Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ኢትዮጵያን ከሥጋት ነፃ የማያደርግ ፉክክር ፋይዳ የለውም!

  የአውሮፓውያን አሮጌ ዓመት (2019) ተጠናቆ አዲሱ ዓመት (2020) ተጀምሯል፡፡ የዓለም ታላላቅ ሚዲያዎችና ታዋቂ ጸሐፍት የአሮጌውን ዓመት ዋና ዋና ክስተቶችና ፈተናዎች በትውስታ ሲያቀርቡ ሰንብተዋል፡፡ አዲሱ ዓመት ምን ይዞ ይመጣ ይሆን ሲሉም ግምታቸውን አሥፍረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. 2020 እንዳለፈው ሁሉ የራሱን ጓዝ ይዞ መምጣቱ የማይቀር ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነው ‹ክራይሲስ ግሩፕ› መሰንበቻውን ያስነበበው መጣጥፍ ትልቅ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 ግጭት ሊታይባቸው ከሚችሉ አሥር አገሮች ተርታ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ ከአፍጋኒስታንና ከየመን ቀጥላ በሦስተኝነት ተመዝግባለች፡፡ ‹ክራይሲስ ግሩፕ› ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ የመግባት ሥጋት ያለባት አገር ናት በማለት በዳበረ ትንተና ላይ የተመሠረተ ብይን ሲሰጥ፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ ምናልባትም ወደፊት የማያጋጥም ድንቅ ዕድል በእጇ እንደጨበጠች አስረግጦ በመግለጽ ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ነው ዓለም ኢትዮጵያን ሊደግፋት ይገባል ሲልም ጥሪ ያቀረበው፡፡ ይህንን በመረጃና በማስረጃ፣ እንዲሁም ወቅታዊውን መሬት ላይ የረገጠ እውነታ ያነጠረ የሥጋት ትንተና ሲቀርብ በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ መጪውን ምርጫ በሰላም አከናውና የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት፣ ከወዲሁ ከውጤቱ ይልቅ ሒደቱን የሚያሰማምሩ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያስፈልጋለ፡፡ ከሥጋት ነፃ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ፉክክር እንዲኖር የሚያስችል ንጣፍ ለማዘጋጀት በጋራ መረባረብ የግድ ይላል፡፡

  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባትና ኢትዮጵያን እውነተኛ ፌዴራላዊት ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ የማድረግ ተግባር ቀዳሚ ሥራው፣ ለውጡን ከአደጋ በመታደግ ሐዲዱን እንዳይስት ማድረግ ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የለውጥ አመራር መደገፍ ያለበት በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ዕርቀ ሰላም ለማውረድ፣ የዴሞክራሲን መደላድል ለማመቻቸት፣ ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት ለመገንባት ደፋ ቀና በማለቱና በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል አንፃራዊ ዕድል ለመፍጠር በመትጋቱ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የለውጡ ቡድን የያዘው መስመር እንደ ሌሎቹ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ለሕዝብ ፈቃድና ውሳኔ እንደ አማራጭ ቀርቦ የሚበየንበት ነው፡፡ የሚፈለገውም ይህ ዓይነቱ ዕሳቤ ነው፡፡ ይህንን ዕሳቤ ትቶ በተቃራኒ አቅጣጫ ሲነጉድ ውሳኔው የሕዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በመርህ የሚመራ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ያስፈልጋታል ሲባል፣ የፖለቲካው የጨዋታ ሕግ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ሲያቅትና የተለመደው እንካ ሰላንቲያ ውስጥ ሲገባ ከግጭት ሥጋት ውስጥ መውጣት አይቻልም፡፡ የውጭዎቹ እየተናገሩት ያሉት ትንቢት ይሰምርና መሳቂያ መሳለቂያ መሆን ይከተላል፡፡ ከታሪካዊ ስህተቶች አለመማር ያደረሰው ጉዳትና ጠባሳ አልሽር ብሎ አገር እየተጨነቀች፣ ዓይን እያየ ሰተት ብሎ የባሰው ቀውስ ውስጥ መዘፈቅ አይገባም፡፡ ለዘመኑም አይመጥንም፡፡

