Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፓርቲዎች ለምርጫ ከሚያቀርቧቸው ዕጩዎች 50 በመቶ ያህሉ ሴቶች እንዲሆኑ ምክረ ሐሳብ ቀረበ

ፓርቲዎች ለምርጫ ከሚያቀርቧቸው ዕጩዎች 50 በመቶ ያህሉ ሴቶች እንዲሆኑ ምክረ ሐሳብ ቀረበ

ቀን:

በ2012 ዓ.ም. ይከናወናል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ እያንዳንዱ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከሚያሳትፏቸው ዕጩዎች 50 በመቶ ያህሉን፣ ይህም ካልተቻለ ቢያንስ 40 በመቶውን ሴት ዕጩዎች እንዲያደርጉ ምክረ ሐሳብ ቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት በ2012 አገራዊ ምርጫ ላይ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማጎልበት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ባዘጋጀው የውይይት መድረክ፣ ግማሽ ያህሉ የኅብረተሰብ ክፍል ሴት በሆነበት አገር፣ ሴቶች ወደ ፖለቲካው፣ መሪነትና ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡ ዕድሉን ማመቻቸት፤ የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና አመለካከቶችን ለማየት፣ ገፅታን ለመቀየር፣ ሕዝብን ለመድረስና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከር ያስችላልም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ገብረመድህን፣ እያንዳንዱ ፓርቲዎች ለምርጫው 50 በመቶ ዕጩ ሴቶችን ቢያደርጉ፣ የኅብረሰቡን ግማሽ ያህል የሚወክሉ ሴቶችን ጉዳይ ወደ መድረክ ለማምጣትና ችግር ለመፍታት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶችን ወደ ፖለቲካው መምጣት ፍላጎታቸው መሆኑን፣ ሆኖም እነዚህን በቡድን ማግኘት ከባድ መሆኑን፣ ፖለቲካ ውስጥ መግባት የማይፈልጉ ምሁራን ሊኖሩ እንደሚችሉና ፍላጎቱ ያላቸው ተሰባስበው ቢገኙ ግን ቅንጅቱ ለመደገፍ እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን አስመልክተው የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ ረድኤት ያስቻለው፣ ሴቶች ወደ ፖለቲካውና ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡ መንገዱን ማመቻቸት፣ የዴሞክራሲ መዳበርን ስለሚያሳይና ሴቶች ካሉባቸው የተለያዩ ኃላፊነቶች አንፃር የተለያዩ የሴቶች አመለካከቶችን ለማካተትም ቁልፍ መፍትሔ ስለሚሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩ  ሴቶችን ማምጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ሴቶች ግጭቶች ሲነሱ በሰላም የመፍታት አቅማቸው ከወንዶች የተሻለ መሆኑን በመጠቆምም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት ዕጩዎችን ለምርጫው እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርገዋል፡፡

ሴቶችን ዕጩ አድርጎ ማምጣት የፆታ እኩልነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን መራጭ የማብዛት ጭምር እንደሆነ በመጠቆምም፣ እያንዳንዱ ተፎካካሪ ፓርቲ 50 በመቶ ዕጩዎችን ሴት ቢያደርግ ተጠቃሚ አንደሚሆንም አክለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ 24.3 በመቶ ያህል ሴቶች በፓርላማዎች እንደሚገኙ፣ በኢትዮጵያ ፓርላማ የሴቶች ተሳትፎ ደህና ቢሆንም፣ የሚገኙት ገዥው ፓርቲ ውስጥ ብቻ መሆኑ እንደክፍተት እንደሚታይ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለቀጣዩ ምርጫ ይህንን ያገናዘበ አካሄድ መከተለ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰቡ የተቀየረ አስተሳሰብ፣ ለሴቶች ኮታ እንዲኖር የሚያስችል አሠራርና በፖለቲካ ፓርቲዎች ተጨባጭ ውክልና አለመኖር ሴቶች ወደ ፖለቲካው በብቃት እንዳይገቡ ማድረጉንም ወ/ት ረድኤት ተናግረዋል፡፡

ቅንጅቱ ፓርቲዎች ሴት ዕጩዎቻቸውን ካሳወቁ በኋላ፣ የሴቶችን አቅም ለመገንባት ተከታታይ ሥልጠና የሚሰጥ ሲሆን፣ ሥልጠናውም ከፓርቲ ባለፈም ኅብረተሰቡ ድረስ ዘልቀው ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ሐሳቦችን እንዲያፈልቁ፣ በጉዳዮች ላይ እንዲከራከሩ፣ በፖሊሲዎችና በአሠራሮች ላይ ሐሳቦቻቸውን እንዲሰጡም አቅም የሚፈጥር እንደሚሆን ወ/ሮ ሳባ ተናግረዋል፡፡

ሴቶች ወደ ፓርላማም ሆነ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ ‹‹ብቃት አላት? ትችላለች?›› የሚል የኅብረተሰቡ ‹‹የአትችልም›› አረዳድ መቀየርና ማብቃት አለበት ያሉት ወ/ሮ ሳባ፣ ወንዶች ሥልጣን ላይ ሲመጡ የማይነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ሴቶች ሲመጡ መነሳታቸው አግባብ እንዳልሆነና ይህ ልማድ ሴቶች ወደ ፖለቲካ እንዳይመጡ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

ሴቶች በፖለቲካው ከመቀመጫ ባለፈ የማኅበረሰቡን ችግር ነቅሰው እንዲያወጡ እንደሚፈለግ፣ ‹‹ሴቶች አይችሉም›› የሚለውን የማኅበረሰቡን አመለካከት ለመቀየር እንደሚሠሩም አክለዋል፡፡

የሴት ጥቂት ስህተት ጎልቶ በሚወጣበትና ወንዶች የሚሠሩት የጎላ ስህተት እምብዛም በማይነገርበት ሁኔታ፣ ሴቶችን ወደ ፖለቲካው ማምጣት አደጋች መሆኑን ሆኖም እንደ ድርጅት የነቁና የበቁ ሆኖም በፖለቲካው ያልተሳተፉ ሴቶችን አግኝተው የፖለቲካው ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል ፍላጎታቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ያልጎላው የተማሩ ሴቶች ስለሌሉ ነው? ሴት ወደ ፖለቲካ ለመምጣት ፍላጎት ስለሌላት ነው፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ሴት ስለማይጋብዝ ነው? እና ሌሎችም መጠናት ያለባቸው ቢሆንም፣ እነዚህ እንደ አደናቃፊ ምክንያት ተቆጥረው ሴቶች ከፖለቲካ መራቅ እንደሌለባቸውና፣ እዚሁ ላይ መሥራትና ግንዛቤ መፈጠር እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍለ ማርያም ሙሉጌታ፣ ሴቶችን ወደ ፖለቲካው መሳብ ከባድ እንደሆነና ችግሩ ከቤት እንደሚጀምር ይናገራሉ፡፡

ሚስቶች ከቤት ሲወጡ አይቻልም ብሎ የሚከለክል ባል ባለበት ሁኔታ ሴቶችን ማምጣት ከባድ መሆኑን፣ ፓርቲያቸው በተለይ በሚንቀሳቀስባቸው አርሲና ባሌ እንኳን ሴቶች ፓርቲያቸውን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ፈተና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሴቶችን ወደ ፖለቲካው ለማምጣት ያለው የባህል ተፅዕኖ ከባድ ስለሆነ ተፅዕኖውን ማቃለል እንደሚያስፈልግ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሴቶች የፖለቲካው ፍላጎት ኖሯቸው እንዲወጡ ማስቻል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

‹‹የባህል አብዮት ካመጣን ሴቶች ወደ ፖለቲካው የማይመጡበት ምክንያት የለም›› በማለትም፣ የራሳቸውን ፓርቲ በመጥቀስ ሴቶችን ወደ አመራር እንደማያመጡና ይህም ድክመታቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በፓርቲያቸው ያሉ ሴቶችን ዝቅተኛ የሥልጣን እርከን ላይ እንደሚያስቀምጡ፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስብሰባና ወሳኝ ጉዳይ ሲኖር ስለማይመጡና ስለማይሳተፉ እንደሆነ፣ ሴቶቹ የሚቀሩትም ቤት ውስጥ ካለባቸው ጫና በተጨማሪ የባህል ተፅዕኖው ስላሰራቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሴቶች ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥት ዘልቆ መግባት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

ስለብቃት ሲነሳ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ በየፓርቲው ያሉት ወንዶችስ ብቁ ናቸው ወይ? ብሎ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ፣ ብቃትና ችሎታ እየተባለ ሴቶችን ለማራቅ የሚቀርቡ ቅድመ ማሰናከያዎች አግባብ እንዳልሆኑም በመድረኩ ተነስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...