Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፕሪሚየር ሊግ ክለቦችና የገጠማቸው የፋይናንስ ቀውስ

የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችና የገጠማቸው የፋይናንስ ቀውስ

ቀን:

“ፕሪሚየር ሊግ” የሚለውን የተውሶ ስያሜ ይዞ ከሁለት አሠርታት በላይ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በፋይናንስ ቀውስ መታመስ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአንዳንድ ክለብ ተጨዋቾች ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ በውላቸው መሠረት ሊያገኙ የሚገባቸው ወርኃዊ ክፍያ እንዳልተከፈላቸው ይናገራሉ፡፡

ሊጉን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ በዚህ ደረጃ ለተጨዋቾቻቸው ወርኃዊ ክፍያ መክፈል ያልቻሉ ክለቦች፣ የገቡትን የውል ስምምነት ሊያከብሩ እንደሚገባ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን ቢልክም ተፈጻሚነቱ እምብዛም እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በዚህም አንዳንድ ተጨዋቾች በገቡት ውል መሠረት ለክለባቸው መስጠት የሚገባቸውን አገልግሎት ለማቋረጥ በመገደድ ላይ እንደሚገኙ እየተነገረ ይገኛል፡፡

የተጨዋቾችን ወርኃዊ ክፍያ ባለመክፈል ከተጨዋቾች ጋር ወደ ከፋ ችግር ውስጥ ከገቡት ክለቦች በዋናነት ስሁል ሽረና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ከተማና በከፊል ጅማ አባ ቡና እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ የስሁል ሽረ ተጨዋቾች በዚህ ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ ለሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ከቡድኑ ራሳቸውን ያገለሉ እንዳሉ ጭምር ተነግሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የስሁል ሽረ ክለብ አመራሮች፣ ተጨዋቾቹ የሚያቀርቡት ቅሬታ ተገቢ ስለመሆኑ፣ ይሁንና በአንዳንድ ምክንያቶች በጀቱ ሊደርስ አለመቻሉን የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ የውድድር ዓመቱ መደበኛ መርሐ ግብር መጀመሩን አስመልክቶ ችግሩ በቶሎ መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ ቡድኑ በፕሪሚየር ሊጉ የሚኖረው ቀጣይነት ከወዲሁ ሥጋት ውስጥ ሊገባ የሚችልበት ሁኔታ እንዴት ይታያል የሚለው የሪፖርተር ቀጣይ ጥያቄ ነበር፡፡

‹‹ሥጋቱ እኛም የምንጋራው ነው፣ ይሁንና ይህን የተናገርነው ማንነት እንኳ ቢታወቅ በራሱ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ክለብ አመራር ተጨዋቾቹ የሚያቀርቡት ቅሬታ ተገቢነቱን በማመን ለሚመለከታቸው አካላት ቀደም ሲል ጀምሮ ብናቀርብም እስካሁን አልተፈጸመም፤›› የሚሉት የክለቡ አመራሮች፣ የአንዳንድ ተጨዋቾች የሰሞኑ ውሳኔ ከሕግ አኳያ ትክክል ነው ተብሎ የሚወሰድ መሆኑ እንደተጠበቀ ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ በሚኖረው ቀጣይ ተሳትፎ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እንዳለ ግን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከተጨዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ጋር ያለው አለመግባባት በእነዚህኞቹ ክለቦች ጎልቶ መውጣቱ ይነገር እንጂ፣ ችግሩ የአዲስ አበባዎቹን ሕዝባዊ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስንና ኢትዮጵያ ቡናን ጭምር የሚያሳስብ መሆኑ ከሰሞኑ ከሜዳ ገቢ ጋር ተያይዞ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑና በሁለቱ ክለቦች መካከል የሚደመጣውን እሰጣ ገባ መመልከቱ በቂ ነው፡፡

ንብረትነቱ የማን እንደሆነ በሕግ ባይረጋገጥም፣ በተለምዶ የስፖርት ኮሚሽን መሆኑ በሚነገርለት የአዲስ አበባ ስታዲየም የሚጠቀሙት ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ከፌዴሬሽኑ ጋር ሊያስማማቸው ያልቻለው ጉዳይ፣ ቀደም ሲል ጀምሮ ሲሠራበት የቆየው የሜዳ ገቢ 68 በመቶ ለክለቦች፣ 32 በመቶ ደግሞ ለፌዴሬሽኑ የሚለው ነው፡፡

የነበረው መቀጠል እንደሌለበት የሚናገሩት ሁለቱ ክለቦች፣ የትኬት ሽያጩን በዳሸን አሞሌ እንዲሆን አድርገው ገቢውም ሙሉ በሙሉ የራሳቸው መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ትኬት አሻሻጡን በሚመለከት ክለቦቹ የተከተሉት አሠራር ትክክል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን በተቋሙ ሥር የሚተዳደሩ ሠራተኞች ወርኃዊ ክፍያን ጨምሮ መብራትና ውኃ ወጪ የሚከፍለው ከዚሁ ገቢ እንደሆነ በመግለጽ ይከራከራል፡፡ ይህ ጉዳይ እስካሁን እልባት አለማግኘቱ ይታወቃል፡፡

ከወርኃዊ ክፍያ ጋር በተገናኘ በክለቦችና በተጨዋቾች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ አቋምና መተዳደሪያ ደንቡም የሚለው፣ ክለቦች ለገቡት ውል ተገዥ ሊሆኑ እንደሚገባ፣ ይህ ተግባራዊ የማይሆን ከሆነ ግን ክለቡ የተጨዋቹ ዕዳ እንደተጠበቀ ሆኖ ዕገዳ ሊጣልበት እንደሚችል ጭምር ይደነግጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...