Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየቀድሞዋን የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጨምሮ 50 ሰዎች ክስ ተመሠረተባቸው

  የቀድሞዋን የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጨምሮ 50 ሰዎች ክስ ተመሠረተባቸው

  ቀን:

  የቀድሞዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀን (ኢንጂነር) ጨምሮ 50 ሰዎች ላይ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዓርብ ታኅሳስ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ክስ መሠረተባቸው፡፡

  ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ ላይ የቀድሞዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ (ኢንጂነር)፣ የቀድሞ የኤሌክትሪክ ኃይል የፖርትፎሊዮ ማኔጅመንት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብረዳ ማሩና የቀድሞ የኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊ አቶ ዓብይ ይሁን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውኃ የሚያርፍበት 123,189 ሔክታር ስፋት የሪዘርቪየር ክሊሪንግና ባዮማስ ዝግጅት ሥራ ደኖችን የመመንጠር፣ የማፅዳትና ከአካባቢው (ከግድቡ አርቆ) ወደ ተዘጋጀለት ቦታ የማጓጓዝ ሥራ ለማከናወን ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር ኅዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር 5,158,611,599.03 ብር መዋዋላቸውን ገልጿል፡፡ ሆኖም በውሉ አንቀጽ 6(1) መሠረት የምንጣሮ ሥራው በ720 ቀናት ውስጥ ማለትም ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. መጠናቀቅ እንዳለበት ቢደነግግም፣ በውሉ አንቀጽ 6(2) መሠረት ያልተከናወነውን ሥራ በመለየት ወ/ሮ አዜብና አቶ ብረዳ ዕርምጃ መውሰድ ነበረባቸው ብሏል፡፡ ነገር ግን ሁለቱ ተከሳሾች በውሉ መሠረት ሥራው አልቆ ርክክብ መፈጸም በነበረበት ወቅት ሥራው ገና 30 በመቶ ብቻ የተከናወነ መሆኑን እያወቁ፣ ውሉ ያላግባብ እንዲሻሻልና እንዲራዘም ማድረጋቸውን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

  ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ ተከሳሾች በመጀመርያው ውል አንቀጽ 5.2 የመጀመርያ ዙር ክፍያ የሚፈጸመው የተከናወነው ሥራ 50 በመቶ ሲደርስ ከአጠቃላይ ክፍያ 30 በመቶ እዲከፈል የሚደነግገውን፣ ያላግባብ ባሻሻሉት የማሻሻያ ውል አንቀጽ 5.2 ላይ 20 በመቶ በመቀነስ የተከናወነው ሥራ 30 በመቶ ሲደርስ ከአጠቃላይ ክፍያ 30 በመቶ የመጀመርያ ዙር ክፍያ ይፈጸማል ወደሚል እንዲሻሻል አድርገዋል ብሏል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፡፡ በመሆኑም የአጠቃላይ ክፍያው 20 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር 1,031,722,315.30 ብር ያላግባብ እንዲከፈል መደረጉን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

  በግንባታ ሥራዎች ግዥ መደበኛ የጨረታ ሰነድ አጠቃላይ የውል ሁኔታዎች አንቀጽ 60.3 መሠረት፣ ውል ከመፈጸሙ በፊት ምንም ዓይነት ቅድመ ክፍያ መፈጸም እንደሌለበት የሚደነግገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ወ/ሮ አዜብና አቶ ዓብይ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሜቴክ ጋር የሥራ ውል ሳይፈርም፣ 500 ሚሊዮን ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም መደረጉን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

  የቀድሞ የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ ኮሎኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤል ገብረ እግዚአብሔርና የቀድሞ የሜቴክ የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኃላፊ ኮሎኔል ያሬድ ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ የሜቴክ ኮርፖሬሽንን በመወከል፣ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የምንጣሮ ሥራ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ኅዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በገቡት ውል 5,158,611,599.03 ብር ከተፈራረሙ በኋላ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት በመጠቀምና የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል የውሉን 50 በመቶ 2,579,305,783.01 ብር ለሜቴክ ገቢ መደረጉን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ሆኖም በስምምነቱ አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ሥራው መጠናቀቅ የነበረበት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ቢሆንም፣ በፌዴራል ዋና ኦዲተር የተሠራው የኦዲት ሪፖርት እስከ ተጠናቀቀበት እስከ ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ከአራት ዓመት በኋላ በ50 በመቶ ክፍያ የውሉ 31.7 በመቶ ብቻ መከናወኑን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

