Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሸን ባንክ ከታክስ በፊት 1.3 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ 25ኛ ዓመቱን ለመያዝ ዋዜማው ላይ የሚገኘው ዳሸን ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.3 ቢሊዮን ብር አተረፈ፡፡

ባንኩ የ2011 ዓመታዊ አፈጻጸሙን ለባለአክሲዮኖች ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንደተገለጸው፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት በ12 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ነው፡፡ ባንኩ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከግል ባንኮች ሁለተኛው ከፍተኛ የትርፍ መጠን እንደሆነም የሚያመለክት ነው፡፡ ከታክስ በኋላ የተመዘገበው የትርፍ መጠን ደግሞ 1.01 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ ከታክስ በኋላ የተገኘው የትርፍ መጠን ባለፈው ዓመት ከተገኘው 928.9 ሚሊዮን ብር አንፃር በ87.8 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው፡፡ ሆኖም የአንድ አክሲዮን ዋጋ ያስገኘው ትርፍ 408 ብር ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት 430 ብር ነበር፡፡

በሌሎች የባንኩ የሥራ አፈጻጸም ምቹ ውጤታማ የተባሉ ሥራዎች ስለመሠራታቸው የባንኩ ሪፖርት የሚያሳይ ሲሆን፣ በተለይም በሒሳብ ዓመቱ ከቀደሙት ዓመታት ብልጫ ያለው የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የባንኩ ዳሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነዋይ በየነ እንደገለጹት፣ በሒሳብ ዓመቱ ከ8.7 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም ከቀደመው ዓመት 24 በመቶ ዕድገት በማሳየት አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ወደ 44.7 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ችሏል፡፡

ከዚሁ የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ በቅርንጫፎቹ በመስኮት ደረጃ ከሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት 1.1 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ እንደቻለም ተገልጿል፡፡ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ የአስቀማጮች ቁጥር 62,713 እንደደረሰለትም ዓመታዊ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ባንኩ በአጠቃላይ የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞቹን ቁጥር በ2011 መጨረሻ ላይ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ስለመቻሉም ያሳያል፡፡

ዳሸን ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመቱ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያበደረው የገንዘብ መጠን በ40 በመቶ እንዳደገ የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት፣ ይህም አጠቃላይ የብድር ክምችት መጠኑን ወደ 32.4 ቢሊዮን ብር አሳድጎታል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ለብድር ያዋለው ገንዘብ 9.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በባንኩ ታሪክ በአንድ ዓመት ለብድር የዋለው ከፍተኛ ገንዘብ ነው፡፡ ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ካዋለው ብድር ውስጥ አብላጫውን ድርሻ የሚይዘው ለአገር ውስጥ ንግድ የተሰጠ ብድር ነው፡፡ ለማኑፋክቸሪንግና ለወጪና ገቢ ንግዶች የተሰጠው ብድር ተከታዮቹን ደረጃ ይይዛሉ፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ 536.2 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ ይህ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ1.5 መቶ ብቻ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዳሸን ባንክ ከግል ባንኮች አንፃር ሲታይ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሀብት መጠን ካላቸው ባንኮች አንዱ ነው፡፡

በ2011 መጨረሻ ላይ የባንኩ ጠቅላላ የሀብት መጠን 56.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት፣ ይህም ካለፈው ዓመት በ23 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑን ነው፡፡ ዳሸን ባንክ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢያቸው ከፍተኛ ከሆኑ ባንኮች አንዱ ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመትም አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢውን 5.6 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡

ይህ ዓመታዊ የገቢ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ1.6 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ ከግል ባንኮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኤትኤሞች ባለቤት ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 50 ኤትኤሞችን በማከል አጠቃላይ ያሉትን የኤትኤሞች ቁጥር 355 አድርሷል፡፡

በተመሳሳይ በሒሳብ ዓመቱ 487 የፖዝ ማሽኖችን በመጨመር አገልግሎት እየሰጠባቸው ያሉ የፖዝ ማሽኖችን ወደ 1,397 አድርሷል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 40 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 418 ማድረስ ችሏል፡፡ የባንኩ የሠራተኞች ቁጥርም 9,733 የደረሰ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ሠራተኞች ካሉዋቸው የግል ባንኮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች