Monday, April 15, 2024

በየጊዜው ችግሮቹ የሚታደሱት የመሬት ሥሪት በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ለመንግሥታት መቀያየርና መውደቅ፣ እንዲሁም መናጋት ዋነኛ ምክንያት ሆነው እስከ ዛሬ ከዘለቁ ጉዳዮች አንዱ የመሬት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች አመፅና የ‹‹መሬት ላራሹ›› መፈክር ወዲህ የፖሊሲና የአመራር ማዕቀፍ ማዕከል ሆኖ የቆየው መሬት፣ ከዚያ ወዲህ በመጡት በደርግና በኢሕአዴግ መንግሥታት ለጥያቄው ምላሽ ይሆናሉ የተባሉ ዕርምጃዎች ቢወሰዱም፣ አጥጋቢ ምላሽና ዘላቂ የመሬት ሥሪት መፍትሔ በአገሪቱ ሊመጣ አልቻለም፡፡

በንጉሣዊ ሥርዓቱ የነበረውን የባላባቶች የመሬት ባለቤትነትና የጭሰኛ ሥርዓት በመቃወም በአዲስ አበባ በተማሪዎች ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚል መፈክር ይዘው ሠልፎች ሲያካሂዱ፣ በወቅቱ የነበረው ኢፍትሐዊና በዝባዥ እንዲሁም ለኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት ለሆነው ለፊውዳሉ ሥርዓት ብቻ ማቆያነት ይውል የነበረው መሬት ከፍተኛ ግፊቶችን አስከትሏል፡፡ እነዚህ ግፊቶች ቢደረጉም ሥርዓቱ ለጉትጎታዎችና ለውትወታዎች ደንታ ቢስ በመሆኑና ሊደረግ የነበረው አነስተኛ ማሻሻያም በእንጭጩ እንዲቀጭ መደረጉን በርካታ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ይኼ እምቢተኝነት ለሥርዓቱ መውደቅ ምክንያት ሆኖ ደርግ ሥልጣኑን ሲቆጣጠር፣ የመጀመርያውን የመሬት ሥሪት አዋጅ ተግባራዊ አደረገ፡፡ ማሻሻያውን በመደገፍም በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ከፍተኛ የድጋፍ ሠልፎች ተደርገው ነበር፡፡

‹‹በየትኛውም ዓይነት መለኪያ የደርግ ማሻሻያ ጥልቅና ሥር ነቀል ስለ ነበር ከቻይናና ከቬትናም ተመሳሳይ ድርጊቶች ጋር ተነፃፃሪ ነው፤›› ሲሉ፣ ይኼንን ማሻሻያ ዕውቁ የመሬት ሥሪት ባለሙያና በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች ያቀረቡት የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ሪሰርች ፌሎ አቶ ደሳለኝ ራህመቶ ያደንቁታል፡፡

ይሁንና ምንም እንኳን መሬትን የተመለከቱ ጥያቄዎች መልካቸውን የቀየሩ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ እጅግ ወሳኝ ሥፍራ ያለው ጉዳይ የመሬት ነው ይላሉ አቶ ደሳለኝ፡፡

ለዚህም ይመስላል ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በሚል ዕሳቤ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተደረጉ ስድስት ተከታታይ ውይይቶች ከተገባደዱ በኋላ፣ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍኤስኤስ) የተባለው አገር በቀል የጥናትና ምርምር ተቋም ለአራት ወራት የሚዘልቅ ተከታታይና በመሬት ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያጠነጥን ‹‹መሬት፣ የመሬት አጠቃቀምና የምግብ ዋስትና በኢትዮጵያ›› የሚል ሕዝባዊ ውይይት የጀመረው፡፡ ሐሙስ ታኅሳስ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዝማን ሆቴል በተካሄደው የመጀመርያው የውይይት መድረክ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ የሆኑት አቶ ደሳለኝም ይኼንን አስፈላጊነት አስምረውበታል፡፡

ለውይይት መድረኮቹ ማስተዋወቂያነት ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍኤስኤስ) ባዘጋጀው በራሪ ወረቀት፣ ኢትዮጵያ ለአሥር ተከታታይ ዓመታት ያስመዘገበችውን ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እንዲሁም በመሠረተ ልማት መስፋፋትና በማኅበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት ረገድ የተመዘገቡ መልካም ውጤቶች እንዳሉ በማስገንዘብ፣ ‹‹እነዚህ መልካም ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው አገሪቱ ዛሬም በዕድገት ወደ ኋላ ከቀሩ አገሮች ተርታ ለመውጣት አልቻለችም፤›› ሲል ይተቻል፡፡ አያይዞም የኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎችን በማሳደግ የሥራ አጥነትን ለመቀነስ የተደረገው ጥረት እምብዛም አጥጋቢ እንዳልነበር በማተት፣ አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በግብርና ላይ ጥገኛ እንደሆነ፣ ግብርናው 84 በመቶ ለወጪ ንግድና 80 በመቶ የሥራ ሥምሪትን እንደሚሸፍን በመጥቀስ፣ ጽሑፉ ጉድለቶችን ይጠቁማል፡፡ ግብርናው ይባስ ብሎ በተፈጥሯዊ፣ አካባቢያዊና ቴክኖሎጂያዊ በሆኑ መዋቅራዊ ችግሮች የተተበተበ ነው ይላል፡፡

‹‹አነስተኛ አርሶ አደሮችን በሚገባ ያላማከለ የመሬት ሥሪት ሥርዓት ጥያቄዎች፣ ወጥ የሆነና የተፈጥሮ ሀብትን ሥርጭት ያገናዘበ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖር፣ እንዲሁም ለአነስተኛ ገበሬዎች የሚሰጡ ድጋፎች መጠንና ጥራት ማነስ፣ ክፍለ ኢኮኖሚውን አንቀው ከያዙት መዋቅራዊ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፤›› ሲልም የመሬት ችግሩ አገሪቱ የተመሠረተችበትን ዘርፍ እየጨቆነው እንደሚገኝ ጽሑፉ ያስረዳል፡፡

ሆኖም የአገሪቱ የመሬት ሥሪት ችግርን ለመቅረፍ ከተወሰዱ ዕርምጃዎችም እንደሚመነጭ አቶ ደሳለኝ ያስረዳሉ፡፡ ለአብነትም ምንም እንኳን የደርግ የመሬት ሥሪት ማሻሻያ አዋጅ ሥር ነቀልና ጥልቅ እንደነበር ቢገልጹም፣ በየወቅቱ በዘፈቀደ ሲደረጉ የነበሩ የመሬት ሥርጭት ይዞታዎችን እያቀጨጨ መምጣቱን፣ የሕዝብ ቁጥርን ያገናዘበ አሠራር መዘርጋት አለመቻሉ፣ ሥጋት ሆኖ ብቅ ላለው መሬት አልባነት ምክንያት መሆን፣ እንዲሁም ለእርሻ ሥራ የጉልበት ቅጥር መከልከሉ ያስከተለው ሥራ አጥነት የደርግ ማሻሻያ ድክመት እንደሆኑ ይጠቁማሉ፡፡

የዚህ የደርግ መንግሥት የመሬት ሥሪት ማሻሻያ ዋነኛ ባህርያት የመሬት የግል ባለቤትነትን ማስቀረትና የሕዝብ ማድረግ፣ አርሶ አደሮች የሚያርሱት መሬት ማግኘት እንዳይችሉ ማድረጉ፣ መሬት በሽያጭ፣ በሊዝ፣ በሞርጌጅ ወይም በውርስ እንዳይተላለፍ ማድረጉ፣ ጭሰኝነትን ማስቀረትና መሬት በአራሹ እንጂ በጉልበት ሠራተኛ ሊታረስ እንዳይችል መከልከል ሲሆኑ፣ ከደርግ በኋላ የመጣው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መንግሥት ከሞላ ጎደል መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ ይኼንን አሠራር አስቀጥሏል፡፡

‹‹ልዩነቱ መሬት ለወራሾች መተላለፍ መቻሉ፣ የአጭር ጊዜ ኪራይ መፈቀዱ፣ እንዲሁም መሬትን በቅጥር ጉልበት ማሳረስ መቻሉ ነው፤›› ሲሉ አቶ ደሳለኝ ያስረዳሉ፡፡

ኢሕአዴግ በተከተለው የፌዴራል ሥርዓት የመሬት አስተዳደርን ሥልጣን ለክልሎች ያስተላለፈ ሲሆን፣ ክልሎች የሚያወጧቸው ሕጎች የሚለያዩ መሆኑ ብሎም በባለመሬቶችና በሕግ ባለሙያዎች መካከል የነበረው የሕግ ግንዛቤ ውስንነት ኢሕአዴግ በ1990 እና በ1997 ያወጣቸው የመሬት ሥሪት የሕግ ማዕቆፎች ያስከተሉት ችግር እንደነበር አቶ ደሳለኝ ገምግመዋል፡፡ ሆኖም በ1997 ዓ.ም. የወጣው የፌዴራል መንግሥት ሕግ ያስተዋወቀው የመሬት ምዝገባና የይዞታ የምስክር ወረቀት ወሳኝ ዕርምጃ ነው ይላሉ፡፡

ይኼ የመሬት ምዝገባና የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በአርሶ አደሮቹ ሰፊ ተሳትፎ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወነ መሆኑን በማስታወስ፣ ድክመቶች እንደነበሩበት ግን አስታውቀዋል፡፡

‹‹የመሬት ምዝገባ መሠረቱ በገበሬዎች መካከል ግጭት፣ ፀብና ክስ እንዳይኖር መሠረት ይጥላል ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ድንበሩን ስለሚያውቅ፡፡ ይኼ የሚሆነው ደግሞ ድንበሩ በማያወላውል መሠረት ሲቀመጥ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራውን የሠራው የአርሶ አደሮች ኮሚቴ መሬቱን ለመለካት መሣሪያ የለውም፡፡ በበርካታ ቦታዎችም በዓይን ግምት፣ በገመድ፣ በእንጨት፣ በክንድ፣ በዕርምጃ ተለክቶ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ የሚያዳግት ነበር፡፡ ቋሚ ድንበሮችም አልነበሩምና በድንጋይ፣ በዛፍ እንዲሁም በቁጥቋጦ የተሠሩ ተንቀሳቃሽ ድንበሮች ነበሩ፡፡ ስለዚህም የመሬት ግጭቶች ይቀንሳሉ ተብሎ የተሠራ ቢሆንም እንዲያውም ጨምሯል፤›› በማለት አቶ ደሳለኝ የአሠራሩን ድክመቶች ይዘረዝራሉ፡፡

ሁለተኛው ዙር አሁን እየተተገበረ እንደሆነ በመጠቆምም፣ በዘመናዊ የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚሠራና እያንዳንዱ ባለ ማሳ ካርታ ተሰጥቶት እንደሚገኝ በመጠቆም፣ በፊት በባህር መዝገብ ይመዘገብ የነበረው የባለ ይዞታዎች መሬት አሁን ዲጂታል በመሆኑ ለማስተካከልና ለማሳደግ ያግዛል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ይኼ የይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባ ባለይዞታዎች መሬታቸውን እንዲንከባከቡ ምርታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ፣ የማሳ ወሰን በግልጽ ስለሚታወቅ የድንበር ግጭቶችን እንደሚቀንስ፣ አርሶ አደሮች ፋይናንስ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው መሆኑ፣ እንዲሁም ሴቶች ከባለቤታቸው ጋር በጋራ ወይም በግል የይዞታ ማረጋገጫ እየተሰጣቸው ስለሚገኝ ለሴቶች አቅም መጎልበት አሌ የማይባል ጠቀሜታ ያስገኛል በማለት ምዝገባውና የይዞታ ማረጋገጫው የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ይዘረዝራሉ፡፡  

ሆኖም ዛሬም ቢሆን የመሬት ሥሪቱ ተግዳሮቶች ያሉበት እንደሆነ ገልጸው፣ እነዚህ ተግዳሮቶችን ውስጣዊና ውጫዊ ሲሉ ይከፍሏቸዋል፡፡ ውስጣዊ (Endogenous) ተግዳሮቶች ከሥርዓቱ የሚመነጩ እንደሆኑ በመቆጠም፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መጨመር እያስከተለ ያለው የመሬት እጥረት፣ የመሬት መበጣጠስና መሬት አልባነት ናቸው ይላሉ፡፡ ውጫዊ (Exogenous) ተግዳሮቶች ደግሞ ከሥርዓቱ ውጪ ያሉ ሲሆኑ፣ በኢንቨስትመንት መስፋፋት ሳቢያ በእርሻ መሬት ላይ የሚደርስ ጫና፣ የከተሞች መስፋፋትና የአርሶ አደሮች መሬት መመናመን የእነዚህ ተግዳሮቶች መገለጫዎች ናቸው ይላሉ አቶ ደሳለኝ፡፡

‹‹የአገሪቱ ልማት መቀጠል ካለበት የመሬት ጥያቄ አሁንም አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፤›› የሚሉት አቶ ደሳለኝ፣ ‹‹ነገር ግን በ1960ዎቹ ከነበረው ጥያቄ የአሁኑ ይለያል፣ ያኔ መሬት ላራሹ ነበር፡፡ አሁን መሬት ባራሹ እጅ ነው፡፡ ግን የመሬት ጥበት፣ መሸርሸር፣ መበጣጠስና የመሬት ዋስትና ጥያቄዎች አሉ፡፡ አሁን ያለው ጥያቄ ዓይነቱና ይዘቱ የዛሬ 60 ዓመት ከነበረው ይለያል፡፡ ሆኖም አሁንም ወሳኝ ጥያቄ ነው፤›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አመሐ ዳኘው፣ አሁን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ በዋናነነት የመሬት ነውና እንዴት ይፈታ ሲሉ ጥናት አቅራቢውን ጠይቀዋል፡፡ በተመሳሳይ አቶ ኃይሉ ተስፋው የተባሉ ተሳታፊ ዕውን በዚህ ዘርፍ ጥናት የሚሠሩ ባለሙያዎች መንግሥታትን እያማከሩ ነው ወይ? ጥናቱ ችግር ይዘረዝራል እንጂ መፍትሔ አይጠቁምም በማለት ጠይቀዋል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት አቶ ደሳለኝ፣ ‹‹እውነት ለመናገር መፍትሔ የሚለው ላይ እፈራለሁ፣ የመሬት ጥያቄ የሚያስፈራ ነው፤›› በማለት፣ በተለይ ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት በተከሰተው የፖለቲካ ለውጥ መሬት እንደ ምርት ግብዓት ማየት እንደማይቻልና ከብሔር፣ ከሃይማኖትና ከማንነት ጋር በመተሳሰሩ ስሜታዊነት ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ስለዚህ በዚህ ነው መሄድ ያለባችሁ ማለት ያስቸግራል፣ እኔ እፈራለሁ፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

አቶ በላይ ደምሴ የተባሉ የቀድሞ የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ የነበሩና በአፍሪካ የመሬት ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አማካሪና በሙያ አግሮ ኢኮኖሚስት የሆኑ የውይይቱ ተሳታፊ፣ በመድረኩ የቀረበውን ጽሑፍ ለምን ለመንግሥትና ለፓርቲዎች ግብዓት እንዲሆን ተሰናድቶ አይቀርብም በማለት ጠይቀዋል፡፡

‹‹ብልፅግና ፓርቲ ደርግ የመሬትን ጥያቄ፣ ኢሕአዴግ ደግሞ የብሔርን ጥያቄ ፈትቶልናል፣ አሁን የእኛ ሥራ የዴሞክራሲ ጉዳይ ነው ይላል፡፡ እንዴት ነው ደርግ የመሬት ጥያቄ ፈታ የሚባለው? ጉዳዩ አሁንም ጥያቄ ሆኖ ሳለ? ስለዚህ የፖሊሲ ጉዳዮች በደንብ ቀርበው መታየት አለባቸው፤›› ሲሉ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡  

አቶ በላይ አክለውም መሬት በሌሎች አገሮች እንዳለው ሁሉ በማዕከላዊ ጠንካራ ተቋም የሚመራበት፣ በተበታተነ ሁኔታ በግብርና ሚኒስቴርና በተለያዩ ተቋማት የሚገኘው አሠራር ተሰባስቦ፣ ተቋማዊ ሆኖ እንዴት ይመራል ሲሉም ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡

ለዚህ ምላሽ የሰጡት አቶ ደሳለኝ ተቋማዊ የሆነ አሠራርን በተመለከተ የተንፀባረቀውን ሐሳብ እንደሚደገፉ ገልጸው፣ ‹‹እኔ አገር አቀፍ የመሬት ኮሚሽን እንዲቋቋምና ለክልሎች ምክር እንዲሰጥ አንዴ አስተያየት ሰጥቼ ነበር፡፡ በአንዳንድ አገሮች በሚኒስትሮች ደረጃ ነው ያለው፣ በአገር ደረጃ ትልቅ ተቋም ያስፈልገናል፤›› ብለዋል፡፡

በመድረኩ የመሬት ሥሪቱን ለማስተካከል መሬት መሸጥና መለወጥ እንዲቻል የግል ባለይዞታነት መብት እንዲረጋገጥ የጠየቁ ተሳታፊዎች ሲኖሩ፣ ከአሁን ቀደም ግን በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ መንግሥት የመሬት ሥሪቱን የመቀየር ሐሳብ ይኖረው እንደሆነ በሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የመሬት ጉዳይ የሕገ መንግሥት መሻሻልን ስለሚጠይቅ ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል አብሮ ይታያል ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -