Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሰኔ 15 ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጣሪ ተከሳሾች ላይ ብይን ተሰጠ

በሰኔ 15 ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጣሪ ተከሳሾች ላይ ብይን ተሰጠ

ቀን:

በእነ ጄኔራል ሰዓረ መኮንንን ግድያ ከቀረቡት ክሶች አንዱ ይሻሻል ተባለ

‹‹ይኼ ነገር [ብይኑ] ነገሮች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄዱ ያደርጋል››

የተከሳሾች ጠበቆች

በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ በአምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ በአቶ እዘዝ ዋሴና በአቶ ምግባሩ ከበደ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ በጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና በጓደኛቸው ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ላይ፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በተፈጸመ ግድያ ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው 13 ተከሳሾች ላይ ማክሰኞ ታኅሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ብይን ተሰጠ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ብይን እንዳስታወቀው፣ ተከሳሾች ያቀረቡት የመጀመርያ የክስ መቃወሚያን አልተቀበለውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ ባቀረበው ክስ ላይ ተከሳሾች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ በማስረጃና በክርክር ሒደት ከማረጋገጥ በስተቀር፣ በመቃወሚያ ብቻ ክሱ የሚሻሻል ወይም ውድቅ የሚደረግ ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ መቃወሚያውን እንዳልተቀበለው በብይኑ ገልጿል፡፡ ነገር ግን የጄኔራል ሰዓረ የግል ጠባቂያቸው እንደነበረና እሳቸውንና ጓደኛቸውን በመግደል ወንጀል የተከሰሰው አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ ካቀረባቸው ሦስት የቅድመ ክስ መቃወሚያዎች ሁለቱ ውድቅ ተደርገው አንዱ እንዲሻሻል ፍርድ ቤቱ በብይኑ አስታውቋል፡፡

ተከሳሹ ሟች ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌንና የአባቱ ስም ያልተገለጸ ጽጌ የተባለ ግለሰብን ስለማገናኘቱና ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን ሊያስገድል እንደነበር በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ ያቀረበበትን ክስ ላይ ተቃውሞ ቢያቀርብም፣ መቃወሚያው ውድቅ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ በክስ ዝርዝሩ ውስጥ በግልጽ ተገልጾ ስለሚገኝ የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ ጄኔራሎቹ የት ቦታ እንደተገደሉና ተከሳሽ ግድያ ከፈጸመ በኋላ ተከቦ ስለመያዙ በክሱ ላይ ባለመገለጹ፣ ዓቃቤ ሕግ ይኼንን ክስ እንዲያሻሽል ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡

የተከሳሾች ጠበቆች ብይኑን ከሰሙ በኋላ ባቀረቡት የቅሬታ አቤቱታ፣ ደንበኞቻቸውን ወክለው ያቀረቡት የክስ መቃወሚያም ሆነ በችሎት ያቀረቡት አቤቱታ በደንብ አለመታየቱን ተናግረዋል፡፡ ይኼ ነገር [ብይኑ] ‹‹ነገሮች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄዱ ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

ተከሳሾቹ ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት በማረሚያ ቤት ሳንሱር እንደሚደረጉ፣ ትኩስ ነገር እንደማይገባላቸው፣ መጽሐፍ መከልከላቸውንና ቤተሰብ ሳይጠይቸው እንዲመለስ ስለመድረጉ ባቀረቡ አቤቱታ ላይ የማረሚያ ቤት አስተዳደር በጽሑፍ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ምላሹም፣ ‹‹ሊጠይቃቸው መጥቶ የተመለሰ የለም፤›› የሚል መሆኑን ችሎቱ ገልጿል፡፡

የተከሳሾች ጠበቆች ምላሹን በመቃወም ባቀረቡት አቤቱታ ማረሚያ ቤቱ አሁንም ሳንሱር እያደረጋቸው መሆኑን፣ ተከሳሾች ሕክምና እንዲያገኙ ቢደረግም፣ አሥር አለቃ መሳፍንት ሐኪም ዘንድ ቀርቦ ቀጠሮ ብቻ ተሰጥቶት በመመለሱ እንደታመመና ፊቱም እየተበላሸ እንደሆነ አስረድተው፣ ተከሳሾች በቂ ሕክምና እያገኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ትኩስ ነገርና መጽሐፍም መከልከላቸውንም አክለዋል፡፡

