Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት በሩብ በጀት ዓመት ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች 43.6 ሚሊዮን ብር ማግኘቱ ተገለጸ

መንግሥት በሩብ በጀት ዓመት ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች 43.6 ሚሊዮን ብር ማግኘቱ ተገለጸ

ቀን:

የፍርድ ቤቶች ችግር የተነገረበት ውይይት ተደርጓል

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማለትም የፌዴራል የመጀመርያ፣ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በ2012 በጀት ሩብ ዓመት 43,625,408 ብር ለመንግሥት ማስገኘት መቻላቸው ተገለጸ፡፡

ፍርድ ቤቶቹ ገቢውን ማስገኘት ያስቻሉት የዳኝነት አገልግሎት ለማግኘት ከሚጠየቀው በጣም ዝቅተኛ ከሆነው የዳኝነት ክፍያ መሆኑን የተናገሩት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ናቸው፡፡

‹‹የዳኝነት አሁናዊ ሁኔታና የወደፊት ዕይታ›› በሚል መሪ ቃል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ (ኢሲኤ) ታኅሳስ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደ ጉባዔ ላይ ነው ይህንን የተናገሩት፡፡ ጉባዔው በኢትዮጵያ ታሪካዊና የመጀመርያው ቢሆንም፣ ዴሞክራሲ የመገንባት ራዕይ ይዘው በሚራመዱ አገሮች (State Of the Judiciary or Legal Year) በሚል ስያሜ በየዓመቱ ከፍ ባለ ሥርዓት እንደሚያከብሩ ጠቁመው፣ ኢትዮጵያም ከዚህ በኋላ እንደምትቀጥል አስረድተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 (1) ድንጋጌ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ነፃ የዳኝነት አካል ሆነው መቋቋማቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቷ፣ በተዋረድ የተደራጁት የፌዴራል የመጀመርያ፣ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የሥራ ቦታቸውን አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ አድርገው፣ በፌዴራል ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ የክልል ፍርድ ቤቶችም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 80 (4 እና 5) ድንጋጌ በተሰጣቸው የውክልና ሥልጣን የፌዴራል ጉዳዮችን እንደሚያዩ ገልጸው ደቡብ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ግን ውክልናቸው መነሳቱንና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 (2) ድንጋጌ፣ የፌዴራል ጉዳዮችን በሚያስተናግዱ ተዘዋዋሪ ችሎቶች አገልግሎት እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ እንግሊዝ ያሉ አገሮች ከ350 ዓመታት በፊት ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤትን በሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ደረጃ መመሥታቸውን አስታውሰው ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ጋና፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም በጥሩ የፍርድ ቤት ግንባታ ሒደት ላይ ቢሆኑምና ኢትዮጵያም ጀማሪ ብትሆንም፣ ከሌሎች አገሮች እየተማረች ዕርምጃዋን ማፋጠን የማትችልበት ምክንያት እንደሌለ ወ/ሮ መዓዛ ተናግረዋል፡፡

የሕዝብ አመኔታን ያተረፉ ፍርድ ቤቶችን ማቋቋም የሩቅ ግብ ቢሆንም፣ ሕዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያጣውን አመኔታ ለመመለስ ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ ከሌሎች አመራሮች፣ ዳኞችና የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር በመሆን ፈታኝ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በ2011 በጀት ዓመት በሦስቱም ፍርድ ቤቶች ዕልባት እንዲያገኙ ዕቅድ ተይዞባቸው ከነበሩት 256,941 መዛግብት ውስጥ 204,230 ወይም 83.5 በመቶ ለሚሆኑ ውዝፍ መዛግብት ውሳኔ መሰጠቱን ተናግረው፣ በ2012 ሩብ በጀት ዓመት ግን ከዕቅድ በላይ በመሥራት ከላይ የተጠቀሰውን ገቢ ለመንግሥት ማስገኘት መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በተያዘው ሩብ ዓመት 2,748 ንብረቶችን ለባለመብቶች ማከፋፈል መቻሉንና 64,621,188 ብር ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም አክለዋል፡፡

በሦስቱም ፍርድ ቤቶች 352 ዳኞችና ከ300 በላይ የድጋፍ ሠራተኞች መኖራቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷ፣ ተጨማሪ ዳኞችና ሠራተኞች ስለሚያስፈልጉ ለመቅጠር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት ለ1,415 ሕፃናት የዳኝነት አገልግሎት መሰጠቱንና በቂ ተከላካይ ጠበቆች መሾማቸውን አክለዋል፡፡ የክልል ተገልጋዮችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ የታገዘ የቃል ክርክር ማድረግ በመቻሉ፣ ተገልጋዮች ወደ አዲስ አበባ ቢመጡ በአማካይ ሊያወጡ ይችሉ የነበረውን ሰባት ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ከቪዲዮ ኮንፈረንስ በተጨማሪ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (SMS) አገልግሎት መስጠት እንደተቻለ፣ ፍርድ ቤትን በተቻለ መጠን የማዘመን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ወ/ሮ መዓዛ ገልጸዋል፡፡ የሦስቱን ፍርድ ቤቶች ተዓማኒነት ለማሻሻል በኔትወርክ ለማገናኘት እየተሠራ መሆኑን፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አዋጅ ቁጥር 684/2002 እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 ጨምሮ ለደንቦችና ለመመርያዎች ማሻሻያዎች በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ወ/ሮ መዓዛ ዘርዘር ያለና ሰፊ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አራተኛውን ዓመታዊ ጉባዔውን ታኅሳስ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በሳፋየር ሆቴል አካሂዷል፡፡ በጉባዔው የኦሮሚያ፣ የትግራይ፣ የአማራና የደቡብ ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች ዓመታዊ ክንውኖቻቸውንና ተግዳሮቶቻቸውን ጠቅለል አድርገው አስረድተዋል፡፡

በተለይ 2011 በጀት ዓመት በኦሮሚያ፣ በደቡብና በአማራ ክልሎች ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ችግሮች የነበሩ መሆኑን አስታውሰው፣ በዚያም ውስጥ ሆነው ፍትሕን በተቻለ መጠን ለማዳረስ መጣራቸውን አስረድተዋል፡፡ ሁሉም ክልሎች ሪፎርም እያደረጉ ቢሆንም የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠሟቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዳኞች አቅም ማነስ፣ የደመወዝና ጥቅማ የጥቅም አነስተኛ መሆኑና የክልል ዳኞች ውሳኔዎቻቸውን በእጅ የሚጽፉ በመሆኑ ወደ ሰበር አቤቱታ ሲቀርብ የማይነበብ መሆኑን በመጥቀስ ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል፡፡ ይህ ችግር በተለይ በአማራ ክልል ከፍ ብሎ እንደሚታይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብዬ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ክልሎች ሪፎርሙን በየግላቸው ከሚያከናውኑ አንድ ላይ ተሰባስበው ቢያደርጉት እንደ አገር ጠቀሜታ እንዳለው አቶ አብዬ ጠቁመው፣ ለየብቻ መሆኑ ተመሳሳይ ፍትሕ ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ የዳኞችን አቅም ለመገንባትና ካደጉ አገሮች ልምድ ለመውሰድ ምንም ዓይነት መንገድ ስለሌላቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲያመቻች ተጠይቋል፡፡     

የማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾች በዳኞች ሥራ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆኑንና ደረቅ ወንጀሎችን ጭምር የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ ግፊት እየፈጠሩ ስለሆነ፣ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በሐረሪና በጋምቤላም በዋናነት የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ችግር እንዳለባቸው እንደ ችግር ተነስቷል፡፡ በደቡብና በአማራ ክልሎች ፍርድ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ በአማራ ክልል ዳኛ መገደሉንና ሌሎችም ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቶች በዚህ ላይ መሥራት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

በደመወዝና ጥቅማ ጥቅም፣ እንዲሁም በሌሎችም ጉዳዮች ላይ እየሠሩ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ መዓዛ፣ ችግሩ አገር አቀፍ በመሆኑ መንግሥት በጀት እንደሌለውና እንዲታገሱ ስለተነገራቸው እንጂ ዝም እንዳላሉ ተናግረዋል፡፡ የዳኞችን ጽሑፍ ማስቸገር በተመለከተ የኮምፒዩተር ሥልጠና እንዲወስዱ እንደሚደረግ፣ ለጊዜው የሚነበብ ጽሑፍ ያላቸውን መቀበል እንዲቻልና ለወደፊቱ ግን ዳኞች ሲቀጠሩ ‹‹የሚነበብ ጽሑፍ ያለውና በኮምፒዩተር መጻፍ የሚችል›› የሚል መሥፈርት በሥራ ማስታወቂያ ላይ መካተት እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...