Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ-ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክት ላይ የተካሄደ ጥናት የኃይልና የፋይናንስን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች አገልግሎቱን እንዳስተጓጎሉት ይፋ አደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክት በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳይሆን የሕግ ማዕቀፍ ችግሮችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የጥገና አገልግሎትና የመለዋወጫ ችግሮች፣ እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት ዕጦት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን እንዳስተጓጎሉት በአገር በቀል አማካሪ ድርጅት የተካሄደ ጥናት ይፋ አደረገ፡፡

ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ ኢንተርናሽናል ኮንሰልት የተሰኘው አገር በቀል አማካሪ ድርጅት ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት፣ በአዲስ አበባና በጂቡቲ የባቡር መስመር ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ48 ሺሕ ሰዓታት ያላነሰ ጊዜ ወይም በአንድ ዓመት ውስጥ ከ131 ቀናት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሲያጋጥመው መቆየቱ በጥናቱ ታውቋል፡፡ የአማካሪ ድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌዲዮን ገሞራ ጃለታ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ይህንን ችግር ጨምሮ የሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶችና ባቡሩ በሚጓዝባቸው መስመሮች የሚያጋጥሙ አደጋዎች የባቡር ትራንስፖርቱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እያወኩት ነው፡፡

እስካለፈው ጥቅምት ወር የተመዘገቡ 573 አደጋዎች እንደተከሰቱ ጥናቱ አመላክቶ፣ በሚያዝያ ወር 2012 ዓ.ም. በምሥራቅ ሸዋ ዞን ያጋጠመው ከባድ አደጋ ዋናው ተጠቃሽ እንደነበር አስታውሷል፡፡ 53 ተጎታች ፉርጎዎች የነበሩት ባቡር የደረሰበት አደጋ ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት እንደደረሰበት፣ በዚህ ሳቢያም ለበርካታ ቀናት የባቡር መስመሩ ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆኖ ለመቆየት መገደዱን ጠቅሷል፡፡ በየጊዜው የእንስሳት ግጭት የሚደርስበት የባቡር መስመሩ፣ በተደጋጋሚ በሚያጋጥመው የኤሌክሪክ ኃይል መቋረጥ ሳቢያም ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች እየተሰረቁ እንደሚወሰዱበት፣ ይህም ተጨማሪ ወጪዎችንና መስተጓጎሎችን እያስከተለበት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በጥቅምት ወር ብቻ ከ6,742 ጊዜ በላይ የኃይል መቋረጥ እንዳጋጠመም ተመልክቷል፡፡ የኃይል መቋረጥ በሚያጋጥመበት ወቅት ከ60 በመቶ በላይ ለሦስት ሰዓታት እንደሚቆይ፣ ሦስት በመቶ የሚገመቱና ቀላል የሚባሉት አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ቀን በላይ መልሰው ሳይስተካከሉ እንደሚቆዩ ጥናቱ አሳይቷል፡፡

በጥገና ረገድም የባቡር ኦፕሬሽኑን ፈተና ውስጥ የጣሉ የጥገናና የመለዋወጫ ችግሮች በሰፊው እንደሚታዩ ተጠቁሞ፣ በተለይም መሠረታዊ ችግሮች እያጋጠማቸው እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡ ስምንት በኤሌክትሪክ ከሚሠሩ 35 የሎኮሞቲቮች ክፍሎች ውስጥ 23 ክፍሎች መሠረታዊ ችግር እንደሚታይባቸው፣ ስድስት ክፍሎች ካሏቸው ሁለት የናፍጣ ሎኮሞቲቮች 34 በመቶው ችግር እንዳጋጠሟቸው፣ አራት የመንገደኞች ፉርጎዎች ካሏቸው 30 ክፍሎች ውስጥ 14 በመቶ ያህሉም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ ከ502 ያላነሱ የጭነት ባቡር ክፍሎች ውስጥ አብዛኞቹ እክል ሲታይባቸው የኩሽኔታ ዘይት ማንጠባጠብ፣ በፍሬን አካባቢ የአየር ማስረግና የመሳሰሉት የቴክኒክ ችግሮች የባቡሩን የደኅንነት ደረጃ ጥያቄ ውስጥ እንደሚጥሉት ከጥናቱ ውጤቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡

እንዲህ ያሉትን ችግሮች ቀርፎ የባቡሩን ጤንነት የሚያረጋግጥ፣ ዘላቄታዊነቱንና ቀጣይነቱን የሚያስጠብቅ የፋይናንስ አቅርቦት ለማግኘት አለመቻሉም፣ የባቡሩን ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ከጣሉት መካከል ተካቷል፡፡ ከቻይና መንግሥት በተገኘ ብድር ከአምስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክት፣ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ብሎም በቻይናና በኢትዮጵያ መንግሥታት በኩል ተጨማሪ ትብብሮችንና ስምምነቶችን በመፈጸም የባቡር መስመሩን ህልውና ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አቶ ጌዲዮን አሳስበዋል፡፡

ከሁለት ዓመታት ባነሰ የአገልግሎት ቆይታው የአዲስ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ከ160 ሺሕ ያላነሱ መንገደኞችንና ከ1,240 ቶን በላይ ጭነቶችን በማመላለስ 60 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች