Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአገር ከቤተሰብ ግንባታ አንፃር

አገር ከቤተሰብ ግንባታ አንፃር

ቀን:

በተመስገን ተጋፋው

አንድ አገር እንድታድግና ዜጎቿም በሥነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ቤተሰብና ትምህርት ቤት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ይህን መሠረተ ሐሳብ የሰነቀ የውይይት መድረክ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ታኅሣሥ 16 ቀን 2012 .. አካሂዷል።
በሁለተኛው ወርኃዊ መድረኩ በአገር ግንባታ ላይ ‹‹የቤተሰብ ሚና ምን ይመስላል?›› በሚል መሪ ሐሳብ በጌት ፋም ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የቤተሰብ አማካሪዎች፤ የሥነ ልቦና ምሁራን፣ የመንግሥት ሹማምንት፣ ተማሪዎችና ወላጆች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ የባህል፣ የኪነ ጥበብና የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ነቢዩ ባዬ (ረዳት ፕሮፌሰር) አገር ለመገንባት ቤተሰብ ልጆቻቸውን ጊዜ በመስጠትና በትምህርታቸው ላይ ድጋፍ በማድረግ በሥነ ምግባር የታነፁ ልጆች እንዲሆኑ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ልጆች የሚነገራቸውን የሚሰሙ ስለሆነ ትምህርት ቤት ሆነ ቤተሰብ ክትትል በማድረግና የሚፈልጉትን ነገር በመስጠት ሐሳባቸውን በመጋራት በፈለጉት መልኩ ስኬታማ የሚሆኑበትን መንገድ መፍጠር ተገቢ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ይኼም ከሆነ ለአንድ አገር በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል የገለጹት ኃላፊው፣ በተቃራኒው ደግሞ በሥነ ምግባር ያልታነፁ ልጆችን መፍጠር በአገሪቷ ላይ ትልቅ ችግር መፍጠሩ አይቀርም ብለዋል፡፡

‹‹ማኅበረሰቡም ሆነ መንግሥት የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት እጅና ጓንት ሆኖ መሥራት ይገባል፤›› በማለትም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡት / ብሌን ተዋበ እንዳሉት፣ በአስተሳሰብና በስሜቱ ጠንካራ የሆነ ትውልድ ለማፍራት ልጆችን ገና ከሕፃናንነታቸው ጀምሮ በጥንቃቄ ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡

አገር ከቤተሰብ ግንባታ አንፃር

 

ሕፃናት በአማካይ እስከ ስምንት ዓመታቸው ድረስ የተነገራቸውን አምነው የሚቀበሉ በመሆኑ ቤተሰብም ልጆቻቸውን በመቅረብ፣ የሚፈልጉትን ነገር በማሟላትና በማወያየት ጤናማ የሆኑ ልጆችን ማፍራት እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ እጅግ ጥንቃቄ ካልተደረገ እያደጉ ሲመጡ ቤተሰብ ከማስቸገርም አልፎ አገርን የሚያውኩ ዜጎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ በሥጋት ውስጥ ያደገ ልጅ ሕይወቱን በሙሉ በሥጋት የተሞላ አስተሳሰብና ስሜቱ የተጎዳ ሊሆን ስለሚችል መሥራት ከሚችለው በጎ ነገር ይልቅ፣ የሚሳሳተው ነገር ስለሚያሠጋው በአዕምሮው ላይ የጤና ቀውስ ሊፈጥርበት እንደሚችል / ብሌን ሳይገልጹ አላለፉም።
አገርን ለመገንባት ማኅበረሰቡም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት አንድ ላይ በመሆን በትምህርት ቤቶች፣ በሃይማኖት ቦታዎች፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ላይ ሕፃናት ልጆችን በሥነ ምግባራቸው የታነፁ እንዲሆኑ መሥራት እንደሚገባ፣ ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ ከባህልና ያላት ዕድገት አንድ ዕርምጃ ከፍ እንደሚል ተናግረዋል፡፡

አንድ ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲኖረውና ብቁ እንዲሆን ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል አንዱ ቤተሰብ መሆኑን፣ ልጆች በሕይወታቸው ውጤታማና ሙሉ የሚሆኑት በትምህርት ቤትና በጤናማ ቤተስብ የሚኖሩ ከሆነ ብቻ እንደሆነም ተንፀባርቋል።
አገርና ቤተሰብ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ነገሮች እንደሆኑና አንዱን ለመገንባት ሌላኛው ላይ መሥራት የግድ እንደሚል በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ ‹‹አገር ማለት ትውልድ ነው፡፡ ወላጆች ደግሞ ለልጆቻቸው የሚፈልጉትን ነገር በማሟላትና ሐሳቦቻቸውን በመደገፍ የተማሩና በሥነ ምግባራቸው የታነፁ ሰዎች እንዲሆኑ መሥራት ይገባል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

አንድ ልጅ ሲፈጠር የራሱ የሆነ ችሎታ ያለው በመሆኑ፣ ወላጁ ይህን የታመቀ ችሎታውን በማገዝና በመርዳት ከአጠገቡ ሲሆን አንድ አገር ሊያድግ እንደሚችል አስታውሰዋል፡፡ በአሁን ወቅትም በሕፃናት ላይ የሚሠራው ሥራ አነስተኛ በመሆኑ መንግሥትና ማኅበረሰቡ በአንድነት መነሳት እንደሚገባቸው የገለጹት አሠልጣኙ፣ ኢትዮጵያም በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዕድገቷ ከፍ እንድትል ሕፃናት ላይ መሥራት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መድረኩን የከፈቱት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ / ቡዜና አልከድር፣ አገር ማለት ሰውን እንደመሆኑ ሰው ደግሞ የሚኖረው በቤተሰቡ ውስጥ ነውና አገር መገንባት ስንፈልግ በቀጥታ ቤተሰብን መገንባት አለብን ብለዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የአገር ግንባታ ከየት ይጀምራል? በሚል ርዕስ ኅዳር 10 ቀን 2012 .. በግራንድ ኤሊያና ሆቴል የመጀመሪያዎቹ ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...