ሰላም! ሰላም! አንዳንዴ እኮ ምን ሰላም አለ ያሰኛል፡፡ እሳት በጉያቸው ታቅፈው የሚዞሩ መሰሪዎች እያሉ የምን ሰላም ነው ቢባል ምን ይገርማል? ለማንኛውም አንዱ ነው አሉ፡፡ አንዱ ስላችሁ ደግሞ ይኼ ኮምፒውተር ላይ ያለው ማለቴ አይደለም፡፡ እሱንማ መሆን ብንችል በምን ዕድላችን? የኑሮ ሩጫችንን አቋርጠን ኑሮን ራሱ አንዱ እያደረግን አንዘፍንም ነበር? ‹እሱም አውቆ ሰማይን አርቆ› ሆነና ነገሩ ሰው ሕይወቱን አንዱ ማለት ቢያቅተው በአምሳሉ ሮቦት ፈጠረ፡፡ ይኼም እንደ አንዱ ከተቆጠረ ቁጠሩት፡፡ ግን አንዱ ይቆጠራል እንዴ? ለጨዋታው ድምቀት ነው የምጠይቃችሁ፡፡ በጣም ከማዳመቄ በፊት ግን ስለዚያ አንዱ ስላልኳችሁ መከረኛ ልንገራችሁ፡፡ ዓይኔን ጋረደኝ ብሎ ሆስፒታል ይሄድላችኋል፡፡ ቅድመ ምርመራ አስፈላጊ በሆነበት ዘመን ጉዳችንን ማንኛው ሐኪም በነገረን፡፡ የምሬን ነው፡፡ እናም አጅሬ ሲመረመር በደምህ ውስጥ ብዙ ስኳር ተገኝቷል አለው ሐኪሙ፡፡ ሰውዬው እየተወናጨፈ ቀወጠው፡፡ ሐኪሙ ስለስኳር በሽታ ያለው ግንዛቤ መስሎት እንዲያ ያደረገው ዘና አለ፡፡ ከዚያ አንዱ ምን ቢለው ጥሩ ነው? ‹‹ዶክተር ስንት ኪሎ ነው?›› አይለው መሰላችሁ?
እኔ ግን ከኪሎው ጥያቄ የተመቸኝ ታሪኩን ሲነግሩኝ አንዱ ብለው መጥራታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ቅድም ስላችሁ እንደ ነበረው ሕይወትን እንደ ኮምፒዩተር ምትኃት ወደ ኋላ ክሊክ ማድረግ ቢቻል የስኳር እጥረት፣ የውኃ ድርቀት፣ የቤት እጥረትና የአየር ንብረት ምን ቅጡ ባለበት ተመለሰ ማለት እኮ ነው፡፡ ዋ ነገር ሁሉ በነበር ቀረ እኮ ጎበዝ፡፡ ይኼን ብዬ ያማረልኝ መስሎኝ ለባሻዬ ልጅ አጫወትኩት፡፡ በአንዴ አመድ መስሎ ዙሪያ ገባውን ካየ በኋላ፣ ‹‹እንዴት እንዲህ ትላለህ? ጤና፣ ስኳር፣ ውኃ፣ መሬት፣ አየር በነበረት ቢመለስ ባለበት የማይመለስ እኮ በዙ አለ፤›› አለኝ፡፡ ‹‹ምንድነው?›› ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? በሁለት አኃዝ ይምዘገዘጋል ተብሎ በሚወራለት አረፋው ኢኮኖሚያችን ጀምሮ፣ ሰርቆ የከበረን አነሳስቶ በመንገድ መሠረተ ልማት አድርጎ የከተማ ባቡራችንን ተሳልሞ ብዙ ብዙ ጠራልኝ፡፡ ‹‹በቃ አሁን የተናገርኩትን አንዱ በለው፤›› ብዬ ፈትለክ አልኩኝ። ይሞታል እንዴ!