  ፀጥታና ዴሞክራሲን ማደላደል የጋራ ሥራቸው ለማድረግ ቅድሚያ የማይሰጡና ሥልጣንና ጥቅምን የሚያስቀድሙ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ‹ክራይሲስ ግሩፕ› የታየውን ፍጅት መደገስ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ከፍጅትና ከዕልቂት መታደግ ከተፈለገ፣ ፋይዳ ቢስ አማራጮችንና የሥልጣን ጥማትን ገታ በማድረግ ለፍትሐዊና ለእውነተኛ ምርጫ ክንውን የበኩልን አዎንታዊ ሚና መጫወት ያስፈልጋል፡፡ ለመንግሥት ሥልጣን መውጫና መውረጃው ብቸኛ መንገድ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር መተባበር የግድ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ምርጫ 2012 ተካሄደም አልተካሄደም በገዛ ራሱ ግብ አለመሆኑን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማደላደል ገና ብዙ ምርጫዎችና በርካታ አምስት ዓመታቶች ትፈልጋለች፡፡ ከዚህ ቀደም በየአምስት ዓመቱ ሳያሰልስ ለአካባቢና ለፌዴራል ተወካዮች ምክር ቤቶች ምርጫ የተካሄደባት፣ በምክር ቤቶቹም ውሳኔ የአካባቢና የፌዴራል ሥልጣን አመራሮች የሚሾሙባት አገርም ነበረች፡፡ ሒደቱ ግን በፍፁም ዴሞክራሲያዊ ሆኖ አያውቅም፡፡ ምክር ቤቶቹ በምርጫ ተደራጅተው አያውቁም፡፡ ሿሚነታቸውና ተቆጣጣሪነታቸውም ከአፍ ያለፈ እውነት ሆኖ አያውቅም፡፡ የእዚህ ምክንያቱ በተለይ የፀጥታ መዋቅሮች ከፖለቲካ ቡድን መዳፍ ነፃ ባለመሆናቸውና ወገንተኛ ስለተደረጉ ነው፡፡ ምርጫዎች የአንድ ቡድን መጫወቻ ከመሆን ያላመለጡት በዚህ ምክንያት ነው፡፡

  በኢትዮጵያ ምድር በመከናወን ላይ ያለው ለውጥ ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶችና መዋከቦች ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ሲባል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤትነት በዴሞክራሲያዊና በነፃ ምርጫ መረጋገጥ ስለሚኖርበት ነው፡፡ ይህም ፍላጎት አስተማማኝ በሆነ መሠረት ላይ እንዲቆም፣ መንግሥታዊ አውታራትና መዋቅሮች ከየትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ ቡድን ታማኝነት ነፃ ሆነው እንዲታነፁ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ የሚቀድም አማራጭም ሆነ የሥልጣን ጥም ሊኖር አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ አደራ በልተው፣ ዳግም ሊገኝ የማይችለውን ይህንን የታሪክ አጋጣሚና ዕድል ማስመለጥ የለባቸውም፡፡ ዓለም ኢትዮጵያን ሊረዳት ይገባል ተብሎ በውጭ ሰዎች ጥሪ ሲቀርብ፣ አገርን ኪሳራ ውስጥ ከቶ ሕዝቡን ለሰቆቃ የሚዳርግ ቀውስ ውስጥ መግባት አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት አገር ናት፡፡ ይህ ተስፋ ለምልሞና አብቦ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ይገባል፡፡ ከግጭት ወደ ግጭት የሚደረገው የሞኝነት ጉዞ ካላቆመ እንኳን ምርጫ ቀርቶ ህልውናም አይታሰብም፡፡

  የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ በአገር ሁለንተናዊ ጉዳዮች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ በሙሉ፣ በአንድ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ መግባባት አለባቸው፡፡ እንደሚታወቀው በፖለቲካ ዘላቂ ወዳጅም ጠላትም የለም፡፡ የኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ክፋቱ ይህንን እውነታ መቀበል አለመፈለጉ ነው፡፡ ልዩነትን አጥብቦ በጋራ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማስፋት ይልቅ፣ ለአገር በማይጠቅሙ ንትርኮች  እየተጋጩ ንፁኃንን ለአደጋ መዳረግ ተለምዷል፡፡ ግጭቶቹ የብሔርና የሃይማኖት ገጽታ እንዲላበሱ እየተደረጉ አገር ለማፍረስ የሚቋምጡ አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ መጪውን ምርጫ ሒደቱን ከማሳመር ይልቅ፣ ውጤቱ ላይ በማተኮር የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ ያደባሉ፡፡ ‹ክራይሲስ ግሩፕ› ይህንን ችግር ከወዲሁ እያመላከተ ተጠንቀቁ እያለ ነው፡፡ ብሔርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገው ፌዴራሊዝም ግጭቶችን ለማራገብ እንደ ነዳጅ ሊያገለግል ይችላል ሲልም አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ዩጎዝላቪያ የምትባለውን አገር ፍርክስክሷን ያወጣው ቀውስ፣ በኢትዮጵያ ሊያጋጥም እንደሚችል ሥጋት ያላቸው እንደሚያስጠነቅቁም አስታውሷል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ የተስፋ ምንጭ መሆኑንና ድጋፍ እንደሚገባው አክሏል፡፡ ከቀውሱ ይልቅ ተስፋው ላይ ማተኮር ለበርካታ ችግሮች መፍትሔ ያመጣል፡፡ ይህ ተስፋ ለሥልጣን መንገብገብን፣ ጥቅም አሳዳጅነትንና መሰሪነትን የሚቋቋምና መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ዘመናዊ፣ ሥልጡንና አርቆ አሳቢ ፖለቲከኞች ለዚህ ምኞት ዕውን መሆን የጋራ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን ከሥጋት ነፃ የማያደርግ ፉክክር ፋይዳ የለውምና!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...

  የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

  የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...

  ሰላም ዘላቂ የሚሆነው ቃል ሲከበር ብቻ ነው!

  እንደ አለመታደል ሆኖ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከተከረመ በኋላ የሰላም መንገድ ተጀምሯል፡፡ በአገር በቀል ሽምግልና ማለቅ የነበረበት ከአገር ውጪ አስጉዞ፣ በባዕዳን...