Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት አሰጣጥ ግራ እያጋባቸው መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት አሰጣጥ ግራ እያጋባቸው መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማው ዋነኛ ሀብት የሆነውን መሬት ያለበትን ሁኔታ ኦዲት አድርጎ እስከሚጨርስ፣ ‹‹በጨረታም ይሁን በምደባ›› መሬት መስጠት ማቋረጡን ያስታወሱ ነዋሪዎች፣ በአሁኑ ጊዜ ግን በከተማዋ እምብርት የሚገኙ መሬቶች እየታጠሩና እየተቆፈሩ መሆናቸውን ሲመለከቱ፣ በምን ሁኔታ እየተሰጡ እንደሆነ ግራ መጋባታቸውን ገለጹ፡፡

ምንም እንኳን አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት 2011 ዓ.ም. መጠናቀቂያ አካባቢ ለጊዜው መሬት መስጠቱን ካሳወቀበት ጊዜ ጀምሮ ለተወሰኑ ወራት ስለመሬት ምንም ዓይነት መረጃ መስጠት የቆመ ቢሆንም፣ ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ ግን በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ወረራ በሚመስል ሁኔታ ለአረንጓዴ ቦታነት የተተው መሬቶች ሳይቀሩ በግለሰቦች እየታጠሩ መሆኑን ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሰለሞን በቀለ (ዶ/ር)፣ አቶ ታደሰ ኃይሉ፣ አቶ ሙሉጌታ ጉልማና ወ/ሮ ጫልቱ ወርዶፋ የተባሉ ነዋሪዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ በሁለት መንገድ መሬት ይሰጣል፡፡ በጨረታና በምደባ፡፡ በጨረታ የሚሰጠው መሬት ለንግድና ለሪል ስቴት ልማት ሲሆን፣ በምደባ የሚሰጠው ደግሞ ለኢንዱስትሪ መገንቢያ፣ ለሕክምና፣ ለትምህርት ቤቶችና በአጠቃላይ ለሕዝብ አገልግሎት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን እየታጠሩና እየተቆፈሩ የሚታዩት ቦታዎች፣ በመሀል ከተማ ለንግድና ለተለያዩ አገልግሎቶቸ የሚውሉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ ቦታዎች በምደባ የሚሰጡ ሳይሆኑ በጨረታ ሊሆን እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡  በተለይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ ወይም በቦሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ወደ ውስጥ መቶ ሜትር ገባ ብሎ የሚገኝ ሰፊ መሬት በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡ መሬቱ መሀል ቦሌ ላይ ከመሆኑ አንፃር፣ ለዘመናት ምንም ዓይነት ግንባታ ሳይደረግበት ቆይቷል፡፡

በምክንያትነት ይጠቀስ የነበረው ደግሞ ቦታው ለበርካታ አገሮች ኤምባሲዎች ሕንፃ መገንቢያ መሰጠቱ ነበር፡፡ አገሮቹ ምክንያቱ ባይታወቅም ከጂቡቲ በስተቀር ሌሎች ሳይገነቡበት በመቆየታቸው፣ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ መሬቱ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ በማድረግ፣ ቀይ አሸዋ ፈሶበት ጊዜያዊ የተሽከርካሪዎች መቆሚያ ሆኖ ነበር፡፡

የከተማው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ሰሞኑን ቦታዎቹ እንዴትና ለማን እንደተላለፉ ባይታወቅም ተሸንሽነው ታጥረዋል፡፡ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ሀብት በመሆኑ አገልግሎት ላይ ሲውል በግልጽ መነገር እንዳለበትም አክለዋል፡፡

ቢር ጋርደን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የነበረ ሰፊ ቦታ ለአካባቢው ሆቴሎችና ለተለያዩ ተቋማት መኪና ማቆሚያና አረንጓዴ ቦታ ሆኖ ያገለግል የነበረ ቢሆንም፣ በማንና በምን ምክንያት እንደሆነ ሳይታወቅ በትራክተር መታረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡ ከቅርብ ወራት ወዲህ በየካ ክፍለ ከተማ አያት፣ ሲኤምሲ አካባቢዎችና ዳርዳሩን መውጫ አካባቢዎች ባዶ ቦታዎች በግለሰቦች እየታጠሩ መሆኑን በኮልፌ ቀራንዮ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በጉለሌ ክፍላተ ከተሞች ወረራ በሚመስል ሁኔታ መሬቶች እየታጠሩ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ የ1997 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫን ተከትሎ በከተማው ያሉ መሬቶች በሕገወጥ መንገድ ለግለሰቦች መተላለፋቸውን በማስታወስ ሥጋት እንደገባቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ የሚያነሱትን ጥያቄና ያደረባቸውን ሥጋት በሚመለከት ሪፖርተር ማብራሪያ ለማግኘት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሸናፊን ኃይሉን ለማግኘት ጥረት አድርጓል፡፡ አቶ አሸናፊን በአጭር የጽሑፍ መልዕክት የተገኙ ቢሆንም፣ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው መረጃውን ከመሬት ባንክ ኃላፊዋ ወ/ሪት ኢየሩሳሌም ሽመልስ ማግኘት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡ አስተዳደሩ የመሬት ኦዲት ያደርግ እንደነበር ወ/ሪት ኢየሩሳሌም አስታውሰው፣ አሁን ግን መስጠት ያቆመውን የተወሰነውን በምደባ መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ለማንና እንዴት እንደተሰጠ ማብራራት ባይችሉም፣ በክፍላተ ከተሞች 14 ቦታዎች ብቻ መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...