ነገርን ነገር ያነሳዋል፡፡ ያጣነው እንደ ስኳር የሚጣፍጥ እንጂ የሚመርስ አላጣንም፡፡ ያውስ ለጨዋታ? ይብላኝ ለእነ ለዛ ሙጥጥ፡፡ ነገረኛ ሆንኩ እንዴ? ለነገረኛም ነገረኛ ያዝለታል፡፡ አላዝልን ብሎ የተቸገርነው በበሽታችን ልክ መድኃኒት ብቻ ነው፡፡ ‹‹በሽተኛው በዛ መድኃኒት አነሰ. . .›› ያለው ዘፋኙ ወዶ መሰላችሁ? ‘ማንም የወደደውን ያገባና የዘፈነ የለም’ እንዳትሉኝና እንዳልስቅ፡፡ ውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ሰሞኑን በገባች በወጣች ቁጥር፣ ‹‹ዱባይና ታይላንድ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁት. . . ›› እያለች ትሞዝቅላችኋለች፡፡ እኔ ደግሞ ‘መልዕክት ይኖረው ይሆን? ሽርሽር አማረኝ እያለችኝ ይሆን?’ እያልኩ መጨነቅ፡፡ አሥር ጊዜ የባንክ ደብተሬ ወጪና ገቢ ላይ ማፍጠጥ፡፡ ስቀንስ ስደምር፣ የሆቴል መኝታ፣ የምግብና የትራንስፖርት ሳባዛ ሳካፍል መዋል፡፡ ግን ለምንድነው ዘንድሮ ለሽርሽር መጓዝ ሲታሰብ ገና ድካም የሚተርፈን? የኢኮኖሚው ዕድገት ማሳያ ይሆን እንዴ? ቢጨንቀኝ እኮ ነው የምጠይቃችሁ። ለነገሩ እሳት የተሸከሙ ጉዶች በበዙበት በዚህ ጊዜ በእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ጨነቀኝ ማለት አጉል ቅንጦት ነው፡፡
በኋላ ታዲያ አስቤ አስቤ ሲደክመኝ የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ምን አባቴ ባደርግ ይሻለኛል?›› ብዬ ማማከር። ምን ይለኛል፣ ‹‹ቆይ ትንሽ ታገስ ማንጠግቦሽ ብቻ አይደለችም ዱባይና ታይላንድ እያለች የምትዘፍነው፣ ሁሉም ነው፤›› አለኝ፡፡ ‹‹እንዴት ሁሉም?›› ስለው፣ ‹‹በቃ ነዳጅ ልናወጣ ነው መሰለኝ፣ ሁሉም ሰው መካከለኛ ባለ ገቢ ይመስል የጉዞ ፕላን ያወጣል፤›› ሲለኝ፣ ‹‹ታዲያ ምነው እንዲህ ያለውን የምሥራች ቀደም አድርገህ ሳትነግረኝ?›› ስለው፣ ‹‹ምን ይታወቃል? ‘የህዳሴው ግድብ ሳይጠናቀቅ በድሎት መሞላቀቅ ጥሩ ነው ወይ?’ የሚል መልስ ከመጣ ብዬ ነዋ፤›› አይለኝ መሰላችሁ። ጉድ እኮ ነው እናንተ! ‹‹ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ›› አለች አሉ፡፡ ‹‹እኔ እኮ የከበሩ ማዕድናትና ዩራኒየም ያወጣን መስሎኝ ነው አዳሜ ለዱባይና ለታይላንድ ሽርሽር ሐዋሳ ላንጋኖን ገልብጦ የሚጫወት የመሰለኝ፤›› ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹ተው እንጂ በማለም በመብታችንማ አትምጣ፤›› ብሎ ተቆጣኝ፡፡ ኧረ እንዴት ነው ነገሩ ይኼ ዓለም እያደር የህልም ዓለም ሆነ እኮ ጎበዝ! ባለፀግነትን ተመኝተው የነገዋን ሸጋ ዓለም የሚመኙ የዋሆች ባሉባት አገር፣ እሳት ተሸክመው የሚዞሩ መሰሪዎች መብዛታቸው ደግሞ እርር ድብን ያደርጋል፡፡ የሚያሳርር ያድብናቸውና!
ይልቅ ባለፈው ሰሞን ምን ሆነ መሰላችሁ? እስኪ ደግሞ ስለሥራና አሳሩ ላጫውታችሁ፡፡ ጥጋብና ልክ የለሽነት የዘመናችን መታወቂያ ጉድ ሆኗል መቼም፡፡ እና ከደንበኞቼ ጋር ተደዋውዬ፣ ሚሊዮንን እንደ ሽልንግ ወደ አቃለለው ቤት ሸመጠጥኩ፡፡ ስደርስ ገዥና ሻጭ ‘ባንኮኒው’ ላይ ‘ብሉ ሌብል’ ቺርስ እየተባባሉ ደረስኩ፡፡ ያሻሻጥኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ሰዓቴን ሳየው ገና ማንጠግቦሽ ቡና አላቀራረበችም፡፡ እንዳልቀደም ላቤ በጀርባዬ እየተንቆረቆረ ያገናኘኋቸው ደንበኞቼ በሞቀ ፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡ ቢሸጥ ኮንቴይነር ሙሉ ሰልባጅ ገዝቶ የሠፈሬን ነዋሪ በሚያንበሸብሽ ውድ ብርጭቆ ከሚጠጡት ውድ ውስኪ ቀድተውልኝ ‘ቺርስ’ አሉኝ፡፡ ‘ግዴለም ይቅርብኝ’ ብል የ‘ኮሚሽኔ’ ነገር አሳሰበኝ፡፡ ስለዚህ ባዶውን እየጮኸ አሲድ በሚተፋ አንጀቴ ላይ አሲድ ቸለስኩበት፡፡ መስማማታቸውን ባልጠራጠርም ለማረጋገጥ ስለፈለግኩ፣ ‹‹እንዴት ነው ታዲያ?›› እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ እነሱ የእኔ ተራ ወሬ አልጣማቸውም መሰል የያዙትን ወግ ቀጠሉ፡፡ ለነገሩ ደላላ ሲያታልል እንጂ በጨዋነት ማን ያውቀዋል? ቢታወቅም ቅሉ አዳማጭ የሚኖረው አፍ የሚያስከፍት የዝርፊያ ወሬ ሲዘረግፍ ነው፡፡ ያኔ አዳሜ ልቡ ቆሞ ያዳምጣል ብቻ ሳይሆን፣ ሁለመናው ጆሮ ሆኖ ያግበሰብሳል፡፡ ወሬኛ ሁሉ!
አንዴ ወልዳ እንድትመጣ ወደ አሜሪካ ስላሳፈሩዋት ሚስታቸው (ወደ አሜሪካ ሲሉ አሁን እዚህ ጉለሌ እዚህ መካኒሳ እንጂ አትላንቲክን አቋርጠው የሚደርሱበት አኅጉርና አገር የሚጠሩ ይመስላል እናንተ?)፣ አንድ ዓመት ሳያሽከረክሯት ስላልተመቻቸው ዘመናዊ አውቶሞቢልና ሊቀይሩት ስላሰቡት የቅርብ ጊዜ ሞዴል አዲስ መኪና በሰፊው ይጫወታሉ፡፡ ከተጠመቀ ቆየት ካለ ውስኪያቸው እየማጉ ከቁብ አልቆጠሩኝም፡፡ ‘ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በአሥር ዓመት አንዴ ከቆጠረህ አይበቃህም?’ ይመስላል ሁኔታቸው፡፡ ነገሩን ላሳጥረውና (እንኳን አንዛዝተነው እንዲሁም አልቻልነው) አንደኛው ‘ቼክ’ አውጥቶ ፈረመና ‘ኮሚሽኔን’ ከባንክ እንድወስድ ሰጠኝ፡፡ ‘በቼክ’ መቀበሌን አደራ ለማንም አልተናገርኩም፣ እናንተም ለማንም አታውሩ፡፡ ደግሞ በኋላ ‹‹አንበርብር በ‘ቼክ’ ነው የሚጫወተው፤›› ብሎ አንዱ ማጅራቴን ቢያስመታኝ ማን አለኝ? ትቀልዳላችሁ እንዴ! ነው ወይስ ውዷ ማንጠግቦሽ ‘አንበርብር ቢሞትም ‘ቼኩ’ አይሞትም’ በሚለው ትፅናናለች ብላችሁ ታስባላችሁ? ኧረ እንዴት ተቀለደ ወገኖቼ፡፡ እኔማ እዚህ ምድር የመጣሁት ሌሎችን ላኗኑር እየመሰለኝ ስበሽቅ ነው የምውለው፡፡ ምን ዓይነቱ ሞኝ ነኝ!
ከፅንፍ ፅንፍ ስወስዳችሁ ደግሞ በቀደም ከአንድ ክልስ ወዳጄ ጋር ወደ ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ጉዳይ ገጥሞን መጓዝ ጀመርን፡፡ ዕድሜ ለጊዜያችን እንጂ መንገድ ባይኖር እግርን አለማየት ነበር፡፡ ይኼን የምላችሁ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ቁሙ ሲለን እኔ የማየው እግር እግሩን ነበር፡፡ ጫማው የወታደር ነው፡፡ የለበሰው መለዮ የትራፊክ ፖሊስ ነው፡፡ ተጠራጠርኩ፡፡ የወታደር ጫማ ደግሞ ይለያል እንዴ? የሚል ካለ የኢሕአዴግ ልጅ ቢሆን ነው በሚል ዝለሉት፡፡ ታግሎ ትግልን ያስረሳን በመፈረካከስ ላይ ያለው ገዥው ፓርቲያችን እስካለ ድረስ ገና መለዮም የማያውቅ ትውልድ ሊነሳ ይችላል፡፡ እና ምን እያልኳችሁ ነበር? አዎ አቀርቅሬ ጫማ ጫማውን ሳይ፣ ‹‹ይኼ ፈረንጅ የየት አገር ሰው ነው?›› አለኝ ክልሱን ጓደኛዬን። ‹‹ኧረ እዚሁ ነኝ፣ ተወልጄ ያደኩት እዚሁ ነው፤›› አለው ወዳጄ በጠራ አማርኛ፡፡ ‹‹ታዲያ ከመጀመርያው እንደ እሱ አትልም?›› ሲል እርስ በርስ ተያየን፡፡ ታዲያ ምን ይባላል? ሰውየው ምን ነክቶት ነው እንዳልል ጤነኛ ይመስላል፡፡ ጤነኛ ነው እንዳልል አነጋገሩ ይገርማል፡፡ ለነገሩ 27 በመቶ ወፈፍ ያደርገዋል በሚባልበት አገር ውስጥ ካልተመረመርን ማን ወፈፌ ማን ጤነኛ መሆኑን መለየት አይቻልም፡፡ እውነቱ ይኼ ነው በቃ!
‹‹እኔ የምላችሁ ውጭ አገር የሚልክ ሰው ታውቃላችሁ? ወይ እናንተ ትልካላችሁ?›› አለን እንደ ዋዛ፡፡ የመንጃ ፈቃዱን መዳፉ ላይ እንደ ካርታ እየገለባበጠ ይጫወትበታል፡፡ እኔና ኢትዮ ፈረንጁ ወዳጄ ደንግጠን ተያየን፡፡ ሁኔታችንን ዓይቶ፣ ‹‹ሲያዩዋችሁ የአዲስ አበባ ልጆች ነው የምትመስሉት፡፡ ምን ታካብዳላችሁ? እኔ የትራፊክ ፖሊስ አይደለሁም፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ነኝ፡፡ ግን እዚህ መድበውኝ ነው፡፡ በጊዜያዊነት እየሠራሁ ነው እንጂ መደበኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ሥራ ላይ እያለሁ በጉልበተኞች ሁለቴ ተፈንክቻለሁ፡፡ ይኼው እዩት፡፡ እናም እዚህ አገር መኖር መሮኛል፡፡ ለማንኛውም ስልኬን እንኩ፤›› ብሎ ስልኩን ሰጠን፡፡ የመንጃ ፈቃዳችንን መለሰ፡፡ ሚሊሻው ለቁስል ማድረቂያ ብሎ ሁለት መቶ ብር ፈለጠንና ሂዱ ብሎ መንገዱን ለቀቀ፡፡ አሁንም በስፖኪዩ ምን ታያለህ ብትሉኝ? ያን የወታደር ጫማ፡፡ ለነገሩ ፀጥታ አስከባሪ ለመምሰል ሬንጀርና የወታደር ቡትስ እያደረጉ ስንት ወንጀል ፈጻሚዎች እንዳሉ ልብ ይባል፡፡ እሳት ተሸካሚዎችም እንዲሁ!
እንሰነባበት። እንደ ፈጠጥኩ ጉዳያችንን ጨርሰን ተመለስን፡፡ እኔና ወዳጄ መነጋገር ያቆምነው ያ የወታደር ጫማ ያጠለቀ የትራፊክ ፖሊስ መሰል ሰውዬ ባህር ማዶ የሚያሻግር ሰው ፈልጉልኝ ካለ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ እንዴት አንቆለፍ? እኔን ያሳሰበኝ ሰፊው መንገድ ነው፡፡ ‹‹ይህ የአንድ ሰው የሁለት ሰው ድምፅ አይደለም እኮ?›› ብዬ ለአዛውንቱ ባሻዬ ስነግራቸው፣ ‹‹እሱስ ልክ ነህ፣ ግን ምን ማድረግ ትችላለህ? ይኼንን ለፈጣሪ መተው ነው፡፡ ይህች አገር እንደሆነች ድሮም በእሱ ጥበብ እንጂ በማን ቀንድና ቀለም ተመርታ ታውቃለች?›› ብለው አሸሞሩ፡፡ ባሻዬ የገባኝ ገብቷቸዋል፡፡ ያሳሰበኝ አሳስቧቸዋል፡፡ ምንም ቢሆን ትልቅ ሰው ናቸዋ፡፡ ትልቅ ሰው ደግሞ በዕድሜ ብዛት ያካበተው ልምድ ብዙ ያስታውሰዋል፡፡ ትልቅ ሰው የነገርን አካሄድ በቀላሉ ስለሚገነዘብ እንደ ዘመኑ ሰው ገለባ አይሆንም፡፡ ገለባ በቀላሉ ለእሳት የሚዳርግ ደካማ ነገር በመሆኑ ነው መሰሪዎች የሚጠቀሙበት፡፡ ‹‹ተረቱም እኮ እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው ነው የሚለው፤›› ያሉኝ ባሻዬ ናቸው፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ ቅኔው!
ወዲያው ከእሳቸው ጋር ስለያይ ደግሞ ምሁሩ ልጃቸው ደወለና አንድ አንድ እንበል አለኝ፡፡ እኔም ጊዜ አላጠፋሁ የኮምፓሴን አቅጣጫ በቀጥታ ወደ ግሮሰሪ አደረግኩ፡፡ ስደርስ የባሻዬ ልጅ ያላበው ቢራ አስቀድቶ በአንድ ትንፋሽ እያንደቀደቀ ነበር፡፡ አጠጣጡ እኔንም አበረታታኝ መሰለኝ የቀረበልኝን አንደቀደቅኩት፡፡ ግሮሰሪው በደንበኞች ተሞልቶ ሁሉም ከቢጤያቸው ጋር ወግ ይሰልቃሉ፡፡ እኔና የባሻዬ ልጅ ወጋችንን ስቀጥል፣ ‹‹ፖለቲካችን ዳዴ ማለት አቅቶት በየቦታው እሳት እየተለኮሰ የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ ጥረት ሲደረግ ያበሳጫል. . .›› ብሎኝ ድንገት ቀና ብሎ ሲያየኝ ፊቴ ጭጋግ ለበሰ፡፡ አላውጣው ብዬ እንጂ የዚህ የእሳት ጉዳይ በጣም እያበሳጨኝ ነበር፡፡ እሳት ተሸክመው የሚዞሩ መሰሪዎች ዙሪያችንን ከበውን ዝም እያልን ነው፡፡ አስተዳዳሪው፣ ዳኛው፣ ፖሊሱ፣ ሕዝቡ ጭምር በሚገባ እንደሚያውቁ ግን ዝምታው መብዛቱ አናደደኝ፡፡ መሰሪን ዝም ማለት ጥሩ አለመሆኑ እየታወቀ ዝምታ ይገድለናል እንጂ የትም አያደርሰንም፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ቀልደኛ ደላላ ወዳጃችን አንዱ በጠራራ ፀሐይ ከበድ ያለ ጥቁር የቆዳ ጃኬት እስከ አንገቱ ቆልፎ፣ እሱ አልበቃ ብሎት ሲጋራውን ለኩሶ በረጅሙ እየማገ ሲሄድ ያገኘዋል፡፡ ቀልደኛው ወዳጃችን ገርሞት እያየው፣ ‹‹ሰማህ በዚህ ጠራራ እሳት ለብሰህ እሳት ጎርሰህ ወዴት ነው?›› ሲለው፣ ‹‹ካለልኝ ወደ ገነት ካልሆነልኝ ወደ ሲኦል፤›› አለው ተብሎ ነበር፡፡ የአገር ጠላት መሰሪዎችን እሳት እንደ ለበሱና እንደ ጎረሱ ልክ ማስገባት አይገባም? መልካም ሰንበት!