Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዳኑን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ብቸኛው የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ በመሆን እየተንቀሳቀሰ ያለው የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በውጭ ኩባንያዎች ይከፍሉ የነበረውን ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዳኑን ገለጸ፡፡ የኩባንያው 2011 የሒሳብ ዓመት ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በከፍተኛ ጥረት ያገኛቸውን ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በጠለፋ ዋስትና መልክ ከአገራችን እንዳይወጣ ማድረግ መቻሉን ገልጿል፡፡

በቀጣይም በተመሳሳይ በጠለፋ መድን ሽፋን ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡

በሌላ በኩልም በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር ከአጠቃላይና ከሕይወት ነክ የመድን ሽፋን ዘርፎች 698.7 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ እንዳገኘ ዓመታዊ ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው ዓረቦን ውስጥ 252.7 ሚሊዮን ብር ወይም 36.2 በመቶ በጠለፋ መድን ከተሰጠ ዓመታዊ ሽፋንና 408.8 ሚሊዮን ብር ወይም 60.7 በመቶ ከእያንዳንዱ የመድን ሽፋን ውል አግኝቷል፡፡ ግዙፍ ለሆኑ ነጠላ የአደጋ ሥጋት ሽፋን ዘርፍ 18.9 ሚሊዮን ብር ወይም 2.7 በመቶ የዓረቦን ገቢ ተገኝቷል፡፡ በተጨማሪም ከውጭ አገሮች የ2.5 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ መገኘቱንም ጠቅሷል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ከአጠቃላይ መድን 672.2 ሚሊዮን ብር ወይም 96 በመቶ የዓረቦን ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ከሕይወት መድን 26.5 ሚሊዮን ብር ወይም አራት በመቶ ገቢ ተመዝግቧል፡፡

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ኩባንያው በአጠቃላይ የ521 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ስለመፈጸሙ የሚገልጸው የኩባንያው ሪፖርት፣ በተመሳሳይ ጊዜ የኩባንያው የተጣራ ጉዳት ካሳ 328.8 ሚሊዮን ብር እንደነበርም አመልክቷል፡፡

የድርጅቱ የኢንቨስትመንት ገቢ 102.7 ሚሊዮን ብር የደረሰ መሆኑንና በአጠቃላይ ኩባንያው ከታክስ በፊት 144.5 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ ይህም አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 21.4 በመቶ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው የ15 በመቶ ክፍያ አንፃር የ42 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ኩባንያው ከጠለፋ መድን ሥራ ጋር በተያያዙ አበይት የተባሉ የተለያዩ ክንውኖች ስለማከናወኑ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ በተለይ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ጠንካራ ከሆኑ የጠለፋ መድን ሰጪ ተቋማት ጋር የድርብ ጠለፋ መድን (Retrocession) ውል መፈጸሙ ለአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህም ከሰሃራ በታች ካሉት አገሮች ጋር ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መሥራት የሚያስችል ስምምነት ስለመደረሱ አስታውቋል፡፡

እንደ ኩባንያው መረጃ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የኩባንያው ጠቅላላ ሀብት 1.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ42 በመቶ ብልጫ እንዳለው ያመለክታል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የኩባንያው ካፒታል 758.8 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ23 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

ኩባንያው የወደፊት ጉዞውን ለማሳካት ስትራቴጂያዊ አቅጣጫው የተመላከተበት “Vision 2027” እና የመጀመርያ አምስት ዓመት (እ.ኤ.አ. 2017/18 – 2021/22) ድረስ የተዘጋጀውን ስትራቴጂክ ዕቅድ በመተግበር በዓለም አቀፍ መድረክ ተፎካካሪ የሆነ፣ የፋይናንስ አቅሙ የጎለበተና የተመሰከረለት ኩባንያ እንዲሆን መሠረት የተጣለ ስለመሆኑ ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ በዚህም በአስገዳጅነት ለኩባንያው ከተሰጠው የጠለፋ መድን ሥራዎች በተጨማሪ የኩባንያውን አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅና የኩባንያውን የሰው ኃይል በዕውቀት በማደራጀት ብቁ ተፎካካሪ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባሻገር፣ ከውጭ ለማግኘት ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ሰፊ መግባባት ተደርሷል ተብሏል፡፡ ይህ ኩባንያ በዋናነት በጠለፋ መድን ወደ ውጭ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረትና እንደ ሌሎች የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያዎች በመሥራት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከዓመታዊ ዓረቦን ገበያቸው ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን በውጭ ምንዛሪ ለውጭ የጠለፋ የመድን ኩባንያዎች እንደሚያውሉ ይታመናል፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር በኢትዮጵያ የተቋቋመ የመጀመርያው ጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ ሲሆን፣ በጠቅላላ መድንና በሕይወት መድን ዘርፎች የጠለፋ መድን ሥራ ላይ የተሰማራ ተቋም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር ባለአክሲዮኖች ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ሰባት ባንኮች፣ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ 78 ግለሰቦችና አንድ የሠራተኛ ማኅበር ይገኙበታል፡፡ የድርጅቱ አጠቃላይ የተፈረመ ካፒታሉ 997.3 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች