Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሰሚ ያጣው የተጫዋቾች አቤቱታና ወርኃዊ ክፍያ

ሰሚ ያጣው የተጫዋቾች አቤቱታና ወርኃዊ ክፍያ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተጨዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ጋር በተያያዘ ህልውናው አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩበት ነው፡፡ በአደረጃጀቱም ሆነ በእግር ኳሳዊ ብቃቱ የነበረውን እንኳ ማስቀጠል የተነሳው ሊጉ በተለይም ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ማሻቀብ የጀመረው የተጨዋቾች የፊርማ ገንዘብና ወርኃዊ ክፍያ፣ ክለቦችን ለከፋ የፋይናንስ ቀውስ መዳረጉን ተያይዞታል፡፡ በፋይናንስ ቀውሱ ምክንያት ወርኃዊ ክፍያ መክፈል ያልቻሉ ክለቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡

ችግሩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ዕጣ ፈንታችን ምን ሊሆን ነው? በሚል ቅሬታቸውን ለክለብ አመራሮች የሚያቀርቡ ተጫዋቾች በውላቸው መሠረት ክፍያ የማይፈጸምላቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ እየተገደዱ ስለመሆናቸው ጭምር መደመጥ ጀምሯል፡፡

ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንዳንድ ተጫዋቾች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ጉዳዩን አስመልክቶ የውድድር ዓመቱ መርሐ ግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ ስፖርት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክለብ አመራሮች ጋር በቢሾፍቱ ባዘጋጁት መድረክ፣ ለተጫዋቾች የሚከፍሉት የፊርማና ወርኃዊ ክፍያ የአገሪቱን ክለቦች አቅም ያገናዘበ ስላልሆነ አንድ ክለብ ለአንድ ተጫዋች መክፈል የሚገባው ክፍያ 50,000 ብር እንዲሆን መወሰናቸውን ያስታውሳሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በወቅቱ የተወሰነውን ውሳኔ መነሻ በማድረግ ተጫዋቾች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበረ መሆኑን የሚናገሩት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ “ከፍተኛ በጀት ተይዞለት የተላለፈው ውሳኔ አሁን ላይ የውኃ ሽታ መሆኑ ሳያንስ፣ በርካታ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች አንዳንዶቹ የሦስት ወር፣ ሌሎች ደግሞ የአምስት ወር ደመወዝ መክፈል ተስኗቸዋል፡፡ ምክንያቱም የቢሾፍቱ ውሳኔ ወረቀት ላይ ካልሆነ መሬት ላይ የሌለ በመሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቹ ክለብ የተጫዋቾቻቸውን ወርኃዊ ክፍያ ገደብ ባስቀመጡ ማግስት ቀድሞ በነበረው አካሄድ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የቆዩ መሆናቸው የምናውቀው ምስጢር ነው፤” በማለት በእያንዳንዱ ክለብ ውስጥ ያለውን ሕገወጥ የአሠራር ሥርዓት ያስረዳሉ፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን የአራት ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር መከናወኑ ይታወቃል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ከሚገኙት 16 ቡድኖች መካከል አምስት ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ከሦስት እስከ አምስት ወር ለተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ መክፈል እንዳልቻሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃው እንዳለው ተጫዋቾቹ ይናገራሉ፡፡ በውድድር ዓመቱ አዲስ ዝውውር ያከናወኑ ተጫዋቾች አንዳንዶቹ ውል በተገባላቸው መሠረት ክፍያ ባያገኙም፣ በአሠልጣኞቻቸው ምልጃ ብቻ ለክለቡ ሲጫወቱ የቆዩ ስለመኖራቸው የሚናገሩም አልጠፉም፡፡ በዚህ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ እንዳሉ ከሚነገርላቸው ክለቦች መካከል፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ከተማ፣ ሆሳዕና ከተማ፣ ስሁል ሽረ ይጠቀሳሉ፡፡

ሊጉን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦች፣ ለተጫዋቾቻቸው በገቡት ውል መሠረት ግዴታቸውን ሊፈጽሙ እንደሚገባ ያምናል፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው ሁኔታ ለሊጉ ቀጣይነት በራሱ ችግር ስለሚኖረው በዚህ ሳምንት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አንድ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ያስረዳሉ፡፡

ተመሳሳይ አቤቱታዎች ከዓምና ጀምሮ የቀረቡ መሆኑን የሚናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በወቅቱ በጅማ አባ ጅፋርና በድሬዳዋ ከተማ ክለቦች የሚጫወቱ ተጨዋቾች ከክፍያ ጋር በተያያዘ ለፌዴሬሽኑ ባቀረቡት ክስ መሠረት ፍትሕ ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ አሁንም ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ጣልቃ እንደሚገባ ያስረዱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በመርሐ ግብሩ አራተኛ ሳምንት እንደዚህ ዓይነት አለመግባባት ውስጥ መገባት እንደሌለበት ጭምር ይናገራሉ፡፡

ከክፍያ ጋር ተያይዞ በክለቦችና ተጫዋቾች መካከል እየተደመጠ የሚገኘው እሰጣ ገባ ለራሳቸው ለክለቦቹም ሆነ ለተጨዋቾቹ አልፎም ለእግር ኳሱ እንደማይበጅ የሚናገሩት ኮሎኔል አወል፣ ጉዳዩ “ክፈል አልከፍልህ” ወደሚል ክርክር ከማምራቱ በፊት መለስ ብሎ ክለቦችም ሆኑ ተጫዋቾች የገቡት ውል ምን ይላል ብለው ወደ ራሳቸው መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡

በቅርቡ በይፋ የተቋቋመው የፕሮፌሽናል ተጫዋቾችና አሠልጣኞች ማኅበር (ፒኤፍኤ) በበኩሉ ክለቦችም ሆኑ ተጫዋቾች ችግሩን ቀደም ሲል በገቡት ውል መሠረት እንዲፈቱ ይጠይቃል፡፡ የፒኤፍኤ ዋና ጸሐፊ አቶ ሳምሶን ዮሴፍ፣ ማኅበሩ እንዲቋቋም መነሻ የሆነው እነዚህና መሰል ችግሮች በአባሎቻቸው ሲደርስ ለምን ብሎ ለመጠየቅና መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ክለቦች ለአሠልጣኞችም ሆነ ለተጨዋቾች የገቡትን ውል በመፈጸም ረገድ ሲንከባለል የመጣ ችግር እንዳለባቸው የሚስረዱት ዋና ጸሐፊው፣ “ከእንግዲህ በነበረው መቀጠል ከባድ ነው፡፡ ችግሮች ካሉ ቁጭ ብሎ መነጋገር ይቻላል፣ አሠልጣኞችም ሆኑ ተጫዋቾች በገቡት ውል መሠረት ግዴታቸውን አውቀው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፣ ቀጣሪው ተቋምም በተመሳሳይ፡፡ ማኅበሩ ባለው መረጃ መሠረት በርካታ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ወርኃዊ ክፍያ አለመክፈላቸው እናውቃለን፡፡ ይህንኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንዲያውቀው የምናደርግ ይሆናል፤” ብለዋል፡፡

ከወርኃዊ ክፍያ ጋር በክለቦችና ተጨዋቾች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ትክክለኛ ብቻ ሳይሆን የእነሱም ጥያቄ ስለመሆኑ፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የክለብ አመራሮች ከማስረዳት ባለፈ ውሳኔ የእነሱ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ችግሩ መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ የክለቦቹም ሆነ የሊጉ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆንም ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...