Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኢትዮጵያ በሴካፋ ያገኘችውን ኃላፊነት አስጠብቃ ትቀጥላለች?

ኢትዮጵያ በሴካፋ ያገኘችውን ኃላፊነት አስጠብቃ ትቀጥላለች?

ቀን:

ለምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) መመሥረት ትልቅ ድርሻ እንደነበራት የሚነገርላት ኢትዮጵያ፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በሴካፋ በተለይ በእግር ኳሱ የነበራት የመሪነትም ሆነ የተፎካካሪነት አቅም እየቀነሰ መምጣቱ ይታመናል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ በአስተናጋጇ ኡጋንዳ የበላይነት ፍጻሜውን ባገኘው የሴካፋ ዋንጫ በብሔራዊ ቡድኗ ያልተወከለችው ኢትዮጵያ፣ ለቀጣዩ አራት ዓመታት ሴካፋን በምክትል ፕሬዚዳንትነት መምራት ትችል ዘንድ ተመርጣለች፡፡ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ታንዛኒያ አግኝታለች፡፡             

ከአፍሪካ እግር ኳስ ዞን አምስት በመባል የሚታወቀው ሴካፋ ከተቋቋመ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ በካፍ ደረጃ ያለው ተፅዕኖ ፈጣሪነት በሁሉም ረገድ ይህ ነው የሚባል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ይህም ለዞኑ አገሮች የእግር ኳስ ተቋማዊ አደረጃጀት ድክመት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ጭምር ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡

ሴካፋ ታኅሣሥ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ሴካፋን በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንደተናገሩት፣ ሴካፋ እንደ ሰሜኑና ደቡቡ እንዲሁም ምዕራቡና ማዕከላዊ አፍሪካ አገሮች ጠንካራ የእግር ኳስ አደረጃጀት ይኖረው ዘንድ አሁን ከሚገኝበት ቁመናው ሙሉ በሙሉ መለወጥ መቻል ይኖርበታል፡፡ ‹‹በግሌ ወደ እዚህ ኃላፊነት ከመጣሁበት ቀን ጀምሮ የምሥራቅ አፍሪካ እግር መሪዎችን ከሚባሉት ከአንዳቸውም ጋር ተገናኝቼ ስለምሥራቅ አፍሪካ እግር ኳስ የተነጋገርኩበት ወቅት ትዝ አይለኝም፡፡

‹‹እንዲያውም የሴካፋን ዓመታዊ መርሐ ግብር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ራሱ በሚገባ ስለማወቁ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ በተቋሙ ምን ያህል የሥርዓት ክፍተት እንዳለ ያመላክታል፣ ይህ ክፍተት ለምንና እንዴት የሚለው ጉዳይ በኡጋንዳው ጉባዔ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት መፍትሔም እንዲበጅለት ይጠበቃል፤›› በማለት ለምርጫው ወደ ኡጋንዳ ከማምራታቸው አንድ ቀን ቀደም ብለው ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ መጠይቅ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የሴካፋ ወንበራቸውን ለታንዛኒያዊ ካሪያ ዋላስ በይፋ ያስረከቡት ሱዳናዊ ሙስታዚም ጋፋር (ዶ/ር) ለምሥራቅ አፍሪካ እግር ኳስ መውደቅ ምክንያት ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡ ደቡብ ሱዳናዊ ፍራንሲስ አሚን ተቀዳሚና አቶ ኢሳያስ ጅራ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሴካፋን ለቀጣዩ አራት ዓመት እንዲያስተዳድሩ መመረጣቸው ለደካማው የምሥራቅ አፍሪካ እግር ኳስ ተስፋ የሰነቁ አልጠፉም፡፡

ኢትዮጵያ በሴካፋ የሚኖራትን የአመራርነት ሚና አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስ ካበረከተችው አስተዋጽኦ አኳያ ያገኘችው የምሥራቅ አፍሪካ ሥልጣን ቢያንስባት እንጂ የሚበዛባት አልነበረም፡፡ በአጋጣሚም ይሁን ታስቦበት እግር ኳሱን ለማስተዳደር ዕድሉን ያገኙ ምሥራቅ አፍሪካን ጨምሮ በሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት የነበራትን ቦታ ከማስጠበቅ ይልቅ እርስ በርስ በመጠላለፍ በከንቱ ማለፍ የሌለባቸው በርካታ ወቅቶች እንዲያልፉ ሆኗል፡፡

መጠላለፉ ከዚህም አልፎ ለአገሪቱ እግር ኳስ ውድቀትም ምክንያት መሆኑ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም በምሥራቅ አፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ታሪክ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ አሁን ላይ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መመልከቱ በቂ ነው ይላሉ፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚኖራት የመሪነት ሚና ጎን ለጎን፣ ከተለያዩ አኅጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ መድረኮች ቀስ በቀስ እየቀነሰ የመጣውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሞራል ስንቅ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንደሚኖረው ተስፋ አላቸው፡፡

ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ሴካፋን በምክትል ፕሬዚዳንትነት መምራታቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...