Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አገር በቀል ሪፎርም አገር በቀል ዕውቀት ይፈልጋል›› አቶ እንዳልካቸው ስሜ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

አቶ እንዳልካቸው ስሜ የኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው፡፡ በይበልጥ የሚታወቁት የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በዋና ጸሐፊነት በማገልገላቸው ነው፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር ዋና ጸሐፊ ነበሩ፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት በግሉ ዘርፍ ውስጥ በርካታ ሥራዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ ከሰሞኑ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና እንደ የዓለም ባንክ ያሉ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ድጋፎች ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ሁሉ አደጋም እንደሚኖራቸው የሚገልጹ አሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የውጭ ምንዛሪ ተመን ገበያ መር ይሆናል የሚለው ሐሳብም በብዙዎች ዘንድ ይነሳል፡፡ እነዚህንና ሌሎች ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ አቶ እንዳልካቸው ስሜን አነጋግሯል፡፡ ላቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽም እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ያሰበው 2.9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ፣ እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችና ብድሮች ለኢኮኖሚው የሚኖራቸው አንድምታ ምንድነው? አስከትለው የሚያመጡት ጣጣ ሊኖር ይችላል የሚል አስተያየት ስለሚሰማ፣ ለዚህስ ምን ምላሽ አለዎት?

አቶ እንዳልካቸው፡- ስለብድሮቹ ከማንሳታችን በፊት ስለኢኮኖሚያችን የአሁን ሁኔታና ብድሮቹ ስለተጠየቁበትና ስለመጡበት ምክንያት ጥቂት ማየቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ኢኮኖሚያችን ላለፉት 15 ዓመታት በሁለት አኃዝ ሲያድግ ጥንካሬዎችንም ድክመቶችንም አስመዝግቧል፡፡ ጥንካሬዎቹ ካፒታል ወይም ሀብት በማፍራት ላይ አተኩሮ የቆየው የመንግሥት ኢንቨስትመንት ካመጣው ዕድገት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ድክመቶቹ ደግሞ ዕድገቱን ይዞ ሊቀጥል የሚገባውን የግሉን ዘርፍ በበቂ ካለማዘጋጀትና ከብክነቶች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ጉድለቶቹ ከኢኮኖሚያዊ አንድምታቸው ያለፈ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ወደ መፍጠር ተሸጋግረው ታይተዋል፡፡ በተለይ ኢኮኖሚው የዕድገቱን ያህል የሥራ ዕድል ማመንጨት አለመቻሉ፣ የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት አለመቻሉና የመመለስ ዕድሉ የመነመነ አገራዊ ዕዳ መቆለሉ፣ ኢኮኖሚው የደም መፍሰስ ሕመም ውስጥ እንደገባ የሚያሳዩ ጠቋሚ ምልክቶች አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ደምን ከማቆም ጊዜያዊ ሕክምና በላይ መሠረታዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ የሞት የሽረት ጉዳይ ሆኖ ከፊታችን ተደቅኗል፡፡

በመቀጠል ማየት የሚያስፈልገው ለዚህ ችግር የሚመጥን መፍትሔ ምን ዓይነት መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ እንደ መፍትሔ የምናስቀምጣቸውን ሥራዎች ደግሞ ለመፈጸም ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምንጮቹን ለይቶ ለችግራችን ማዋል በምንችልበት ነፃነት ገንዘብ ማግኘት ቀጣዩ ሥራ ነው፡፡ ብድሩ የመጣበትን አካሄድ ስናይ ችግሮቻችንን በራሳችን ሁኔታ ተንትነን ለመረዳት ሞከርን፣ ለችግሮቻችን መውሰድ ያለብንን መፍትሔ ለየን፣ መፍትሔውን ለመተግበር የሚያስፈልገንን ፋይናንስ ጠየቅን ያንን አገኘን፡፡ በዝርዝር ዝግጅቱ ውስጥ ባልሳተፍም ያሉኝ መረጃዎች አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ብሎ መንግሥት የሄደበት አካሄድ  ይኼንን የሚያሳይ ነው፡፡ ብድሩ ሌላ ጣጣ አያመጣም ወይ ለሚለው እንደ አያያዛችን ይወሰናል ባይ ነኝ፡፡ ብድርና ዕርዳታ የሚመጡበት የየራሳቸው አጀንዳ እንዳለ ሆኖ ተቀባዩ ጠቃሚም፣ ጎጂም የማድረግ አቅም አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላ በኩል ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ ይቅርብን አንፈልግም ማለትስ እንችላለን ወይ? ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ኢኮኖሚውን የማስተካከል ጉዳይ የማደግና ያለ ማደግ ጉዳይ ከመሆን አልፎ፣ እንደ አገር የመቀጠልና ያለ መቀጠል ጉዳይ ወደ መሆን ተሸጋግሯል የሚል ሐሳብ ስላለኝ ነው ይህን የምልህ፡፡  

ሪፖርተር፡- አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በተለይም ለሥራ ፈጠራ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍና የመዋቅር ማስተካከያ ለማምጣት እንደሚሠራ ይነገራል፡፡ ከዚህ አንፃር የውጭ አበዳሪዎችና ለጋሾች ምክረ ሐሳቦች ብቻ ሳይሆን፣ ከአገር ውስጥም የሚቀርቡ አስተያየቶችና ማሳሰቢያዎች መደመጥ ስላለባቸው እርስዎ ምን ዓይነት ምክረ ሐሳብ ያቀርባሉ?

አቶ እንዳልካቸው፡- አገር በቀል የዕድገት ንድፈ ሐሳብና የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ሐሳብ የተቀዳበት የኢኮኖሚ ቲዎሪ ከኒዮ ክላሲካል የዕድገት ቲዎሪዎች ሁሉ የተሻለ፣ በተለይ ለታዳጊ አገሮች የሚመከር የዘመናችን አስተሳሰብ ነው፡፡ ዋና ብልቱም የጎለበተ አገር በቀል የሰው ኃይል ነው፡፡ መንግሥት ይፋ ያደረገው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምም ውጤታማ ሆኖ ተግባራዊ እንዲሆን፣ አገር በቀል አቅምንና ዕውቀትን አሟጦ መጠቀም ትኩረት የሚፈልግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የውጭ ደጋፊዎችና የአበዳሪዎች የዕውቀትም የገንዘብም ድጋፍ ወሳኝና ጠቃሚ መሆኑንም ከግንዛቤ መውሰድ ግን ይገባል፡፡ አገር በቀል ሪፎርም ስንል የእኛን መሪነት፣ ባለቤትነትና ዋና ተዋናይነት የሚያሳይ እንጂ ሌላው ሳያግዘን እኛው ጀምረን እኛው የምንጨርሰው ሪፎርም አይደለም ብዬ ነው የማምነው፡፡ ገንዘቡና ዕውቀቱ ሁሉ አለን እንኳን ብንል እንደዚህ ዓይነት ሥራ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ከባቢ ውስጥ በሌሎች ልምድና ትብብር የሚሠራ ነው፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ደግሞ የገንዘብም፣ የዕውቀትም፣ የልምድም ድጋፍ የምንፈልግበት በመሆኑ በምንፈልገው አቅጣጫ የመምራት ሚናና ኃላፊነትን ወስደን የአጋሮችን ድጋፍ መጠቀም አማራጭ ያለው አይመስለኝም፡፡

አገር በቀል ስንል የኢኮኖሚ ዕድገት ሳይንሱን እዚሁ አገር ውስጥ እንፈልስፈው አይመስለኝም፡፡ ኢኮኖሚውንም አገር በቀል እናድርገው አይመስለኝም፡፡ አገር በቀል በዋናነት የሚያነጣጥረው ሪፎርሙ ላይ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ሳይንሳዊ ዕውቀትና የሌሎች ልምድን በመቀመር ላይ ድጋፍ ወስደን የእኛን ችግር በራሳችን መንገድ በባለቤትነት ተንትነን፣ መፍትሔዎቻችን ሁሉ ሁኔታዎቻችንን ያማከለ አድርገን፣ ለትግበራው ደግሞ የፋይናንስ ድጋፍ ፈልገን፣ በትግበራው ውስጥ ደግሞ ግንባር ቀደም የባለቤትነት ሚና ይዘን የምንፈጽመው ሪፎርም ይመስለኛል፡፡ ሒደቱ ውስጥ አገር በቀል ዕውቀቶች ትልቅ ሥፍራ እንዳላቸው ማየት እንችላለን፡፡ መሠረተ ሰፊ የዜጎች ተሳትፎን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ ይህም ትልቅ ትኩረት የሚፈልግ ሥራ እንደሆነ መውሰድ እንችላለን፡፡   

ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማስወገድ በርካታ ሐሳቦች ይሰማሉ፡፡ በፖሊሲ ደረጃ ለውጭ ምንዛሪ እጥረት መሠረታዊ የሚባሉ ምክንያቶችና መፍትሔዎች ምንድን ናቸው? የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማስወገድና የተስተካከለ ሥርዓት ለመፍጠር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ እንዳልካቸው፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረታችን በዋናነት የሚመነጨው በውጭ ገበያዎችም ሆነ፣ በአገር ውስጥ ገበያዎች ላይ ያለን የአቅራቢነት ሚና በመሳሳቱ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ የሚገኘው ከገበያ ነው፡፡ ከውጭ ገበያ የውጭ ምንዛሪ ታመርታለህ፡፡ ከአገር ውስጥ ገበያ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ትቆጥባለህ፡፡ ሁለቱ ምንጮች የውጭ ምንዛሪ ክምችትህን ይሠሩልሃል፡፡ ለሁለቱም የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ግን እጅህ ላይ ሊኖር የሚገባና ገበያው የሚፈልገው ምርት ያስፈልግሃል፡፡ ያን ምርት ነው መያዝ ያቃተን፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት የሚይዘውን ድርሻ በአራትና በአምስት ዕጥፍ ማሳደግ ካልቻልን፣ ገቢ ምርቶችን ለመተካት የሚጠይቀንን የአገር ውስጥ ገበያም ሆነ አምርተን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የምንችለው ምርት እጃችን ላይ እንዲኖር ማድረግ አይቻልም፡፡ ይህ ማኑፋክቸሪንግን ቀዳሚ የማድረግ መዋቅራዊ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ አሁን ላጋጠመን አጣብቂኝ ጊዜያዊና ጥገናዊ ሥራዎችን መሥራት መሰንበቻ ትንፋሽ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሪፎርምን ብናነሳ ለቀጣይም መሠራት ያለበትና አሁንም ላለብን አጣብቂኝ ፋታ ሊመጣ የሚችል በመሆኑ፣ በፍጥነት አጠናክሮ መሥራቱ ድርብ ጥቅም አለው፡፡  

ሪፖርተር፡- የብር የምንዛሪ ተመን ሥርዓትን ከነበረበት (Fixed Exchange Rate System) አሠራር ወደ ገበያ መር (Managed Float Exchange Rate System) ለመውሰድ ፍላጎት አለ እየተባለ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ጥቅሙና ጉዳቱ እንዴት ይገለጻል? ዝግጅቱስ ምን መምሰል ይኖርበታል? የብር የምንዛሪ ተመን በትክክለኛው የገበያ ዋጋ ይሠላ ቢባል በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሊሆን ይችላል? የአገሪቱ ኢኮኖሚም ሆነ ሸማቹ ይችለዋል ወይ?

አቶ እንዳልካቸው፡- የውጭ ምንዛሪ ተመን በፋይናንስ ገበያ ፍላጎትና አቅርቦት የሚወሰን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እ.ኤ.አ እስከ 1980ዎቹ የዓለማችን አብዛኞቹ አገሮች የውጭ ምንዛሪ ተመናቸውን በመቆጣጠር በራሳቸው ይተምኑ ነበር፡፡ ነፃ ገበያ እየተስፋፋ ከመጣባቸው ከ1990ዎቹ ጀምሮ ግን አብዛኞቹ ያደጉት አገሮች የውጭ ምንዛሪ ተመን ቁጥጥራቸውን ቀስ በቀስ በማንሳት ገበያው እንዲወስነው ሲደርጉ ተስተውሏል፡፡  ተመኑን ሙሉ በሙሉ ለገበያው መልቀቅም የራሱ የሆነ ጉዳት እንዳለው ከግንዛቤ መውሰድ ይገባል፡፡ በተለይ በፋይናንስ ገበያው ፍላጎትና አቅርቦት ድንገተኛ ለውጥ ሲከሰት፣ በአገሮች ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ድንገተኛ ንዝረት መጠነ ሰፊ ጉዳቶች እንዳሉት የአገሮች ልምድ ያሳያል፡፡ የአገራችን መደበኛ የምንዛሪ ተመንን ስናይ (ለምሳሌ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ያለው የ30 ብር አካባቢ ተመንን ልንወስድ እንችላለን) የብር ዋጋ ከፍ ብሎ የተተመነበት እንደሆነ በሁለት ማሳያዎች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ አንደኛው በኤክስፖርታችንና በኢምፖርታችን መካከል ያለው ልዩነት በፍጥነት እየተለያየ መምጣቱን ስናይ፣ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችን ከአቅርቦታችን በአራትና በአምስት እጥፍ ተበልጦ እናገኘዋለን፡፡ ሁለተኛው ማሳያችን የጥቁር ገበያ ተመኑ ከመደበኛው ተመን በጣም ከፍተኛ (ከ30 በመቶ በላይ የሚደርስ) ልዩነት እያሳየ መምጣቱ ነው፡፡

እነዚህ ሁለት ማሳያዎች የብር ዋጋን የመቀነስ አስፈላጊነት ያሳያሉ፡፡ ሲቀነስ ግን ጥናትና ጥንቃቄ ይፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ አንደኛ አገራዊ ጠቀሜታን መሠረት ማድረጉን፣ ሁለተኛ ደግሞ የመቀነስ ዕርምጃው የጎንዮሽ ጉዳት እንዳያስከትል (ለምሳሌ የብር ዋጋ እንደሚቀንስ በመጠበቅ የሚከሰቱ ግምትና ተያያዥ ችግሮች) በመጠንቀቅ መደረግ ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም የገበያውን አቅጣጫ የተከተለ፣ ነገር ግን የአሁን ሁኔታችንን ያማከለ፣ ቀስ ብሎ ወደ ትክክለኛው ተመን የሚያመራ የምንዛሪ ማስተካከያ አሠራር ተገቢ ነው ባይ ነኝ፡፡ ይህ ሲባል ግን ያለችውን ኤክስፖርት እንዳያዳክምና በአገር ውስጥ ገበያም እየተከሰተ ያለውን የዋጋ ንረት የባሰ እንዳያቀጣጥል ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ጥንቃቄ ያስፈልጋል ይላሉ?

አቶ እንዳልካቸው፡- ጥንቃቄው የምርት አቅርቦት መጠንን በመጨመር ሊሆን ይችላል፡፡ አቅርቦት ሲጨምር የዋጋ ንረትን ይቆጣጠርልሃል፣ የውጭ ምንዛሪም ያመጣልሃል፡፡ በመሆኑም የተመን ማስተካከያው መጨመር ከአቅርቦት መጠን ጋር መናበብ ይኖርበታል፡፡ ሌላው መታሰብ ያለበት በኢምፖርታችን ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን የተወሰኑ አገሮች ለይተን፣ የእነሱን ገንዘብ የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ክምችት አካል ማድረግ እንደ መፍትሔ ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ቻይናን ብንወስድ የኢምፖርታችንን የአንበሳ ድርሻ ትወስዳለች፡፡ ዋነኛ የገቢ ንግድ ሸሪክ ነች፡፡ ነገር ግን ከቻይና ጋር እየተገበያየን ያለነው በሦስተኛ አካል መገበያያ ገንዘብ ማለትም በዶላር ወይም በዩሮ ነው፡፡ የእኛ ኢምፖርተሮች ዶላር ገዝተው ለቻይና ኤክስፖርተር ይከፍላሉ፡፡ ቻይናዊውም ዶላሩን ወስዶ ወደ ራሱ ገንዘብ ይቀይረዋል፡፡ ብር ከቻይና ገንዘብ ጋር በቀጥታ የሚገበያይበት አሠራር ማመቻቸት ማለት ነው፡፡