  ሜቴክ ከተቀበለው 50 በመቶ ውስጥ 23 በመቶ ማለትም 595,321,945.39 ብር ብቻ በሥራው ውስጥ ለተሳፉት ድርጅቶችና ማኅበራት በመክፈል ቀሪውን 1,983,983,837.62 ብር ምን ላይ እንደዋለ አለመታወቁን የገለጸው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ኮሎኔል ሙሉና ኮሎኔል ያሬድ በሜቴክ አደረጃጀት መመርያ መሠረት የውል አስተዳደሩን በአግባቡ ባለመከተላቸውና ባለማስፈጸማቸው በሜቴክ ላይ 1,983,983,837.62 ብር የገንዘብ ኪሳራ አድርሰዋል ብሏል፡፡

  ሐምሌ 1 ቀን 2003 ዓ.ም. በወጣው የሜቴክ የግዢ መመርያ አንቀጽ 12 ላይ እንደ ተደነገገው ማንኛውም የኮርፖሬሽን ግዥ በግልጽ ጨረታ የሚፈጸም ሲሆን፣ ከግልጽ ጨረታ ውጪ ባሉ ሌሎች ዘዴዎች ግዥ መፈጸም ቢያስፈልግ በመመርያ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት እንደሚኖርባቸው የሚያዘውንና በመመርያው አንቀጽ 24.1 ግዢዎች በሥራ ክፍሎች ውስጥ በተቋሙ የግዥ አፅዳቂ ኮሚቴ በኩል ማከናወን እንደሚገባ የተደነገገውን በመጣስ፣ ኮሎኔል ያሬድ የሜቴክ ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ምንም ዓይነት ጨረታ ሳይከናወን ለ187 ድርጅቶችና ማኅበራት የህዳሴ ግድቡ ውኃ የሚተኛበት ቦታ የደን መመንጠር፣ መቆራረጥና ማፅዳት ሥራ በቀጥታ ያለ ጨረታ በመስጠት፣ ሜቴክ ያገኝ የነበረውን ዝቅተኛ ዋጋና የተሻለ ጥራት በማሳጣት ለድርጅቶቹና ለማኅበራቱ 585,999,217.08 ብር እንዲከፈል ማድረጋቸውን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

  በሜቴክና በሥራ ተቋራጮች መካከል በተገባው የምንጣሮ የሥራ ስምምነት ውል አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 8.3 መሠረት የሥራ ተቋራጮቹ ሥራውን ሠርተው ካጠናቀቁ በኋላ፣ ለሥራ አፈጻጸም ዋስትና የተያዘው መያዣ (ሪቴንሽን) እንደሚከፈላቸው በግልጽ ተመልክቶ እያለ፣ ድርጅቶቹ ለመመንጠር ውል የገቡትን ሔክታር ያህል መንጥረው ሳያስረክቡ ከውሉ ድንጋጌ ውጪ የኮርፖሬሽኑን ጥቅም በሚጎዳ መንገድ የተቀነሰባቸው መያዣ 4,355,403.73 ብር ድርጅቶቹና ማኅበራቱ በውሉ መሠረት የምንጣሮ ሥራውን ባለማስረከባቸው ምክንያት መወረስ ሲገባው፣ ከውሉ ድንጋጌ በተቃራኒው ኮሎኔል ሙሉ ገንዘቡ ለድርጅቶቹና ለማኅበራቱ እንዲከፈል በማዘዛቸው ምክንያት፣ 4,355,403.73 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

  ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስገባው 18 ገጽ ክስ ውስጥ ዘጠኝ የሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ሲከሰሱ፣ ሦስቱ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች ናቸው፡፡ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ውስጥ የተካተቱት ቀሪዎቹ 38ቱ ደግሞ በህዳሴ ግድቡ የደን ምንጣሮ፣ መቆራረጥና ማፅዳት ሥራ የተሰጣቸው ድርጅቶችና ማኅበራት ናቸው፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...