Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢትዮጵያ ያመጠቀቻት ሳተላይት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖራት ተገለጸ

ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት ሳተላይት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖራት ተገለጸ

ቀን:

እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2015 በተፈረመ ስምምነት መሠረት ዕውን ሆና በቻይና መንግሥት በስምንት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ዓርብ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ህዋ የመጠቀችው ሳተላይት፣ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደምታስገኝ ተገለጸ፡፡

ይህች 72 ኪሎ ግራም የምትመዝነው የመሬት ምልከታ ሳተላይት በሰሜን ቻይና ከተማ ሻንግዚ ግዛት ከሚገኘው የታዩአን ሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ሎንግ ማርች ፎር ቢ (Long March 4B) በተባለ ሮኬት ተሸካሚነት ወደ ህዋ መጥቃለች፡፡ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠር፣ ከግብርና ጋር የተያያዙ ጥናትና ምርምሮች ለማካሄድና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ታስችላለች ተብሏል፡፡ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ የኮሙዩኒኬሽንና የብሮድካስት ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ከቻይና ወደ ህዋ የመጠቀችው ሳተላይት በአጠቃላይ ግንባታዋ ከንድፍ አንስቶ ሁለት ዓመታትን የፈጀ ሲሆን፣ በንድፍና በግንባታ ሒደት 21 ኢትዮጵያውያን የሥልጠና ተሳትፎ አድርገውበታል፡፡ “ETRSS-1” የሚል መጠሪያ የተሰጣት ሳተላይት የመጠቀችው ከቻይና ቢሆንም፣ የሳተላይቱ የመቆጣጠሪያና የአንቴና ክፍሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው የሚገኘው መረጃ ለግብርና፣ ለአደጋ መከላከልና ለመሳሰሉ ጉዳዮች ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአፍሪካ እስካሁን ሰባት አገሮች ብቻ ሳተላይት ያመጠቁ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ሳተላይት በማምጠቅም ከአኅጉሪቱ ስምንተኛ ሥፍራን ይዛለች፡፡ ይህች ሳተላይትም በቀጥታ ከምትሰጠው ጠቀሜታ ባለፈም የቴክኖሎጂ አቅምን በመገንባት፣ የወደፊት የሳተላይት ግንባታንና ማምጠቅን በራስ አቅም ማከናወን የሚያስችል ጠቀሜታ ይኖራታል ተብሏል፡፡

ከዚህ አኳያም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና ኤርያል ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሳተላይት መገጣጠሚያና መሞከሪያ ጣቢያ ለመገንባት በትብብር እየሠሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናት ከኅዳር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ሲከናወን እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአሁኑ ሳተላይት ማምጠቅ ከሲቪል ጠቀሜታዎች ባለፈም ኢትዮጵያ በሒደት ልትገነባው ለምታስበው የህዋ መከላከያ ኃይል በር ከፋች ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዓለም የጦርነት ዓውዶች ከተለመደው ወጣ በማለት ወደ ሳይበርና ወደ ህዋ እየተቀየሩ ስለሆነ፣ በዚህ ዘርፍ ጠንካራ የመከላከል አቅምን መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ በማተት፣ የህዋ መከላከያ ክፍል በአገር መከላከያ ሠራዊት እንደሚቋቋም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ከዚህ ፍላጎት ጋር በሚመጋገብ ሁኔታ የዛሬ ዓመት ገደማ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)፣ ከቻይና የስፔስና የሳይበር ደኅንነት ተቋም ጋር የትብብር ውይይት አድርገው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሳተላይት ወደ ህዋ ከመጠቀች ከሦስት እስከ አምስት ባሉ ቀናት ምህዋሯን ይዛ መረጃዎችን ከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት ባለው ካሜራ ፎቶ እያነሳች ወደ ዕንጦጦ መቀበያ ማዕከል መላክ ትጀምራለች ተብሏል፡፡ ሳተላይቷ በቻይና ቁጥጥር ሥር ሆና መረጃ ወደ ዕንጦጦ ማዕከል መላኳ በአንዳንዶች ዘንድ ሥጋት ቢፈጥርም፣ አቅምን መገንባት እስከሚቻል ድረስ በሳተላይቷ መጠቀም አማራጭ የለውም የሚሉ ድምፆች ተሰምተዋል፡፡

