Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዴፓ ለውጡ ወደ መክሸፍ ደረጃ መቃረቡን አስታወቀ

ኢዴፓ ለውጡ ወደ መክሸፍ ደረጃ መቃረቡን አስታወቀ

ቀን:

ምርጫው እስከ ሁለት ዓመት እንዲራዘም ጠይቋል

ላለፉት 18 ወራት ሲካሄድ የነበረውና በሕዝብ ውስጥ ከፍተኛ የለውጥ ተስፋ ፈጥሮ የነበረው ‹‹የለውጥ ሒደት›› በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ መክሸፍ ደረጃ ተቃርቧል ሲል፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አስታወቀ፡፡

ኢዴፓ ይህን ያስታወቀው ማክሰኞ ታኅሳስ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ‹‹ቀዳሚ ትኩረት ለአገራዊ ህልውና›› በሚል ርዕሰ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡ በመግለጫው የፓርቲውን ውስጣዊ ሁኔታ፣ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ፣ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን፣ እንዲሁም መጪውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት የለውጡ ሒደት ወደ መክሸፍ ደረጃ ተቃርቧል ለማለት ያስቻለው ምክንያት እንዳለ የፓርቲው የቀድሞው ሊቀመንበር፣ አሁን ደግሞ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ምክንያቶቹን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

እንደ አቶ ልደቱ ገለጻ ከሆነ ለውጡ በሕዝብ ትግል ከመጣ በኋላ፣ ገዥው ኢሕአዴግ ብቻውን አድራጊ ፈጣሪ መሆኑ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በኢዴፓ በኩል የቀረበው የሽግግር ኮሚሽን የማቋቋም ሒደት ተቀባይነት ማጣቱም አንዱ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የችግሩ አካል የሆነውና በሕዝብ ትግል የተሸፈነው ኢሕአዴግ የሒደቱ አካል ነው እንጂ መሆን የሚችለው፣ ብቻውን የሽግግሩን ሒደት ሊመራ አይችልም፡፡ ስለዚህም ይህንን የሽግግር ሒደት የሚመራ አንድ ሁለን አቀፍ የሆነ ኮሚሽን ማቋቋም አለበት ስንል ነበረ፡፡ ነገር ግን እንደሚታወቀው የሽግግሩን ሒደት የሚመራ የተቋቋመ ኮሚሽን የለም፡፡ ኢሕአዴግ በተለመደው መንገድ እኔ አሻግራችኋለሁ በሚል የተሳሳተ መስመር ነው ራሱን ይዞ የቀጠለው፡፡ ስለዚህ አንዱ መሠረታዊ የነበረው፣ ኢሕአዴግ አሻጋሪም ተሻጋሪም ሊሆን አይችልም የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም፤›› ሲሉ አቶ ልደቱ አንደኛውን ምክንያት አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለውጡ የሚመራበት ፍኖተ ካርታ አለመዘጋጀቱ ሌላው የለውጡ መክሸፍ ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከፖለቲካ ኃይሎች ከድርድር የመነጨ ፍኖተ ካርታ ያስፈልገናል፡፡ ዝም ብሎ በዘፈቀደ ሊመራ የሚችል የለውጥ ሒደት ሊሆን አይችልም፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው አካል ምን እንደሚሠራ የሚነግረን ነው፡፡ ነገ ወዴት እንደምንሄድም አናውቅም፡፡ አስቀድሞ የተጻፈ ኅብረተሰቡ ሊከታተለውና ኦዲት ሊያደርገው የሚችል ፍኖተ ካርታ የለውም፣ በዚህ ረገድም አልተሳካም፤›› በማለት አክለው አስረድተዋል፡፡

ሌላው ለውጡ እየከሸፈ ነው ያሉበት ምክንያት ደግሞ አገሪቱ ውስጥ የሚታዩትን የፖለቲካ ቅራኔዎች መሠረት በማድረግ መሆኑን አቶ ልደቱ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በቅራኔ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በእርስ በርስ መተላለቅ ውስጥ ነው የኖርነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የአሸናፊነትና የተሸናፊነትን አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስቆም የሚችል፣ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት መምጣት አለበት፡፡ ነገር ግን ይህንንም በሚመለከት የተሠራ የለም፡፡ አሁንም በለውጥ ኃይሉ የተቋቋመ የዕርቅ ኮሚሽን አለ፡፡ ነገር ግን እኛ ከምንጠብቀው ጋር በተያያዘ አገራዊ የሆነና ትርጉም ያለው ዕርቅ ለማምጣት የሚያስችል ሥራ እያከናወነ አይደለም፤›› በማለት አሁንም በአስቸኳይ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት እንዲካሄድ አቶ ልደቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አገሪቱ አሁን ለምትገኝበት ደረጃ ያበቃት መዋቅራዊ ችግር እንደሆነ ፓርቲያቸው እንደሚያምን የገለጹት አቶ ልደቱ፣ ለዚህ ችግርም መዋቅራዊ መፍትሔ አስፈላጊነት ላይ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

መዋቅራዊ ችግሩ ከሕገ መንግሥቱና ከብሔር ተኮር ፌዴራላዊ አደረጃጀት ጋር የተያያዘ ነው ያሉት አቶ ልደቱ፣ ‹‹ለእነዚህ መዋቅራዊ ችግሮች መዋቅራዊ መፍትሔ ሳንሰጥ ወይም በእነዚህ መሠረታዊ የፖለቲካ ቅራኔዎች ላይ ብሔራዊ መግባባት ሳንፈጥር ሊሳካ የሚችል የሽግግር ሒደት የለም፡፡ በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥቱም ሆነ ብሔር ተኮር የሆነው የፌዴራል አደረጃጀት እስከ አሁን አልተሻሻለም፡፡ ሊሻሻል እንደሚችል የተገባ ቃልም የለም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሳይከናወኑ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼውንም ቢሆን ሊሳካ የሚችል የሽግግር ሒደት የለም፡፡ ለዚህ ነው የከሸፈ ነው የምንለው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

ከመጪው ጠቅላላ ምርጫ ጋር በተያያዘ ደግሞ ኢዴፓ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊና ለሕዝብ መንግሥት መመሥረት የሚያበቃ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ አለ ብሎ እንደማያምን የገለጸ ቢሆንም፣ ነገር ግን ምርጫው የግድ የሚካሄድ ከሆነ በምርጫው እንደሚወዳደር አስታውቋል፡፡

ከዚህ አንፃር ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለምርጫ ምቹ አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ ተደርሶ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ፣ እንሳተፋለን የሚሉት ሐሳቦች እርስ በርስ አይቃረኑም ወይ ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ አቶ ልደቱ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በድሮው ኢሕአዴግ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንደማይካሄድ እያመንን፣ ነገር ግን በሒደቱ መሳተፍ ለአገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ብለን ከማሰብ ነው ስንሳተፍ የነበረው፡፡ አሁንም ያንን መድረክ ለፅንፈኛና ለብሔርተኛ ኃይሎች አሳልፈን ጥለን ልንወጣ አንችልም፡፡ በሚኖሩ የክርክር መድረኮች ለኢትዮጵያ ሕዝብ አደጋውን ለማሳየት፣ ወዴት አቅጣጫ መሄድ እንዳለብን በአስተሳሰብ ደረጃ አቅጣጫ ለማመልከት መድረኩን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ስለዚህ በምርጫው ሊመጣ የሚችለው አደጋ ራሱ እንዲመጣጠን ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖረናል ብለን እናምናለን፡፡ በእኛ እምነት ግን በምንም ተዓምር ምርጫው አሁን መካሄድ የለበትም፡፡ ለምርጫ ዝግጁ የሆነ ነባራዊ ሁኔታም፣ በምርጫ የሚፈታም ችግር የለም፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሠረት የተሳካ የሽግግር ሒደት በአገሪቱ ማካሄድ እስኪቻል ድረስ፣ መጪው ጠቅላላ ምርጫ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ መራዘም እንዳለበት ኢዴፓ አሳስቧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በሕገወጥ መንገድ ተወስደውብኛል ያላቸውን ቢሮዎቹንና የተለያዩ ንብረቶቹን የማስመለስ ሥራ እንዲከናወን መወሰኑም በመግለጫው ወቅት ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...