ኮንቬንሽኑ የዳኝነት ሉዓላዊነትን የሚጋፋ ቢሆንም ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል ተብሏል
በውጭ አገር የተሰጠ የግልግል ዳኝነት ውሳኔን የመጨረሻ ውሳኔ አድርጎ የመቀበልና የማስፈጸም ግዴታን በተዋዋይ አገሮች ላይ የሚጥለው “የኒውዮርክ ኮንቬንሽን” በሚል ስያሜ በስፋት የሚታወቀው፣ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ስምምነትን ፓርላማው እንዲያፀድቅ ተጠየቀ፡፡
ፓርላማው ይህንን ስምምነት እንዲያፀድቅ የተጠየቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በላከው የስምምነቱ ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን፣ ፓርላማው ማክሰኞ ታኅሳስ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ወቀት የቀረበለትን ረቂቅ ተመልክቶ በዝርዝር እንዲታይ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት፣ እንዲሁም ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡
“በውጭ አገር የተሰጡ ግልግል ዳንኝት ውሳኔዎችን ዕውቅና የመስጠትና የመፈጸም ስምምነት” የተሰኘውን ዓለም አቀፍ ስምምነት በማፅደቅ፣ የስምምነቱ አባል የሆነ አገር በሌላ አገር ለተሰጠ የግልግል ዳኝነት ዕውቅና የመስጠትና የመፈጸም ግዴታ ይኖርበታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በውጭ አገር የግልግል ዳኝነት የተሰጠው ውሳኔ አስገዳጅና የመጨረሻ ውሳኔ ስለሚሆን፣ ስምምነቱን የተቀበሉ አባል አገሮች ውሳኔውን ከማስፈጸም ውጪ በውሳኔው ላይ በራሳቸው የሕግ ሥነ ሥርዓትም ሆነ ውሳኔውን ባሳለፈው የውጭ አገር የዳኝነት አካል ላይ ይግባኝ የማለት መብት አይኖራቸውም፡፡
ስምምነቱን ለማፅደቅ ለፓርላማው የቀረበው ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ የሆነው አባሪ ሰነድ፣ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች አስቀምጧል፡፡
ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ ከሚጥላቸው ግዴታዎች መካከል እንደ ጉዳት ሊታይ የሚችለው መሠረታዊ ነጥብ፣ በሉዓላዊነት ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች በሌላ የስምምነቱ አፅዳቂ አገር የተሰጠ የግልግል ዳኝነት ውሳኔን ተቀብለው ለማስፈጸም እንደሚገደዱ፣ ይህም የአገሪቱን የዳኝነት ሉዓላዊነት የሚጋፋ መሆኑን ማብራሪያው ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም “በዚህ ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቶች እንደገና በይግባኝ መልክ ውሳኔውን ማየት የለባቸውም የሚለው ድንግጋጌ ውሳኔው መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለው ሆኖ ሲገኝ፣ ጉዳዩ በሰበር እንዲታይ ማየትን ይከለክላል ወይ የሚለው ነጥብ ላይ የተለያየ አረዳድ ያለ ሲሆን፣ ስምምነቱ ሲፀደቅ የአገሪቱ የሕግ አካል ስለሚሆን ፍርድ ቤቶች ሕግን የመተርጎም ሥልጣናቸውን በመጠቀም የተለያዩ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ሥልጣን ይኖራቸው ወይም አይኖራቸው እንደሆነ አቋም የሚይዙበት ጉዳይ ይሆናል፤” በማለት ማብራሪያው ያስረዳል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ሥር ከተዘረዘሩት መሠረታዊ መብቶች መካከል አንዱ ፍትሕ የማግኘት መብትን በተመለከተ በአንቀጽ 37 (1) ሥር የተደነገገው ይገኝበታል፡፡
አንቀጹ፣ “ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፤” ሲል ይደነግጋል፡፡
በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ በአንቀጽ 20 (6) ላይ ደግሞ፣ “የተከሰሱ ሰዎች ክርክሩ በሚታይበት ፍርድ ቤት በተሰጠባቸው ትዕዛዝ ወይም ፍርድ ላይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት አላቸው፤” በማለት ይደነግጋል፡፡ በምዕራፍ ሦስት ሥር የተዘረዘሩትን መሠረታዊ መብቶች ተፈጻሚነትና አተረጓጎምን በተመለከተ በአንቀጽ 13 (1) ላይ ደግሞ፣ “በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና የዳኝነት አካላት በዚህ ምዕራፍ የተካተቱትን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፤” ሲልም ይደነግጋል፡፡
ለፓርላው የቀረበው የስምምነቱ ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅን ለማብራራት የተያያዘው ማብራሪያ ሰነድ፣ “የኒውዮርክ ስምምነት ምንም ጉዳት አያስከትልም ብሎ ማስቀመጥ ባይቻልም፣ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል፤” ሲል ያስረዳል፡፡
ኢትዮጵያ ስምምነቱን ካፀደቀች የውጭ ኢንቨስተሮች በግልግል ዳኝነት መፍቻ መንገዱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑ፣ ኢትዮጵያን የውል አለመፈጸም ሥጋት የሌለባት አገር በማድረግ አበዳሪዎች በአነስተኛ ወለድ እንዲያበድሩ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር፣ ይህም ኢንቨስተሮችን የሚያበረታታ እንደሚያደርገው በፋይዳነት ተዘርዝረዋል፡፡
በንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች የሕግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አቶ ምሕረተአብ ልዑል በትዊተር ገጻቸው የስምምነቱ መፅደቅ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው፣ እስከ ዛሬ ድረስም የሚያማክሯቸው የውጭ ኩባንያዎች አዘውትረው የሚያነሱት መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ ማፅደቂያ አዋጅ በስምምነቱ ላይ ተዓቅቦዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ እነዚህም የስምምነቱ አባል ባልሆኑ አገሮች የሚሰጥ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ በኢትዮጵያ በአስገዳጅነት ተፈጻሚ እንደማይሆን፣ ንግድ ነክ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች ላይ ብቻ ስምምነቱ ተፈጻሚ እንደሚሆንና ስምምነቱ ከመፅደቁ በፊት ውሳኔ ያገኙ ወይም በመታየት ላይ የሚገኙ ጉዳዮች ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው የሚገልጹ ናቸው፡፡