Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከታክስ በፊት 767 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በተጠናቀቀው 2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 767 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ሲያሳውቅ፣ በባንኩ የተቀማጭ ሒሳብ የከፈቱ ደንበኞችን ቁጥር ከ5.3 ሚሊዮን በላይ ማድረሱ ተገለጸ፡፡

ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርቱ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን ከባለፈው ዓመት የ14 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ባንኩ ከታክስ በኋላ ያገኘው የትርፍ መጠን ደግሞ 657.7 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ134.3 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ታውቋል፡፡ ባንኩ ከሌሎች የግል ባንኮች በተለየ የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞቹን ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመር ችሏል፡፡ ይህም ከ16ቱ የግል ባንኮች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞች አድርጎታል፡፡ የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያመለክተውም በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የባንኩን አስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር በማሳደግ ከ5.3 ሚሊዮን በላይ ማድረስ የቻለው በአንድ ዓመት ብቻ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ደንበኞችን በማፍራት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ አስቀማጮች አፍርተዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ወጋገን ባንክ 1.31 ሚሊዮን፣ ዳሸን ባንክ 2.22 ሚሊዮን፣ አቢሲኒያ ባንክ 1.28 ሚሊዮን የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞች ያላቸው ከመሆኑ አንፃር፣ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከግል ባንኮች ቀዳሚ ያደርገዋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ከ25 ሚሊዮን በላይ የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የደንበኞቹን ቁጥር በዚህን ያህል በማሳደጉ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ላይም ለውጥ እንዲታይ አስችሏል፡፡ የ2011 የሒሳብ ዓመት ሪፖርቱ እንደሚያሳየውም፣ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 40 በመቶ ዕድገት በማሳየት 36.17 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ለተቀማጭ ገንዘብ መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት የግለሰቦች ተቀማጭ፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና በዘመኑ የተሠሩ ሌሎች በስትራቴጂ የተደገፉ ሥራዎች እንደሆኑ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡  

ባንኩ ካለው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን የተቀማጭ ቁጠባው 45.5 በመቶ ዕድገት በማሳት 23 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ የተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ቁጠባው ደግሞ 26.4 በመቶ በመጨመር 11.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ባንኩ አስተማማኝ የተቀማጭ ገንዘብ ምንጮች ላይ አተኩሮ መሥራቱን በዋናነት ይዞ መቀጠሉም፣ 63 በመቶ የሚሆነው የተቀማጭ መጠኑ የቁጠባ ተቀማጭ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ባንኩ ካገኘው ተቀማጭ ገንዘብ ተንቀሳቃሽ ተቀማጩ 32.4 በመቶን ሲሸፍን፣ የጊዜ ገደብ ተቀማጩ ደግሞ 4.1 በመቶ ብቻ ስለመሆኑም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ባንኩ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን በ11.4 በመቶ በማሳደግ በሒሳብ ዓመቱ 310.4 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ችሏል፡፡ በአገር ደረጃ በዚህ መስክ ያለው ለውጥ ብዙ የሚባል ባይሆንም፣ ባንኩ ከገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎቶች የውጭ ምንዛሪ የተሻለ ውጤት መገኘቱን በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ብድር የሰጠበት ዓመት ነው፡፡ ከዓመታዊ ሪፖርቱ መረዳት እንደሚቻለውም ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች 14.86 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ብድር ሰጥቷል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ብድር 24.36 ቢሊዮን ብር ሲደርስ በ2010 ዓ.ም. የነበረው የብድር ክምችት ላይ የ57.1 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

ከባንኩ ብድር ሥርጭት የአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት 39.9 በመቶ በመሆን ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡ የውጭ ንግድ 30.5 በመቶ ሲሸፍን፣ 5.4 በመቶ ደግሞ የፋብሪካ ምርቶች ላይ ውሏል፡፡ ባንኩ የብድር መጠኑን እያሳደገ ቢመጣም የተበላሸ የብድር መጠኑ 2.77 በመቶ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡

በ2011 የሒሳብ ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ትርፍ ከግብር በፊት 767 ሚሊዮን ብር መድረሱ ባፈለው ዓመት ከተገኘው በ14.5 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ የባንኩ ትርፋማነት ከባንኩ አክሲዮን አኳያ ሲመዘን 36.8 በመቶ ደርሷል፡፡

ባንኩ በ2011 ከፍተኛ ውጤት አግኝቶበታል ተብሎ የሚጠቀሰው አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢውን በ1.2 ቢሊዮን ብር በመጨመር 3.7 ቢሊዮን ብር ማድረሱ ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን ዓመታዊ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ባንክ ሆኗል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚያሳው፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ወጪ 60 በመቶ በመጨመር 2.94 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ የቀደመው ዓመት ወጪው 1.8 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በዚህን ያህል ደረጃ ወጪው ማደጉ ባንኩ ሥራውን ለማሳደግ በቅርንጫፍ ማስፋፋት፣ በመሠረተ ልማቶች፣ ቴክኖሎጂና የሰው ሀብት ላይ በስፋት በመሥራቱ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ በተቀማጭ ገንዘብ መጨመር ምክንያት የወለድ ክፍያ ብቻ በ414.7 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱም ለወጪው ዕድገት አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ የደመወዝ ወጪና ሌሎች ወጪዎች በ56.9 በመቶ ዕድገት ማሳየቱም ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ከሌሎች የግል ባንኮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው አዳዲስ ቅርንጫፎችን መክፈት የቻለው ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት 96 አዳዲስ ቅርንጫፎች ከፍቷል፡፡ ባንኩ 22 ንዑስ ቅርንጫፎችን ወደ ቅርንጫፍ በማሳደግ በሰኔ ወር መጨረሻ የአጠቃላይ ቅርንጫፍ ብዛት 389 ደርሷል፡፡ ከእነዚህ የባንኩ ቅርንጫፎች 314 የሚሆኑት ወይም 81 በመቶ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከፈቱ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባንኩ ባለ 16 ወለል ያለው የሽግግር ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ እያካሄደ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የ12 ፎቅ የኮንክሪት ሥራ አጠናቋል፡፡ ቋሚ ሀብትን ለማፍራት ባንኩ የያዘው ስትራቴጂ ላይ በማተኮር በሌሎች ከተሞችም መሰል ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት በወሊሶ ከተማ የግንባታ ፕሮጀክት ሲጀመር፣ በጅማ ከተማ የተያዘው ፕሮጀክት ደግሞ የዲዛይን፣ የአርክቴክቸርና መነሻ ሥራዎች ተጠናቀዋል ተብሏል፡፡ ወደ ፊትም ባንኩ በተለያዩ ቦታዎች ሕንፃዎችን ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ 46 ኤቲኤም ማሽኖችን በመጨመር ያለውን የክፍያ ማሽን ብዛት 84 አድርሷል፡፡ የሠራተኞች ቁጥር  ደግሞ 4,369 እንደሆነ የባንኩ መረጃ ያሳያል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች