ለወራት ተቋርጦ የነበረው ለሥራ ወደ ዓረብ አገሮች የሚደረገው ጉዞ ዳግም እንዲጀመር ከተደረገ ሰነባብቷል፡፡ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየውም፣ እስካሁን ከ8,000 የሚበልጡ ዜጎች ወደ ዓረብ አገሮች ሄደዋል፡፡ ሕጋዊው መንገድ ተከፍቶ ጉዞ ቢቀናም በሕገወጥ መንገድ የሚደረገው ጉዞ ግን እንዳለ ነው፡፡
በሕገወጥ መንገድ የሚደረገው ጉዞ በድብቅ የሚከናወን በመሆኑ በየጊዜው ምን ያህል ሰዎች እንደሚወጡ በውል የተረጋገጠ ነገር ባይኖረውም በሕጋዊ ከሚወጡት የላቀ ቁጥር እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ሕገወጥ ስደተኞች የተለያዩ መውጫ በሮችን፣ አሳቻ መንገዶችና ዘዴዎችን ስለሚጠቀሙ ለቁጥጥር አዳጋች ነው፡፡ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በአንደኛው መውጫ መስመር ብቻ በየቀኑ 100 ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን እንደሚገቡ ያሳያል፡፡ አንደኛው መውጫ በሆነው የደቡብ መስመር የሚጓዙ በሞያሌ ወጥተው ኬንያን አቋርጠው የታንዛንያ፣ ማላዊና ሞዛምቢክ ድንበርን ተሻግረው ደቡብ አፍሪካ ይገባሉ፡፡
ይህንን መስመር በግርድፉ እስከ 20 ሺሕ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንና የሶማሊያ ዜጎች በየዓመቱ እንደሚያቋርጡት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በምሥራቅ መውጫ በሮችም ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ጂቡቲን፣ ፑንትላንድን አቋርጠው የመን ከዚያም ሳዑዲ ዓረቢያ ይገባሉ፡፡ በሰሜን መውጫ በሮች አድርገው ወደ እስራኤልና ሌሎች አገሮች የሚገቡም ጥቂት አይባሉም፡፡
በእነዚህ መውጫ በሮች በየቀኑ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን እንደሚወጡ መላምትን ተንተርሰው ከሚወጡ አኃዞች ውጪ በትክክል የሚታወቅ በጥናት የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ በሕጋዊ ከሚወጡት የበለጠ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ሕገወጡን መስመር እንደሚያዘወትሩ ግን የማኅበራዊና ሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡
አደገኛውንና አታካቹን ሕገወጥ ስደት የሚቀላቀሉ ዜጎች ላይ ስለሚደርሰው ዘርፈ ብዙ ጥቃት ብዙ ተብሏል፡፡ ዜጎችን በሚነግዱ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይም የተለያዩ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም መንገዱ አልተዘጋም፡፡ ከላይ እስከ ታች የተዘረጋው ጠንካራ ሰንሰለትም በቀላሉ የሚበጠስ አልሆነም፡፡ በሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ እጀ ረዥም ደላሎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በመተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችም በእጅ አዙር የጥቅም ተጋሪ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች መፈጠራቸው ደግሞ ጉዳዩን ውስብስብ አድርጎታል፡፡ በሕገወጥ ስደተኞች የሚዘወተሩ ቦታዎችን መርጠው በሶ እና ውኃ የሚሸጡ ነጋዴዎች የተጠሙና የተራቡ ዜጎችን ዱካ እየተከተሉ ኪሳቸውን መሙላት ሥራዬ ብለዋል፡፡ በእነዚህ መስመሮች አንድ ሊትር ውኃ ከመሸጫ ዋጋው በአራት እጥፍ በልጦ እንደሚሸጥ መዘገባችንም ይታወሳል፡፡
የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቀው ይህ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መረብን መበጠስ ይበልጡን እየከበደ የመጣ ይመስላል፡፡ በስደተኞች ላይ እየደረሱ የሚገኙት ለጆሮ የሚከብዱ ጥቃቶችና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች የተለመዱ፣ ተራ ድርጊት እስኪመስሉ እንደቀላል እስከመታየት ደርሰዋል፡፡ ስደተኞች ጥቃት ማስተናገድ የሚጀምሩ ገና ከአገራቸው ሳይወጡ አንድ ብለው ጉዞ ከጀመሩበት ዕለት ሊሆን ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለቅኝ ግዛት እጅ ያልሰጡ ኢትዮጵያውያን ሠፈር ውስጥ በሚያውደለድሉ ደላሎች አማካይነት ለባርነት እየተሸጡ ስለመሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
ኑሮ የገፋቸውና ገንዘብ እንዳላቸው የሚጠረጠሩ ዒላማ ውስጥ ቀድመው ይገባሉ፡፡ ገንዘብ የሌላቸው ለባርነት ሲሸጡ፣ አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ከፍለው እንዲያስለቅቋቸው አሊያም በሕይወት እንደማያገኟቸው ይነገራቸዋል፡፡ ይህም አዲስ ያይደለ ብዙዎች የሚያውቁት ሀቅ ነው፡፡ ሆድ ዕቃቸው ተከፍቶ ኩላሊታቸውን የተነጠቁ ኢትዮጵያውያን ዕንባም ብዙዎችን አስለቅሷል፡፡ ያለደመወዝ ለዘመናት በነፃ እንዲያገለግሉ የተፈረደባቸው ሴቶች ፍዳም የሚታወቅ ነው፡፡
በሴቶች ስደተኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ገና ከመነሻው የሚጀምር መሆኑን የሚያሳይ አንድ ጥናት፣ በሴት ስደተኞች ላይ የሚደርሰው የፆታ ጥቃት በየቦታው የተለያየ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከ100 ስደተኛ ሴቶች መካከል በአሥሩ ላይ ፆታዊ ጥቃት የሚደርሰው ገና ቀዬአቸውን ከመልቀቃቸው ጀምሮ ነው፡፡ በጉዞ ወቅትም ከ100 ሴቶች መካከል 35ቱ ፆታዊ ጥቃት ያስተናግዳሉ፡፡ ከ100 ሴቶች መካከል 58ቱ በመዳረሻ ቦታዎች ላይ ጥቃቱ ይፈጸምባቸዋል፡፡ 19ኙ ደግሞ በማቆያ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች ይደርሱባቸዋል፡፡
“Sexual Violence at Each Stage of Human Trafficking Cycle and Associated Factors” በሚል የተሠራው ጥናት በግምት በየዓመቱ ከ600,000 እስከ 800,000 ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ መንገድ ድንበር እንደሚያቋርጡ ያሳያል፡፡ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ታዳጊ ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ በሕገወጥ መንገድ ድንበር የሚያቋርጡ ዜጎች ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለወሲብ ባርነትና ለአካል ንግድ እንደሚጋለጡ ያሳያል፡፡
ከ14 እስከ 49 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚያስገባቸውን አንዱን መውጫ መስመር ይዘው ይተማሉ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ በአጠቃላይ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ፆታዊ ጥቃትን እንደሚያስተናግዱና ለተለያዩ ችግሮች እንደሚጋለጡ ያሳያል፡፡ አብዛኞቹም ያልተፈለገ እርግዝና እንዲሁም በአባለዘር ለሚተላለፉ በሽታዎች ሲያደርጉ፣ ጥቂት የማይባሉ በተለይ በተደጋጋሚ ጊዜ በቡድን የተደፈሩ ከባድ አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ አዕምሯቸውን የሳቱና እስከ ሞት የደረሱ ሴቶች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
እንዲህም ሆኖ በሕጋዊ መንገድ ከሚወጡ ዜጎች የላቀ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በአዘዋዋሪዎች መሪነት የተለያዩ አገሮች ድንበርን ማቋረጣቸውን ቀጥለዋል፡፡ በጦርነት የታመሱ፣ መንግሥት የሌላቸው እንደ የመን ያሉ አገሮችን ሳይቀር ይደፍራሉ፡፡ ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው ሲንቀሳቀሱ የተያዙም በየአገሩ በሚገኙ እስር ቤቶች ይማቅቃሉ፡፡ ግፍ በሚፈጸምባቸው የአፈና ቤቶች የሚሰቃዩም ብዙ ናቸው፡፡ የትና በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረጃ ባለመኖሩ ድጋፍ ለማድረግ ለመንግሥት አስቸጋሪ እንደሆነ፣ ቁጥራቸው በውል አለመታወቁም ችግሩን ማባባሱን ተያይዞታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሕይወት መኖራቸው ያልተረጋገጠ ኢትዮጵያውያን ብዙ ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን ከአፈና ለማስለቀቅ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ገንዘብ የሚጠየቁ ወላጆችም የመንግሥት ያለህ ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ሰቀቀን ጀርባ ሆነው የሚያተርፉ ደላሎችም የተለያዩ ማባበያ ዘዴዎችን ተጠቅመው ከሕግ በላይ ሆነው በሰው መነገዳቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 18፣ በማንኛውም መንገድ በሰው መነገድን ይከለክላል፡፡ በሴቶችና ሕፃናት መነገድን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት፣ ሰውን በሕገወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህር፣ በአየር ማስወጣትና ማስገባትን ለመከላከል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጡ ፕሮቶኮሎችንም ኢትዮጵያ ተቀብላ አፅድቃለች፡፡