የሳተላይቶች ዋጋና መጠን እያነሰ በመጣ ቁጥር በርካታ አገሮች ሳተላይት የማምጠቅ ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ እንደ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካና ሞሮኮ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ያመጠቁና ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ ካሉ አገሮች ተርታ ይገኛሉ፡፡ ይኼ ፍላጎትም በአፍሪካ ኅብረት የስፔስ ፖሊሲ የሚደገፍ ሲሆን፣ የሳተላይት ግንኙነቶችን ለኢኮኖሚ ልማት መጠቀምን በእጅጉ ያበረታታል፡፡

የሳተላይቷን ጠቀሜታ በሚመለከት ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት ዚነሲስ ቴክኖሎጂስ የተባለው የመረጃ ትንታኔ ላይ የሚያተኩር ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ካሳ፣ ‹‹የETRSS-1 ሳተላይት መምጠቅ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ነው፤›› ብለው፣ በተለይም ከመረጃ (Data) አኳያ ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዳዊት እንደሚሉት ሳተላይቷ ለኢትዮጵያ በአየር ንብረት፣ በደን ሀብትና በተለያዩ ዘርፎች ቀዳማዊ መረጃን በመሰብሰብ የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ ታግዛለች፡፡

‹‹አዲሱ መረጃ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለነበራት መረጃ ትልቅ ጭማሪ ነው የሚሆነው፡፡ መረጃ ደግሞ ኃይል ነው፡፡ የወቅቱ ነዳጅ መረጃ ነው፡፡ ስለዚህም ‘ETRSS-1’ ኢትዮጵያ ካላት መረጃ ጋር በማጣመር የግብርና ዘርፏን ለማሳደግ፣ ለግብርና ፖሊሲ ቀረፃና ለድርቅ ቅድመ ትንበያ የሚረዱ መረጃዎችን ለማመንጨት ታግዛለች የሚል ትልቅ ተስፋ አለኝ፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይኼም ለአካባቢ ጥበቃና ለአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሾችን ለመስጠት አጋዥ ነውም ብለዋል፡፡ ‹‹ይኼ ለኢትዮጵያ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ጥሩ ቀን ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የህዋ ሳይንሱ እንደ አንድ ቴክኖሎጂ ብቻ የሚታይ ጉዳይ አይደለም በማለት ጠቀሜታውን አጉልተው የሚያስረዱት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዱቃን ደበበ ናቸው፡፡ ሳተላይት ለኢትዮጵያ አሁን ጊዜው እንዳልሆነ በመጥቀስ ዳቦ ይቅደም የሚሉ እንዳሉ በማንሳት የሚከራከሩ እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ሳንዱቃን፣ ‹‹አሁን ከሰባት ሺሕ በላይ ሳተላይቶች በህዋ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሳተላይት ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2019 ከተመሳሳይ ሥፍራ ከተወነጨፉ ሳተላይቶች 99ኛው ነው፡፡ ቁጥሮች የሚያሳዩት እንዲያውም መዘግየታችንን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሳተላይቱ በመጨረሻ ለዳቦና ለጤና ነው ጥቅም ላይ የሚውለው፤›› ብለው፣ ‹‹ከዚህ በተጨማሪም ቴክኖሎጂው ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ መቅደም ወይም እኩል መሄድ ነው ያለብን እንጂ ለምን እንዘግይ?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹በቆየን ቁጥር የሳተላይት መቀመጫ ምህዋር በሳተላይቶች ብዛት ስለማይኖር ዕድሎችን ሊያጠብብን ይችላል፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በግብርና ላይ የተሰማራ ሕዝብ ቁጥር ከ80 በመቶ በላይ በሆነበት አገር የአየር ንብረት ሁኔታን፣ የጎርፍ፣ የእሳተ ጎሞራ፣ እንዲሁም የአውሎ ንፋስ ሁኔታዎችን መከታተልና ማወቅ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ቀድሞ የአየር ሁኔታውንና የሙቀት መጠኑን መረዳት እጅግ ጠቃሚ ነው መሆኑን አቶ ሳንዱቃን ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የከተማ ልማት፣ የመሬት አስተዳደር፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የደኅንነትና የመሳሰሉ ዘርፎችን በእጅጉ የሚደግፍ ጠቀሜታ ያለው የመሬት ቅኝት ሳተላይት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...