Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበውጭ የሚኖሩ 52 ኢትዮጵያውያን ምሁራን የህዳሴ ግድቡ ውይይት በአግባቡ እየተመራ አይደለም አሉ

በውጭ የሚኖሩ 52 ኢትዮጵያውያን ምሁራን የህዳሴ ግድቡ ውይይት በአግባቡ እየተመራ አይደለም አሉ

ቀን:

በተለያዩ አገሮች የሚኖሩና ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የሚባል ኮሚቴ ያቋቋሙ 52 ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ባለሙያዎች 12 ምክንያቶችን የዘረዘሩበትን ደብዳቤ በማያያዝ፣ የህዳሴ ግድቡ ውይይት እየተመራ ያለበት አግባብ ልክ አይደለም ሲሉ በተለይ ግብፅን የኮነኑበትን ፊርማ ለአሥር አገሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት አቀረቡ፡፡

ይኼ የ52 ምሁራንና የተለያዩ ባለሙያዎች ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ፣ ለፓን አፍሪካ ፓርላማ ፕሬዚዳንት፣ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ፣ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ ለሩሲያ ፕሬዚዳንት፣ ለዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ለግብፅ ፕሬዚዳንት፣ ለዓረብ ፓርላማ አፈ ጉባዔ፣ ለግብፅ ምሁራንና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲደርስ የታለመ ነው፡፡

ደብዳቤው የአሜሪካና የዓለም ባንክ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ላለው ቅራኔ መፍትሔ ለማበጀት የሚያደርጉት ጥረት ከመልካም ዕሳቤ የመነጨ እንደሆነ በመግለጽ፣ ነገር ግን እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 6 ቀን 2019 ዓ.ም. በኢትዮጵያ፣ በሱዳን፣ በግብፅ፣ በአሜሪካና በዓለም ባንክ የወጣው የጋራ መግለጫ ለውይይቱና ለችግሮቹ መፍትሔ በቂ ጊዜ የማይሰጥ እንደሆነ በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የወደፊት ትውልድ ተጠቃሚነትን እንደሚጎዳ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ከናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ የዓለም ባንክና አሥር አገሮችን ያካተተ ማዕቀፍ ተቀምጦ ሳለ፣ የህዳሴ ግድቡን በገንዘብ አልደግፍም ያለው የዓለም ባንክ አሁን ገለልተኛ ታዛቢ ሆኖ መቅረቡ ምን ማለት ነው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ባለሙያዎቹና ምሁራኑ አክለውም የህዳሴ ግድቡን የውኃ አሞላል በተመለከተ በቴክኒክ ቡድን እንዲጠና ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የተስማሙ ቢሆንም፣ ግብፅ አሁንም ከስምምነቱ ወደ ኋላ እያለችና እየተደራጀች እንደምትገኝ በመጥቀስ ኮንነዋል፡፡ ይባስ ብሎም ግብፅ ዘመናዊ የድንበር አቋራጭ ወንዞች መዳኛ ስምምነቶችን ልክ እንደ ናይል ቤዚን ኢንሼቲቭና በአሜሪካና በሜክሲኮ መካከል እንዳለው ዓይነት ከመጠቀም ይልቅ፣ ለወቅቱ የማይመጥነውንና የተዛባውን የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን ይዳዳታል በማለት፣ ኢትዮጵያ የዚህ ስምምነት አካል ሆና ስለማታውቅ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም፣ አይችልም ብለዋል፡፡

የግብፅ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ ኃይልን ለመጠቀም እንደሚያስቡ በመግለጽ ማስፈራራት እየፈጸሙ እንደሆነም የሚያትተው ጽሑፉ፣ ግብፅ የህዳሴ ግድቡ ውኃ እንዳይሞላ የምታደርገው የማጓተት ተግባር በኢትዮጵያ ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸዋል፡፡ ይኼም እያደገ በመጣው የዋጋ ግሽበትና ከአሁን ቀደም  ባመለጡ መልካም ዕድሎች ሳቢያ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሚዛናዊ የሆነ መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው ኢትዮጵያ በዓባይ ምንጭ ላይና በግድቡ ሥራ ላይ ያላት ሉዓላዊነት በሚያረጋግጥ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ እንደሚመታ የታወቀ ሲሆን፣ ፍትሐዊና ሚዛናዊ መፍትሔ ማምጣት ካልተቻለ ዘግናኝና እጅግ አጥፊ የሆነ ታላቅ የአፍሮ ዓረብ ጦርነት ሊቀሰቀስ ስለሚችል ጥንቃቄ ይደረግ፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...