ይህ እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉ አገሮች የተሞከረና ውጤት ያመጣ አሠራር በመሆኑ ለአገራችንም ሊጠቅም ስለሚችል፣ አገሮቹን በጥንቃቄ መርጦ የተወሰኑትን አጥንቶ መሞከሩ አሁን የገጠመንን የምንዛሪ አጣብቂኝ ሊያቀልልን ይችላል፡፡ የብር ተመን የግድ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ገበያው ተመን ጋር የግድ አንድ መሆን አለበት ማለትም አይደለም፡፡ ተጠቃሚነታችንን እያየን ተመኑን ከፍም ዝቅም ማድረግ እንደሚገባ እንደ ቻይና ያሉ አገሮች ልምድ ያሳየናል፡፡ ነገር ግን ያንን ስናደርግ ከውጤቱ ተጠቃሚ እንሆናለን ወይ የሚለው በሙያዊ መንገድ ሊጤን ይገባል፡፡ ባለፈው ኤክስፖርትን ለማበረታታት ተብሎ የብር ዋጋ እንዲቀንስ ሲደረግ የማምረት አቅማችን ባልጎለበተበት በመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳመዘነ ማየት ችለናል፡፡   

ሪፖርተር፡- የዋጋ ግሽበቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ ፓርላማ ደርሶ ለውይይት ከመቅረቡ በተለያዩ ምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለዎትን ምልከታ ቢነግሩን?

አቶ እንዳልካቸው፡- እየጨመረ ያለውን የዋጋ ንረትና በዝግጅት ላይ ያለውን ኤክሳይዝ ታክስ አንስተሃል፡፡ ጥሬ መርሆዎቹን ለመገንዘብ ለያይቶ ማየት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ወደ ተግባር ስንወስዳቸው በጋራ ያላቸውን ቁርኝት ማየት ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ የዋጋ ንረቱ መሠረታዊ ምክንያት አቅርቦት እንደሆነ ቀደም ብዬ ጠቅሻለሁ፡፡ ይህ መፍትሔውን ያሳየናል፡፡ የኤክሳይዝ ታክሱን ስናይ ደግሞ መንግሥት ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን አስቦ ገቢውን ለማሳደግ አማራጩን እየፈተሸ ይመስለኛል፡፡ የታክስ ጂዲፒ ጥመርታችን ዝቅተኛ እንደሆነና የታክስ መሠረታችንን አስፍተን የበለጠ ታክስ መሰብሰብ እንደምንችል የተለያዩ ጥናቶች ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን መቼና እንዴት የሚለው ላይ መሬት ወርዶ ሥራ መሥራት ይጠይቃል ባይ ነኝ፡፡ ኤክሳይዝ ታክስ ፍላጎታቸው የማይቀንስ የቅንጦት ዕቃዎች ላይ በመጨመር ገበያውን ብዙ ሳይጫኑ የመንግሥትን ገቢ ማሳደግ የሚል ዕሳቤ የያዘ ነው፡፡ ሐሳቡ ጥሩ ሆኖ በተግባር ሲታይ ውጤቱ ምን ይሆናል የሚለው አሁን ካለንበት ሁኔታ ጋር በዝርዝር ማየት ተገቢ ነው ባይ ነኝ፡፡ ዋጋ ቢጨምር ፍላጎታቸው የማይቀንሱ የቅንጦት ዕቃዎች ፍላጎታቸው አይቀንስ እንጂ፣ በኤክሳይዝ ታክሱ ወደ ኢኮኖሚው የሚያስገቡት የገንዘብ መጠን መጨመሩ አይቀርም፡፡ ይህንን አሁን ካለንበት ብዙ ብሮች ጥቂት ምርት ከሚያሳድዱበት የዋጋ ንረት ጋር በአንድነት ማየት ተገቢ ይሆናል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ የነበረውን የገዘፈ ድርሻ ለመቀነስ የፕራይቬታይዜሽን እንቅስቃሴ እየተጀመረ ነው፡፡ የመንግሥት ፕሮጀክቶችም እየተቀዛቀዙ ነው፡፡ በሌላ በኩል የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ አሁንም ደካማ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ፕራይቬታይዜሽኑም ሆነ የመንግሥት ሚና መቀነስ እንዴት ሆኖ መመራት አለበት? ውዥንብር የሚታይ አይመስልም?

አቶ እንዳልካቸው፡- መንግሥት የኢኮኖሚ መሪነት ሚናውን ለግሉ ዘርፍ በሒደት የማስረከብ አቅጣጫ መያዙ፣ አማራጭ የሌለውና የዘገየ ሥራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ያሉት የፕራይቬታይዜሽንም ሆነ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች አቅም ላለው የግል ዘርፍ፣ በተለይ ለውጭው የግል ዘርፍ አጓጊ እንደሆኑ በተለያየ ሁኔታ እንሰማለን፡፡ የውጭውን የግል ዘርፍ ለማሳተፍ ከባድ አይመስለኝም፡፡ አገር በቀሉን የግል ዘርፍ ግን ማሳተፉ በጣም ስትራቴጂካዊ ስለሆነ በቁርጠኝነት መረባረብን ይጠይቃል፡፡ ሰፊ የማብቃት ሥራም አለበት፡፡ በሌላ በኩልም መንግሥት በስፋት የከረመባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች የኢኮኖሚው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ውስጥ ትንሽ የማይባል ድርሻ ይዘው ስለቆዩ፣ መንግሥት የመውጣት ወይም የመልቀቅ ስትራቴጂ ሳይሆን የማስረከብ ስትራቴጂ ነው መከተል ያለበት ባይ ነኝ፡፡ መውጣት በማስረከብ ካልታገዘ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝንና ሥራ አጥነትን ሊወልድ ይችላል፡፡ የመንግሥት መውጣት ግን ለግሉ ዘርፍ በማስረከብ ከሆነ ግን መቀዛቀዝን ሳይፈጥር ወደ ዘላቂ ልማት መሸጋገር ያስችላል፡፡ በተለይ አገር በቀሉን የግል ዘርፍ ስናስብ የማብቃት ሥራም ስላለው የመንግሥት ከዘርፎቹ የመውጣት አካሄድ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ሳይቋረጡ፣ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሳይፈጠር መሆኑ ጠቀሜታው ድርብ ነው፡፡ መንግሥት ሳይወጣም ሊቀጥል የሚጠበቅባቸው ዘርፎች እንዳሉም ማሰብ ይገባል፡፡ በጥንቃቄና በጥናት ይሁን እንጂ መንግሥት እንደ አዲስ ሊገባባቸው የሚገቡ የኢኮኖሚ ዘርፎችም ሊኖሩ እንደሚችሉም ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ አወጣጡን ስናይ ደግሞ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝን ሊቀንስ በሚችል ሁናቴ፣ አወጣጡን በሒደት ማድረግ አለበት ሲባል ደግሞ አንዴ ገብተሃልና የግል ዘርፍ ካልተረከበህ እዚያው መቆየት አለብህ ወደ ሚል ዋልታ ሊወስደን አይገባም፡፡ በጥናት ማየት ይገባል፡፡ ዘርፉ ቀድሞም መንግሥት መግባት ያልነበረበት ከሆነና የግል ዘርፉም የመግባት ፍላጎት የሌለው ከሆነ ሙሉ ለሙሉ ቆሞ፣ የኢኮኖሚ መቀዛቀዙን መቀበል ያለብን ከሆነም በጥናት ማረጋገጥ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳው የአገሪቱን ችግሮች ለማቃለል መነሳቱን አስታውቋል፡፡ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አቅም አለው ብለው ያምናሉ? የሪፎርም አጀንዳውን ለማሳካት ምን የጎደሉት ነገሮች አሉ ይላሉ? የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከገባበት መዛባት ውስጥ ለማውጣትና መልክ ለማስያዝ ምን ቢደረግ ውጤት ሊገኝ ይችላል ይላሉ? በመንግሥትም ሆነ በባለሙያዎች ትኩረት የተነፈጋቸው ጉዳዮች ምንድናቸው ብለው ያስባሉ?

አቶ እንዳልካቸው፡- መንግሥት አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ለመተግበር አቅም አለው ወይ ካልን፣ ብቻውን ሊፈጽመው የሚችለው አይደለም ነው መልሴ፡፡ ካሁን በፊት ከነበሩ የሪፎርም አካሄዶች በተለየ ሰፊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ሥራ እንደሆነ ነው የሚገባኝ፡፡ ተሳታፊ ለማብዛት ደግሞ መግባባት ላይ ማተኮሩ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በአገራችን በጣም ሊለወጥ የሚገባው ነገር የውይይት ባህላችን ነው፡፡ ምክንያታዊነት የዳበረበት የውይይት ባህል ከመቼውም በላይ ያስፈልገናል፡፡ መደገፍም መቃወምም አስፈላጊ ናቸው፡፡ ነገር ግን ዝርዝር ምክንያቶቹ አብረው ካልቀረቡ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ባይ ነኝ፡፡ ምክንያት ያልደገፈው ተቃውሞ ጥላቻን ብቻ ነው የሚሳየው፡፡ ምክንያት የሌለውም ድጋፍ ከዚያው ያልተናነሰ ጉዳት ያለው ርካሽ ተወዳጅነትን መሠረት የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡ ከሁሉ በፊት በሪፎርሙ አስፈላጊነትና በሪፎርሙ ሦስት አቅጣጫዎች መግባባት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ መጨመርም መቀነስም ያለበት ጉዳይ ሲታየን በኃላፊነት መሳተፍ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ይመስለኛል፡፡ በአስፈላጊነቱ ላይ ብዙ ብዥታ አላይም፡፡ ምክንያቱም ትኩሳቶቹ እያንዳንዳችን ኑሮ ውስጥ በግልጽ መታየት ጀምረዋል፡፡ ሪፎርሙን አገራዊ ቅኝትና አተያይ ለመስጠት በተሞከረበት አካሄድ ላይ ብዙ ብዥታ አልጠብቅም፡፡

ምናልባት በሦስት ተከፋፍለው የተቀመጡት የሪፎርሙ አቅጣጫዎች (ማክሮ፣ ስትራክቸራልና ሴክተራል) የየዘርፉን መሠረታዊ ጉዳዮች ይዳስሳሉ ወይ የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ በመሆኑ የየዘርፉ ዋና ዋና ተዋናዮች አንድም አፈጻጸሙን በባለቤትነት እንዲይዙት፣ በሌላም በኩል ቁልፍ ጉዳዮች እንዳይዘነጉ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ውይይት ማድረጉ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የሪፎርሙ ዝርዝር በዝግጅት ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ በየዘርፉ የማወያየቱ ሥራ አሁን መሆን እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በተሳትፎ ላይ ደግሞ በአገር የተያዙ ልምዶችን፣ ዕውቀቶችን፣ የየዘርፉ ባለሙያዎችን በስፋትና በባለቤትነት ማሳተፉ የሪፎርሙ ዋና ጉዳይ መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ አንዳንድ የየዘርፉ ባለ ልምዶች ምናልባት ከባባድ ሙያዊ ቃላት ላይጠቀሙ ይችላሉ፣ በእንግሊዝኛም ላያወሩ ይችላሉ፣ በየሚዲውም ላናያቸው እንችላለን፡፡ በሥራ ላይ ያሉትን የየዘርፉን ጎምቱ ጎምቱ ባለልምዶች በባትሪ ፈልገን የዚህ ሪፎርም ባለቤት ማድረጉ የስኬቱ ቁልፍ ተግባር ይመስለኛል፡፡

ለምሳሌ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስንገባ ከትንሽ ቢዝነስ ተነስተው በጥረታቸው በብዙ ትግል ብዙ ልምድ ያካበቱ፣ ሥራውን የሚያውቁ በስፋት ግን የማይታወቁ አምራቾች አሉ፡፡ የቢዝነሳቸው ግዝፈት ላይስበን ይችላል፡፡ ዕውቀታቸው ግን የሪፎርሙ የጀርባ አጥንት ሊሆን ይችላል፡፡ በየዘርፉ ስንሄድ ተመሳሳይ ቢዝነሶችን እናገኛለን፡፡ አገር በቀል ሪፎርም አገር በቀል ዕውቀት ይፈልጋል፡፡ ይህን አገር በቀል ዕውቀት አጎልብተን ሳይንሳዊ መሠረት እየሰጠን፣ በፋይናስ እየደገፍን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የግሉ ዘርፍ አደረጃጀቶች ትልቅ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡ ገንዘቡ ችግር ሊሆን እንደማይችል እያየን ነው፡፡ አሁን ኳሱ እኛ ሜዳ ላይ የመጣ በመሆኑ፣ እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን ከተወጣን የማይቻል አይደለም ባይ ነኝ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...