Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናነባሩ የፀረ ሽብር አዋጅ እንዳለ ውድቅ መደረግ የለበትም ተባለ

ነባሩ የፀረ ሽብር አዋጅ እንዳለ ውድቅ መደረግ የለበትም ተባለ

ቀን:

በሥራ ላይ ከዋለ ከአሥር ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውና በርካታ ኢትዮጵያውያንን ለእስር የዳረገው የፀረ ሽብርተኝት አዋጅ ቁጥር 652/2001፣ ሙሉ በሙሉ በአዲስ አዋጅ መተካት የለበትም ተባለ፡፡

አዋጁ ጉዳቱ ያመዘነ ሆኖ ቢቆይም ያበረከታቸው አስተዋጽኦዎችም እንዳሉ በመጠቆም፣ ሙሉ በሙሉ ሰርዞ ከዜሮ ከመጀመር መልካም የሆኑ አንቀጾች (ድንጋጌዎችን) አካቶ ማወጅ ተገቢ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር ሰኞ ታኅሳስ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በራዲሰን ብሉ ሆቴል ባደረጉት ውይይት ላይ፣ አዋጅ ቁጥር 652/2001 አገር ለማዳን አስተዋጽኦ እንደነበረው ተመልክቷል፡፡ ከአንድ ነገር ወደ ሌላ ሽግግር ሲደረግ የነበረውን አጥፍቶ ሳይሆን፣ ጠቃሚውን ይዞና በላዩ ላይ እየጨመሩ መሄድ ተገቢ መሆኑን ተወያዮቹ ተናግረዋል፡፡

አዋጅ ቁጥር 652/2001 ስለጊዜ ቀጠሮ በአንድ ተጠርጣሪ ላይ ከ28 ቀናት እስከ አራት ወራት ሊሰጥ እንደሚችል የደነገገ ቢሆንም፣ ስያሜው ጭምር በተቀየረውና ‹‹የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ›› በሚል በቀረበው ረቂቅ ላይ ግን የተባለ ነገር እንደሌለ ተጠቁሟል፡፡ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 15 (1) ሥር ተጠርጣሪን አለማሳወቅና መርዳት በሚለው ድንጋጌ፣ ‹‹እያወቁ በቂ ምክንያት ሳይኖረው›› የሚለውን፣ ‹‹ማወቅ እስከምን ድረስ ነው?›› እና ‹‹በሕግ ሚስጥርን ያለመግለጽ መብት›› የሚለው ንዑስ አንቀጽ (5) ደግሞ፣ በሥራ ላይ ያለው አዋጅም ተመሳሳይ ቃላት በመጠቀም ዜጎች ሲሰቃዩበት የነበረ መሆኑንና ግልጽ ሊደረግ እንደሚገባ በተወያዮች ተጠቁሟል፡፡ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ጋዜጠኞችና የሕክምና ባለሙያዎች በሕግ ሚስጥር ያለመግለጽ መብት እንዳላቸው ቢገልጽም፣ ወንጀል እንደተፈጸመ መረጃ ካላቸው ግን በመከላከያነት ማቅረብ እንደማይችሉ መገለጹ እርስ በርሱ የሚጋጭና ተገቢ አለመሆኑን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ የነበረው በዚህ መሆኑን በመጠቆም መስተካከል እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ድርጅቶችን በአሸባሪነት የመሰየም ሥልጣን ለሕዝብ ተወካዮቸች ምክር ቤት በአንቀጽ 18 (1) ሰጥቶ፣ በንዑስ አንቀጽ (2) ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አንድን ድርጅት በአሸባሪነት ሲሰይም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመገናኛ ብዙኃን ይፋ ካደረገ፣ በኢትዮጵያ ተፈጻሚ ይሆናል መባሉ እርስ በርሱ የሚጋጭና የአገርንም ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት በመሆኑ መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ረቂቁ በአንቀጽ 33 እንደደነገገው አከራይንና በቤቱ ውስጥ ሰዎችን ማኖርን በሚመለከት ያሰፈረው ሐሳብ ትችት ቀርቦበታል፡፡ አንድ የፓርላማ አባል እንደገለጹት፣ እሳቸው በሚኖሩበት ሶማሌ ክልል፣ ‹‹እንግዳ ሆቴል አያድርም፣ በነዋሪዎች ቤት ነው የሚቆየው፡፡ እንግዶቻቸውን ታዲያ እንዴት ነው የሚያስመዘግቡት?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የውጭ ዜጋን በሚመለከት አከራይ መረጃውን ለሦስት ዓመታት ማስቀመጥ አለበት መባሉ ተገቢ እንዳልሆነም ተወያዮቹ ገልጸዋል፡፡ ከአገሪቱ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አንፃር የሚመለከተው ተቋም እንዲይዝ ተብሎ እንዲስተካከልም ተጠይቋል፡፡

ተቋማትን በሚመለከት የፌዴራል ፖሊስ የመመርመር ሥልጣን ቢሰጠውም፣ በክልሎች ገብቶ የመያዝ ሥልጣን እንዲሰጠው ቢደረግ ጥሩ እንደሆነ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተጠርጣሪዎች እንዲያዙ ለፖሊስ ማስረከብ እንዳለበት እንጂ፣ መቼና በስንት ጊዜ ውስጥ ማስረከብ እንዳለበት ስላልተገለጸ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡

የረቂቅ ሕጉን ካዘጋጁት አንዱ የሆኑት ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን በሰጡት ምላሽ፣ አዋጅ 652/2001 እንዳለ አለመሰረዙንና ጠቃሚ የነበሩ ድንጋጌዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ከቤት ኪራይ ጋር በተገናኘ የተደነገገው ‹‹ያኖረ›› ስለሚል ለተወሰኑ ቀናትን ማስቀመጥ እንደማይከለክል ተናግረዋል፡፡ ሚስጥር መጠበቅ በሕግ መብት የተሰጠቸው የወንጀሉ መረጃ እያላቸው ዝም ቢሉ መከላከያ አይሆናቸውም የተባለው፣ የማይቀርና በሕዝብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ እያወቁ ዝም ካሉ እንጂ ሌሎች ሚስጥሮችን እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...