መንግሥት ደግሞ ሰዎች በተፈጥሮና በሕግ የተጎናፀፉትን መብትና ጥቅም የማክበር፣ የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በመሆኑም ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ይሠራል፡፡ ወንጀል ፈጻሚዎችን በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
በዚህ መሠረትም ወንጀል ፈጻሚዎች የሚቀጡበትን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል የተመለከተውን አዋጅ ቁጥር 909/2007 በሥራ ላይ አውሏል፡፡ አዋጁ በሚደነግገው መሠረትም እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2016፣ ከ2,000 የሚበልጡ ግለሰቦች ተከሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን አከርካሪ ለመምታት መንግሥት የተለያዩ ዘዴዎችን በሥራ ላይ እያዋለ ይገኛል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ግብረ ኃይል ተደራጅቶም ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
በየጊዜው በተሠሩ የዘመቻ ሥራዎች ከጀርባ ሆነው ይህንን ሕገወጥ እንቅስቃሴ የሚዘውሩ ግለሰቦች ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ ወንጀሉን ከመከላከል አንፃር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ጥፋተኞች በሕግ የሚዳኙበትን ሕግ ከማስተካከል አኳያም በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ቁጥር 909/2007 ለመቀየር አዲስ ረቂቅ ተዘጋጅቷል፡፡ ግልጽነት ይጎለዋል፣ ከሌሎች ሕጎች ጋር የማይጣጣም፣ ለችግሩ በቂ ምላሽ የማይሰጥ የተባለውን አዋጅ እንደሚሽር የሚጠበቀው ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል፡፡
እስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት የተካተተበት ረቂቁ የተጎጂዎች ጥበቃና መልሶ ማቋቋምን የተመለከቱ ድንጋጌዎችንም ይዟል፡፡ ‹‹በሰው የመነገድና ሰውን በሕገወጥ ድንበር የማሻገር›› ወንጀልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ፣ ሰውን በባርነት ወይም በባርነት መሰል ተግባር፣ በአገልጋይነት የተጠቀመ፣ እንደ መያዣነት የያዘ፣ አካል ያወጣ፣ በዝሙት አዳሪነት ያሰማራ፣ የወሲብ ብዝበዛ የፈጸመ፣ በግዳጅ ሥራ፣ በልመና፣ በወንጀል ተግባርና የመሳሰሉትን ተግባራት የፈጸመ ከሰባት እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ፣ ከ20,000 እስከ 100,000 ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበት ይገልጻል፡፡
በተጎጂ ላይ የደረሰው እንግልት ሞትን አስከትሎ እንደሆነም ከ15 እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት፣ ወይም የዕድሜ ልክ እስራት እንዲጣልበት ሲያልፍም በሞት እንዲቀጣ ይሆናል፡፡ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና የማስረፅ ዳይሬክተር አቶ በላይ ይርጋ፣ የሞት ቅጣት በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ የነበረ መሆኑን፣ ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ አንድ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ወንጀለኛ ፍርዱ ሳይፈጸም ሁለት ዓመታት ካለፈው ቅጣቱ ወደ ዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀየርለት የሚል አቋም መያዙንም አስረድተዋል፡፡ የቅጣቶች ሁሉ መጨረሻ የሆነው የሞት ፍርድ እስከ ታች ለተዘረጋው የወንጀለኞች ሰንሰለት ልጓም እንደሚሆን የብዙዎች እምነት ነው፡፡