Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የመጨረሻው ውይይት በቅርቡ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

  በህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የመጨረሻው ውይይት በቅርቡ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

  ቀን:

  ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ አለመግባባታቸውን በአራት ዙር ውይይቶች ለመፍታት በተስማሙት መሠረት፣ የመጨረሻውን ዙር ውይይት በጥር ወር መጀመሪያ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዘዋል።

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው የህዳሴ ግድቡን ድርድር የሚከታተሉ የኢትዮጵያ ወገን ከፍተኛ ኃላፊ በሦስቱ አገሮች መካከል ሲደረግ በቆየው የቴክኒክ ውይይት ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል የነበረ ቢሆንም፣ በግብፅ በኩል ጉዳዩ ፖለቲካዊ አቋም የተደረሰበት በመሆኑ በመጨረሻው ውይይት ስምምነት ተደርሶ በፊርማ ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

  የግብፅ ተደራዳሪዎች ከታኅሳስ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሱዳን በተደረገው ውይይት ቀደም ሲል በህዳሴው ግድብ ሙሌት ወቅት በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜቴር ኪዮብ ውኃ እንዲለቀቅና የሙሌት ሒደቱም የታላቁ አስዋን ግድብ ውኃ 165 ሜትር ከፍታ አለመውረዱን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ ሲያራምዱት የነበረውን አቋም አንስተው፣ ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃ ተፈጥሯዊ ፍሰትን ማረጋገጥ አለባት የሚል ከህዳሴ ግድቡ ጋር ግንኙነት የሌለው የሚመስል ነገር ግን ከህዳሴ ግድቡ ወጪ ያለውን የዓባይ ውኃን ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም የሚከለክል የውይይት ሐሳብ ማንሳታቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።

  ኢትዮጵያ በዚህ ሐሳብ ላይ ለውይይት እንኳን እንደማትቀመጥ እየታወቀ ይህንን ሐሳብ ያነሱት ጊዜ በመግደል አለመግባባትን ለመፍታት ወደ ተቀመጠው ቀጣይ አማራጭማለትም ሦስተኛ ወገንን በአሸማጋይነት ወደሚጋብዘው የትብብር መግለጫ ስምምነቱን አንቀጽ 10 ለመተግበር ፍላጎት እንዳላቸው ኃላፊው ገልጸዋል።

  በሱዳን ወይይት ከላይ የተገለጹትን 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብና የአስዋን ግድብ ከፍታ ቅድመ ሁኔታዎች መነሳታቸው ላይ ቢስማሙም የስምምነት ፊርማ ለማድረግ አለመፈለጋቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ይህም ውይይቱን ያለ ስምምነት የማጠናቀቅ ታክቲክ እንደሆነ አስረድተዋል።

  በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚካሄደው ስብሰባም ከዚህ የተለየ ውጤት ይኖራል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል። በመሆኑም ሦስተኛ ወገን በአሸማጋይነት ይግባ ወደሚለው ነጥብ ለመሸጋገር ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸው መረዳት እንደሚቻል፣ በኢትዮጵያ ወገንም ለዚህ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

  ቀጣዩን አማራጭ በተመለከተ የኢትዮጵያን አቋም ምን ሊሆን እንደሚችል ተጠይቀው፣ ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ ጊዜው ሲደርስ ቢታወቅ የተሻለ እንደሚሆን ገልጸዋል።

  በሱዳን የነበረውን ወይይት አስመልክቶ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተው የነበሩት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (/)፣ ግብፆች በቀጣዩ የአዲስ አበባ ውይይት ለስምምነት የቀረበ ሐሳብ ይዘው ሊመጡ እንደሚችሉ ተስፋ ቢኖራቸውም ወደ ስምምነት ፊርማ ግን ይገባሉ ለማለት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።

  የስምምነት ፊርማ ሳያኖሩ እንደተስማሙ ገልጸው ለሕዝባቸውም የህዳሴ ግድቡ በግብፅ ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ማስረዳትን ሊመርጡ የሚችሉበትን የስምምነት ፊርማ ጉዳይ፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ክፍት ሆኖ እንዲቀር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

  ይህ ካልሆነ የሚቀረው አማራጭ አንቀጽ 10 በማንሳት ሦስተኛ አሸማጋይ እንዲገባ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን በሦስቱም አገሮች ስምምነት ሲወሰን ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።

  በተጨማሪም አንቀጽ 10 የሦስተኛ ወገን አሸማጋይን ብቻ በአማራጭነት እንደማያቀርብ፣ ከዚያ በመለስ ወደ ሦስቱ አገሮቹ መሪዎች ሊመራም እንደሚችል ተናግረዋል።

  በአጠቃላይ ከዚህ አኳያ ያለው የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቦ፣ ወቅቱ ሲደርስ በእሳቸው በኩል እንደሚገለጽ ጠቁመዋል።

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...