቻልበት ደረጃ ላይ መገኘትም ሌላው ግብ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህንን ታላቅ ተግባር ከጥንስሱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያከናወኑ ወገኖች በሙሉ ሊመሠገኑ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ ስሟ ሲነሳና የነገ ተስፋዋ ሲበሰር ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ማስደሰት አለበት፡፡ ከደስታው በመለስ ደግሞ ሌሎች ጉዳዮችን እያነሱ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውጤት ለማግኘት፣ ተወዳዳሪ ለመሆን፣ የተፈጥሮ ሀብትን በሚገባ ለመጠቀምና ከድህነት ለመውጣት ዓይንንም ልብንም መክፈት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ለከፍታ የሚያበቃ አስተሳሰብ የግድ ይሆናል፡፡

ዘወትር እንደምንለው ኢትዮጵያ ከሥራ ባህል ውጪ ምንም የጎደላት ነገር የለም፡፡ የሥራ ባህልን መሠረት ለማስያዝ ጥራት ያለው ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ሲኖር ጥራዝ ነጠቅነት ሥፍራ አያገኝም፡፡ በአስተማማኝ ዕውቀት የሚገነባ ማኅበረሰብን ለሥራ ማዘጋጀት በጣም ቀላል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማኅበረሰብ በሥርዓት መኖር የሚችል፣ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ለምክንያታዊነት የሚያደላ፣ ባልተረጋገጠ መረጃ የማይተራመስ፣ የሚጠይቅና የሚሞግት፣ እንዲሁም ለሞራልና ለሥነ ምግባር ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጥ ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ሕይወቱ በከፍተኛ ዲሲፕሊን የታነፀ ይሆናል፡፡ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም ይልቅ ለአገር ጥቅም ቅድሚያ ከመስጠቱም በላይ፣ ለፀብና ለጭቅጭቅ ቦታ አይሰጥም፡፡ በመርህ መመራትና በሥርዓት መኖርን የለመደ ማኅበረሰብ ለሥራ ትልቅ ክብር አለው፡፡ ሠርተው የሚያሠሩ መሪዎችን ይፈልጋል፡፡ ሁሌም የሚተጋው ለዕድገት ነው፡፡ ዕድገት የሚገኘው በትምህርት በመሆኑ ትውልዱን ጥራት ባለው ትምህርት ለማነፅ ይተጋል፡፡ ለነገዎቹ በርካታ ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች የምትመች አገር ያዘጋጃል እንጂ፣ በማይረቡ ምክንያቶች እየተጋጨ አገር ለማፍረስ አይሯሯጥም፡፡ የነገውን ባለ ሙሉ ሰብዕና ትውልድ ያፈራል እንጂ፣ አገር የሚያዋርድና የሚያተራምስ ትውልድ አይፈጥርም፡፡ ኢትዮጵያም የምትፈልገው ይህንን ዓይነቱን ከፍታ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሳተላይት ወደ ህዋ ልካ ለሁለንተናዊ ዕድገቷ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ማሰባሰብና መጠቀም ስትጀምርና በርካታ ወጣት ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች በሥራ ገበታ ላይ ሲሆኑ፣ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያንም አኩሪ ተግባር በመፈጸም አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ ፖለቲከኞች የፓርቲ ፖለቲካ ሥራቸውን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እያከናወኑ፣ የነገዋ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ዘመኑ የሥልጣኔ ነው እየተባለ በዘመነ መሣፍንት አስተሳሰብ መገኘት የለባቸውም፡፡ ከመሰሪነት፣ ከጥላቻ፣ ከቂም በቀልና ከኋላቀር ድርጊቶች መላቀቅ አለባቸው፡፡ ካላስፈላጊ ግጭቶችና ትርምሶች በመውጣት ለውይይት፣ ለክርክርና ለድርድር ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክሮች ብቁ ለመሆን ዝግጅት ቢያደርጉ ይመረጣል፡፡ የታሪክ ስንክሳሮችን እያገላበጡ ባልነበሩበት ዘመን ላይ ከመወዛገብ፣ ዛሬ ከእነሱ የሚፈለገውን ለመወጣት ቢተጉ ያስከብራቸዋል፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ በትናንት ስህተቶች ጊዜ ከማባከንና ራስን ከማስገመት መውጣት ይሻላቸዋል፡፡ ሕዝብ ዳኝነቱን የሚሰጠው ዛሬ ለሚከናወን ተግባር እንጂ፣ ለትናንቱ ጥፋት ውግዘት አይደለም፡፡ ዛሬ ሳይሠሩ ትናንትን መወንጀል ስንፍና ነው፡፡ ዘመኑ ደግሞ ሰነፎችን አይታገስም፡፡ ስለዚህ ፖለቲከኞች ሆይ ወደ ቀልባችሁ ተመልሳችሁ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላችሁን ተወጡ፡፡ ካልቻላችሁ ደግሞ ለሚችሉት ተውላቸው፡፡ አዲሱን ትውልድ በአሮጌ ታክቲክ ለማታለል አትሞክሩ፡፡ የዘመኑን ነገር ለዘመኑ ትውልድ ተውለት፡፡ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ይህንን ከፍ ያለ ሐሳብ ነው፡፡

ከእያንዳንዱ ግለሰብ ጀምሮ መንግሥትን እስከሚመሩ ሰዎች ድረስ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሥርዓት የሚጀምረው ከራስ ነው፡፡ ራስን ለትልቅ ዓላማ ሳያዘጋጁ የሚሠራን መኮርኮም፣ ማበሳጨትና ተስፋ ማስቆረጥ ተገቢ አይደለም፡፡ የሚሠራ ሰው መከበር አለበት፡፡ አገር የሚዘርፉ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ እንደ ልባቸው እየሆኑ፣ ንፁኃንን በተለያዩ መንገዶች ማስመረር መቅረት አለበት፡፡ የአገሪቱን መሬት በግላጭ እየወረሩ የሚሸጡ፣ የመንግሥት ካዝና የሚያራቁቱ፣ ፕሮጀክቶችን ከጥራት ደረጃቸው በታች በማከናወን ሌብነት የሚፈጽሙ፣ በቡድን በመደራጀት የአገር ሀብት የሚያግዙ፣ ግብር የሚሰውሩ፣ ጥራት የሌላቸው ዕቃዎችን በገፍ ከውጭ የሚያስገቡ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችንና ምግቦችን የሚሸጡ፣ ሚዛን የሚያጭበረብሩ፣ ተሽከርካሪዎችንና የተለያዩ ንብረቶችን ተደራጅተው የሚዘርፉና በአጠቃላይ በአቋራጭ ለመክበር ከሰማይ በታች ያሉ ኃጢያቶችን የሚፈጽሙ በሕግ አደብ ሊገዙ ይገባል፡፡ ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ከሕግ በላይ የሆኑ ጉልበተኞችን መንግሥት ሥርዓት ማስያዝ አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት በሕገወጥነት ላይ የበላይ መሆን ካልቻለ ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሣል፡፡ ኢትዮጵያ ሌቦችንና ዘራፊዎችን የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም፡፡ አዲሱን ትውልድ በሥርዓት መቅረፅ ከተፈለገ፣ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ያለባቸውን ግለሰቦችና ስብስቦች በሕግ አደብ ማስገዛት የግድ ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሌቦችና ዘራፊዎች አንቱ እየተባሉ እንደፈለጋቸው ሲሆኑ፣ ምስኪኑ ታታሪ ዜጋ ግን እንደ ቆሻሻና አልባሌ ነገር ይቆጠራል፡፡ ይህ በፍፁም ትዕግሥት የማያስፈልገው ድርጊት ነው፡፡ ለኢትዮጵያም አይጠቅማትም፡፡ ከፍ ለማለት ከዝቅጠት ውስጥ መውጣት የግድ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ የከፍታ ጊዜ እየመጣ ለመሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ማመላከቻዎች ይታያሉ፡፡ በረሃብ፣ በጦርነት፣ በኋላቀርነትና በተለያዩ መከራዎች ስሟ ይነሳ የነበረ አገር አሁን ገጽታዋ እየተቀየረ ነው፡፡ እዚህና እዚያ በአሳቻ ጊዜ የሚነሱ ግጭቶችንና ውድመቶችን ማስቆም ከተቻለ የከፍታው ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ የነፃነት፣ የፍትሕ፣ የልማትና የእኩልነት አገር እንድትሆን በአንድ ላይ መነሳት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያን እየተፋቀሩ፣ እየተሳሰቡ፣ እየተከባበሩና በኅብረት እየሠሩ መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓድዋ ጦርነት ድል ታላቅ ምስክር ነው፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችና በጭቆና ቀንበር ለነበሩ ሁሉ ታላቅ ተምሳሌት የነበረችው ኢትዮጵያ ከተሠራባት፣ እንኳን በአፍሪካ በዓለም ደማቅ ሆና መታየት ትችላለች፡፡ ከወሬ፣ ከአሉባልታ፣ ከሐሜት፣ ከሴራ፣ ከጥላቻ፣ ከቂም በቀልና በአጠቃላይ ለዕድገት ከማይጠቅሙ አላስፈላጊ ድርጊቶች በመራቅ የሥራን ክቡርነት ማንገሥ ተገቢ ነው፡፡ ወጣቱን ጥራት ያለው ትምህርት በመመገብ አስተማማኝ ዕውቀት ማስጨበጥ ይገባል፡፡ ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ ዋነኛው ቁልፍ ዕውቀት ነው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ብርቱ ተፎካካሪ ለመሆን መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በሞራልና በሥነ ምግባር በመታነፅ ነገን ማቀድ የብልሆች ተግባር ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ በአንድነት መነሳት ሲቻል ደግሞ፣ የሚገኘው ውጤት እጅግ በጣም አስደማሚ እንደሚሆን መጠራጠር አይገባም፡፡ አሁን ከቻይና ሳተላይት ያመጠቀችው ኢትዮጵያ፣ ነገ ከገዛ መሬቷ ራሷ የሠራቻቸውን ሳተላይቶች ማመንጠቅ እንደምትችል ተስፋ ሊኖር ይገባል፡፡ ከፍታ የሚገኘው በሥራ ስለሆነ ለሥራ ታጥቆ መነሳት የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ከፍ ብሎ መገኘት ይገባል የሚባለው ለዚህ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነፃነትና የአንድነት ትዕምርት እንጂ የድህነትና የጉስቁልና ምክንያት አይደለችም!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ማሳሰቢያ ይህ ጽሑፍ የፕሮቴስታንት ሃይማኖትን እምነትን አስተምህሮ...

ሕዝብ በሌለበት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድ መባሉን እንደማይቀበለው የቁጫ ምርጫ ክልል አስታወቀ

በኢዮብ ትኩዬ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ይካሄዳል የተባለውን ‹‹የደቡብ...

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ላደረሰው ኪሳራ ክስ ተመሠረተበት

ኩባንያው በግማሽ ዓመት ስምንት ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገልጿል ኢትዮ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ማስተካከያ

በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም...

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...