አቶ አየለ አስማረ (ዘጠነኛ ተከሳሽ) ባቀረበው አቤቱታ እንደተናገረው፣ ቀደም ባለው ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ ፖሊስ በምርመራ ወቅት የወሰደባቸው ዕቃዎቻቸው እንዳልተመለሰላቸው፣ ሞባይሎቻቸውንም ፖሊሶች እየተጠቀሙባቸው መሆኑን፣ ሌሎች ሥራዎችን ለቤተሰቦቻቸው ውክልና እንዳይሰጡ መታወቂያቸውን ፖሊስ ይዞ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ተናግሯል፡፡

በማረሚያ ቤት ያሉ ጠባቂዎቻቸውን አንድ ነገር ሲጠይቋቸው ጠባቂዎቹ ዞር ብለው በሌላ ቋንቋ እንደሚነጋገሩ ጠቁሞ፣ የት እንዳሉ ግራ እንደሚገባቸውና እየተፈጸመባቸው ያለው ነገር አማራ በመሆናቸው የዘር ጥቃት መሆኑን ተከሳሹ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡  

አቶ በለጠ ካሳ (13ኛ ተከሳሽ) ደግሞ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገረው፣ ማረሚያ ቤቱ ‹‹ቀርቦ የተመለሰ ቤተሰብ የለም›› ያለው ውሸት ነው፡፡ ሁለት የማረሚያ ቤቶች ኮማንደሮች (ስማቸውን ጠቅሶ) ከ700 በላይ ጠያቂዎችን እንደመለሱ እንደነገሩት፣ የቴዲ አፍሮ ጠያቂና የእነሱ ጠያቂዎች ብዛት አንድ ዓይነት መሆኑንም እንደነገሩት አስረድቷል፡፡ ከችሎቱ የተለየ ነገር የጠበቀ ቢሆንም፣ ከጀርባው ሰው እንዳለና እንደሚመራ እንደሚያስታውቅ ገልጾ ፍርድ ቤቱ ነፃ መሆኑንና ገለልተኛ አቋም እንዳለው እንዲያሳየው ጠይቋል፡፡

የአብን አመራር አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ (12ኛ ተከሳሽ) ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ የሌሊት ልብስ (ፒጃማ) ተከልክሏል፡፡ ባለቤቱ የሌሊት ልብሱን ፍርድ ቤት ይዛ እንድትመጣ ነግሯት እንደነበር ተናግሮ፣ ‹‹አማራነት እንደ ወንጀል እየታየ ነው፤›› ብሏል፡፡ የሌሎች ክልሎች ተከሳሾች የራሳቸው ክልል ቴሌቪዥን እንዲከፈት ሲጠይቁ ሲከፈትላቸው፣ የአማራ ክልል ቴሌቪዥን እንዲከፈት እነሱ ሲጠይቁ ግን እንደማይከፈትላቸው አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ገለልተኝነት ከዚህ እንደሚጀምርም አክሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን አቤቱታ ከሰማ በኋላ ብይን ሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ከላይ በተጠቀሰው አንድ መቃወሚያ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ፣ የማረሚያ ቤት አስተዳደር ኃላፊ ለምን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳልተተገበረ ቀርበው እንዲያስረዱ በማዘዝ፣ ለጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

ችሎቱ ትዕዛዙን ሰጥቶ እንዳበቃ የችሎቱ ታዳሚዎች ቀድመው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ፣ ተከሳሾች ተከትለው ወጥተዋል፡፡ አዳራሹ ሞልቶ በርካታ ሰዎች ውጭ ሆነው የዕለቱን ችሎት፣ ብይንና ትዕዛዝ በመጠባቅ ላይ ነበሩ፡፡

ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ በአዲስ አበባ፣ በፌዴራል፣ በፈጥኖ ደራሽና በማረሚያ ቤት በርካታ ፖሊሶች ታጅበው የቀረቡት ተከሳሾች፣ ከችሎት ወጥተው በር ላይ ሲደርሱ እጃቸውን ወደ ታዳሚዎች በማውለብለብ፣ ‹‹አማራ አይሞትም! አንድ አማራ!…) የሚሉ መፈክሮችን በጩኸት አሰምተዋል፡፡ በማረሚያ ቤት መኪና ውስጥ ከገቡ በኋላ በከፍተኛ ውጥረት እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

በመቀጠል በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ ታዳሚዎች እጆቻቸውን ወደ ላይ በማድረግና በማጣመር በሠልፍ ሆነው በፍርድ ቤቱ የተለያዩ በሮች ሲወጡ ፖሊስ ግማሾቹን ወደ ሜክሲኮና ዳርማር እንዲሄዱ፣ በሌላ በር የወጡትን ደግሞ ወደ ጦር ኃይሎች መስመር እንዲሄዱና እንዳይገናኙ በማድረግ በትኗቸዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...