ተሻሽሎ የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ሰሞነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ነበር፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች እየተንሸራሸሩ ነው፡፡ አዲሱ ረቂቅ በአንዳንድ ምርቶች ላይ ተጥሏል የተባለው የታክስ መጠን ከፍተኛ ነው የሚሉ ወገኖች የመኖራቸውን ያህል፣ የለም ተገቢ የሆነ ዕርምጃ ነው የሚለውም አስተያየት ይደመጣል፡፡ ረቂቁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲመከርበት እንደሰማነውም በአንዳንድ ምርቶች ላይ እንዲጣል የታቀደው የኤክሳይስ ታክስ መጠን እጅግ ስለመጋነኑ በመግለጽ ሲከራከሩበት ነበር፡፡
የእርሻ መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ ይሆናሉ የሚለውን ዜና አጣጥመን ሳንጨርስ፣ በትራክተሮች ላይ ሊጣል የታሰበው ኤክሳይስ ታክስ የተምታታ ምስል ይፈጥራል የሚለው አስተያየት ውኃ ሊያነሳ ይችላል የሚል እምነት ያሳድራል፡፡ ለምን እንዲህ እንደታሰበ ባናውቅም፣ ማብራሪያ ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡
አንዳንድ ምርቶች ደግሞ በእርግጥ ኤክሳይስ ታክስ ሊጣልባቸው ይገባል ወይ? የሚለውም አስተያየት ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡ ረቂቁ ገና የሚመከርበትና ሊሻሻሉ የሚችሉ ነገሮች እንደሚኖሩ ታሳቢ የምናደርግ ቢሆንም፣ በእርግጥም ኤክሳይስ ታክስ ከፍ ብሎ ሊጣልባቸው ይገባል ተብለው የተለዩ አንዳንድ ምርቶች ላይ ይህ ለምን ይሆናል? የሚለው ጥያቄ ብዙ ሊያነጋግር ይችላል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ሊጣል የታሰበው ኤክሳይስ ታክስ ጉዳይ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ እንደ አገር ከታሰበ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በዚህች አገር ኢኮኖሚ ላይ እያደረሱ ያሉትን አደጋ በቅጡ ፈትሸን መፍረድ ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ያገለገሉ መኪኖች ይዘው የሚመጡት ጣጣ ብዙ መሆኑ ነው፡፡ እነዚህን አገልግሎት ሰጥተው የቆዩ ተሽከርካሪዎችን በገፍ በማስገባት ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ አውቆ፣ በቶሎ የሚገደቡበትን መንገድ ሥራ ላይ አለማዋል ዋጋ አስከፍሏል፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ከመሸጫ ዋጋቸው በላይ ለመለዋወጫና ለመሰል ግብዓቶች ያስወጣሉ፡፡ እንደ አገር ከታሰበ ችግሩ ከዚህም የባሰ ነው፡፡ ያገለገለ ተሽከርካሪ የነዳጅ ፍጆታ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ በመከራ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ የሚገባ ነዳጅን ያለአግባብ እንዲባክን ማድረጉንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ አሮጌ ተሽከርካሪዎችን ለመግታት እንዲህ ያለ ሕግ መቅረፅና በአዳዲስ ተሽከርካሪዎች መተካት የሚለው ፈጽሞ ስህተት የለውም፡፡ አንዳንድ ወገኖች ግን አሮጌ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ታክስ አግባብ አይደለም ብለው፣ ስምምነቱ ምንን ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ ይጠይቃሉ፡፡
ባይሆን መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የታሰበው የኤክሳስ ታክስ መጠን መጨመሩን ሳይሆን ታክስ የተቀነሰላቸውን አዳዲስ መኪኖች ለማግኘትስ ምን ታስቧል? የሚለው ይሆናል፡፡ ስለዚህ አዳዲስ መኪኖችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት የሚቻልበት መንገድ መታሰብ እንዳለበት መሞገትና ለዚህ ዕውን መሆን መሠራት ይኖርበታል፡፡
እንደ አገር ዛሬ በተሽከርካሪዎች እየደረሱ ላሉት አሰቃቂ አደጋዎች አንዱ ምክንያት ያገለገሉ መኪኖች እንዳሻቸው ወደ አገር ያለ ከልካይ እንዲገቡ መደረጉ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን ረቂቅ ሕጉ አደጋ ሊሆን የሚችለው ኅብረተሰቡ በብዛት ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ምርቶችን ከነካ ነው፡፡ መንግሥት ይህን ሳያስብ ይቀራል ተብሎ ባይታሰብም፣ ከአሮጌ መኪና መግባትና አለመግባት ጋር ሙግት ከመግጠም በኤክሳይስ ታክሱ ምክንያት አብዛኛው ሕዝብ ላይ ጫና የሚያሳድሩ ምርቶች ተካተዋል ወይ ብሎ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በደንብ መሰመር ያለበት ጉዳይ ቢኖር፣ አሁን በረቂቅ ደረጃ በቀረበው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅና እስካሁን በሥራ ላይ ባለው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ መካከል ምን ልዩነት አለ? ምንስ ተለወጠ? የሚለው ነገር በደንብ የታየ አልመሰለኝም፡፡ ከአገለገሉ ተሽከርካሪዎች ውጭ ኤክሳይስ ታክስ የሚመለከታቸው ምርቶች የትኞቹ? እንዴት? እና በምን ያህል መጠን? ማስተካከያ እንደተደረገባቸው መጠናት አለበት፡፡
ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን የሚያስመጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች የአንዳንድ ተሽከርካሪዎችን መሪ በምን ዓይነት መንገድ እንዲዛወር አድርገው ሲሸጡ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከአገር ውጭ እንደ ዱባይ ያሉ ከተሞች መንደር ውስጥ በርካሽ ዋጋ መሪ አዟዙረው የሚያመጡት መኪና ምን ያህል አደጋ እንዳደረሰ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ አንዳንድ ምርቶች ከዚህ ጋር ተያይዞ የኤክሳይስ ታክስ አዋጁን ከቀደመው ጋር ሲያነፃፅረው እንደውም ቅናሽ የተደረገባቸው ምርቶች መኖራቸውን እንገነዘባለንና፣ በዚህ ዙሪያ እየሰማናቸው ያለ መረጃዎች ሥራ ላይ ያለውና ረቂቅ አዋጁ በማመሳከር ቢታይ ጥሩ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ዋናው ጉዳይ አዋጁ ከአገር ጠቀሜታ አንፃር ያለውን ጥቅም በቀዳሚነት መታሰብ ይኖርበታል፡፡ የአየር ብክለት ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተያዘ ነው፡፡
ለማንኛውም አሮጌ መኪኖች እንዲገደቡ ወይም እንዳይገቡ ጫና የሚያደርግ ሕግ ከተተገበረ፣ አዲስ ተሽከርካሪን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት የሚስችል ፖሊሲና ሕግ ሊኖረን ይገባል ማለት ነው፡፡ ዋናው መከራከሪያም ይህ ነው፡፡ ስለዚህ ዜጎችን ብሎም አገርን ለመታደግ ሊወጣ እንደታሰበውና ይህንን ለማሳካት የተደረገውን ተነሳሽነት ያህል፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ተሽከርካሪ ሊቀርብ የሚችልበት አሠራር መዘርጋትም የመንግሥት ኃላፊነት ይሁን፡፡